Saturday, 03 November 2018 15:52

አስገራሚው የጋዜጠኞች እገታ በጋምቤላ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(0 votes)

   ከጋምቤላ ክልል ዋና ከተማ በ42 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደምትገኘው አቦቦ ወረዳ ያቀናነው ባለፈው እሁድ ማለዳ ላይ ነበር፡፡ የጉዟአችንም ዋንኛ ዓላማ በክልሉ በተለይም በአቦቦ ወረዳ ውስጥ ስለሚገኙ የእርሻ ልማት ኢንቨስትመንት ስራዎችና ከዚሁ ጋር በተያያዘ በወረዳው በስፋት ይስተዋላል ስለሚባለው የመልካም አስተዳደር ችግር በስፍራው ተገኝተን ለማየት፣ የሚመለከታቸውን አካላትም አነጋግረን ለመዘገብ  ነበር፡፡
ከስድስት የተለያዩ ሚዲያዎች የተውጣጡ ስምንት አባላት ያሉት የጋዜጠኞች ቡድን በስፍራው ደርሶ በወረዳው በተለያዩ የኢንቨስትመንት ስራዎች ላይ ከተሰማሩ ባለሃብቶች፣ ከአካባቢው ነዋሪዎች፣ ከእርሻ ልማቱ ሠራተኞችና በደል ደርሶብናል ከሚሉ ኢንቨስተሮች ጋር ቃለ መጠይቅ አድርገን፣ የተለያዩ የጽሁፍ ማስረጃዎችን አሰባስበን ካጠናቀቅን በኋላ ዘገባውን ሚዛናዊ ለማድረግ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን የመንግስት አካላት ማነጋገር ነበረብን፡፡ በዚህም መሰረት ለክልሉ ኮሚኒኬሽን ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ኡመድ ኡቶዎ ስልክ ደወልን፡፡ የመጣንበትን ጉዳይ ነግረናቸው፣ የወረዳውን የስራ ኃላፊዎች ለማግኘት የምንችልበትን ሁኔታ እንዲያመቻችሉንና ወደ ሥፍራው የምንጓዝበት  መኪና እንዲመድቡልን  ጥያቄ አቀረብን፡፡
ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ የኮሚኒኬሽን ቢሮ የሚዲያ ባለሙያ የሆነ አንድ ሰው ወዳለንበት ሆቴል በመምጣት መኪናው ሊገኝልን አለመቻሉን ነገረን፡፡ ወደ ኃላፊው መልሰን ስልክ ደወልን፡፡ ከቅሬታ አቅራቢዎቹ መካከል አንዱ፣ መኪናውን ለማድረስ ብቻ እንድንጠቀምበት መፍቀዱንና በዚህ መሄድ እንችል እንደሆነ ጠየቅናቸው፡፡ “ምንም ችግር የለውም፡፡ ስትመለሱ መስተዳድሩ ይመልሳችኋል” የሚል ምላሽ ሰጡን፡፡ በመኪናው ተሳፍረን ወደ ስፍራው አቀናን፡፡ እቦታው ደርሰን ከመኪናው ከወረድን በኋላ ቆመን እንድንጠብቅ ተነገረን፡፡ አካባቢው በክልሉ ልዩ ሃይሎችና በወጣቶች መሞላቱ ፍርሃት ፈጥሮብን ነበር፡፡ ከደቂቃዎች ቆይታ በኋላ ግን ወደ ወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ኡክሪ ኡመድ ቢሮ እንድንገባ ተፈቀደልን፡፡
የድምጽና የምስል መቅረጫችንን ከመክፈታችን በፊት የመጣንበት አላማ ምን እንደሆነ ተጠየቅን። ዓላማችን ወረዳው በተለያዩ የልማት ስራዎች ላይ እያከናወነ የሚገኘውን ስራ ለማየትና ከኢንቨስትመንት ስራዎች ጋር በተያያዙ ቅሬታ ያቀረቡ ባለሃብቶች በመኖራቸው፣ ለቅሬታቸው ምላሽ መስጠት የሚችለውን አካል አነጋግረን ሚዛናዊ ዘገባ ለመስራት እንደሆነ አስረዳን፡፡ ያገኘነው ምላሽ ግን ያልጠበቅነው ነበር፡፡  
“ስለ ኢንቨስትመንት ጉዳይ ምንም ማንሳት አትችሉም፡፡ ይህንን ጥያቄም ለመመለስ ፍቃደኞች አይደለንም፡፡ እናንተ እነማን ናችሁ ይህንን ለመጠየቅ የመጣችሁት? ምንስ ያገባችኋል” ተባልን፡፡ ጋዜጠኞች መሆናችንን የሚያረጋግጥ መታወቂያችንን አሳየን። ሁኔታው መልኩን ቀይሮ መካረር ሲበዛ “በቃ ኢንቨስትመንቱ ይቅርና በሌሎች ጉዳይ ላይ እናውራ” ብለን ለማግባባት ሞከርን፡፡ ሙከራችን ተሣክቶልንም ስለ ወረዳው የመንገድ ስራ፣ ስለ ጤና ጉዳይና የወረዳው ስጋት ስለሆነው ሙርሌ ከወረዳው አስተዳዳሪ ጋር አወጋን፡፡ በመሃል በመሃሉ የኢንቨስተሮቹን ቅሬታ እያነሳሳን ምላሽ ለማግኘት ሙከራ አደረግን፡፡ የወረዳው አስተዳዳሪ ሲቆጡ እያበረድን፣ አልመልስም ያሉትን እያለፍን ቃለ መጠይቃችንን አጠናቀን ለመውጣት እቃዎቻችንን መሸካከፍ ጀመርን፡፡
ወዲያው  በርካታ ወጣቶች፣ የወረዳው የፀጥታ ክፍል ኃላፊ ነኝ ያለ አንድ ሰውና የወጣቶች ተወካይ ነው የተባለ ሌላ ወጣት፤ ባለንበት እንድንቆይ አስጠነቀቁን፡፡ ሁኔታው እጅግ አስደንጋጭ ነበር። “ምን አጠፋን?” አልናቸው፡፡ የወረዳው አስተዳዳሪ ወደ ውጪ በመውጣት የልዩ ሃይል ዩኒፎርም የለበሱና መሳሪያ የታጠቁ ወታደሮችን ይዘው በመምጣት “ወደ ፖሊስ ጣቢያ ውሰዱና እሰሩልኝ፤ የቀረፁትን ሁሉ አስጠፏቸው” ሲሉ ትዕዛዝ ሰጡ፡፡ የፀጥታ ክፍል ኃላፊ ነኝ ያለው ሰው ከመካከላችን ሁለቱን ጋዜጠኞች በጥፊና በቦክስ እያዳፋ፣ “የቀረፃችሁትን ሁሉ አምጡ” ሲል አምባረቀብን፡፡ ሁላችንም በእጃችን ላይ ያለውን ስልክና ካሜራ ሰጠነው፡፡ ላፕቶፕ አስመጥተው ፋይሎቻችን በሙሉ ከየስልኮቻችንና ከሜሞሪ ካርዶቻችን ላይ እንዲጠፋ አስደረጉን፡፡ እየፈፀሙ ያሉት ህገ ወጥ ተግባር መሆኑን፣ ህገ መንግስቱ ያጐናፀፈንን ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ፣ መረጃዎችን የማግኘትና በነፃነት የመዘገብ መብታችንን እየጣሱ መሆናችንን ደጋግመን ነገርናቸው፡፡ ሰሚ ግን አላገኘንም፡፡ የከፋ ችግርና ጉዳት ሊያጋጥመን እንደሚችል ገልጸውልን፣ “ዝም ብላችሁ ተቀመጡ” ተብለን በር ተዘግቶብን ታገትን፡፡
ከመካከላችን የቡድኑ አስተባባሪ ነህ ያሉትንና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ተፈጽሞብናል ከሚሉ ቅሬታ አቅራቢዎች የተሰጡንን በርካታ የጽሑፍ ማስረጃዎች በወቅቱ በእጁ ይዞ የተገኘውን አንድ ጋዜጠኛ እየደበደቡ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ወሰዱት፡፡ ሁኔታው እጅግ አስፈሪ ነበር፡፡ የወረዳው የስራ ኃላፊዎች እኛን ጨርሶ ሊሰሙን አልፈለጉም፡፡ “ይህ ሁሉ ማስረጃ እንዴት እጃችሁ ገባ? ከየትስ አመጣችሁት?” ሲሉ ጠየቁን፡፡ “በሉ የሚደርስላችሁን እናያለን” ሲሉም አስፈራሩን፡፡ ለሰዓታት በዚሁ ሁኔታ ቆየን፡፡ ቀጣዩ እጣ ፈንታችን ምን እንደሆነ ግራ ተጋብተን እየጠበቅን ሣለ፣ የወረዳው አስተዳዳሪ ተመልሰው በመምጣት፣ “ታስረናል ብላችሁ አዲስ አበባ አሣውቃችኋል፤ ለምን ተናገራችሁ?” ብለው አፈጠጡብን፡፡ ስልክ መደወል በማንችልበት ሁኔታ ውስጥ መሆናችንን አስረዳናቸው፡፡ ከመሃላችን ግን ስለ ሁኔታው በጽሑፍ መልዕክት ያሳወቁ ጋዜጠኞች ነበሩ፡፡ ከሰዓታት እገታ በኋላ የሰራነውን ቃለ ምልልስ በተመለከተ ምንም አይነት መረጃ በእጃችን ላይ አስቀርተን ብንገኝ ወይም ደግሞ ስለ ጉዳዩ አንዳች አይነት ዘገባ ብንሰራ  እጅግ የከፋ አደጋ እንደሚደርስብን አስጠነቀቁን፡፡ ስለ መታሰራችን፣ መደብደባችንና መንገላታታችን ምንም መረጃ ለማንም እንዳንሰጥ  ማስጠንቀቂያ ከሰጡን በኋላ  ለቀቁን፡፡ ከመሃላችን ተነጥሎ ወደ ፖሊስ ጣቢያ የተወሰደው ጋዜጠኛ ባልደረባችንን ጥለን መሄድ እንደማንችል ስንነግራቸው፤ “እናንተ ሂዱ፤ እሱን እኛ እንለቀዋለን” አሉን፡፡ እነሱ ያሉትን አምኖ ጋዜጠኛውን  ለብቻው ትቶ መሄዱ አስቸጋሪ ስለነበር ተመካከርንና ለልመናውም ከወንዶች ይልቅ ሴቷ ትሻላለች በሚል ሃሳብ፣ እኔ እንድቀር ተወሰነ፡፡ ፖሊስ ወደ ጣቢያው ይዞኝ ሄደ፡፡ እጅግ አታካች ከሆነ ልመና በኋላም፣ ታስሮ የነበረው ጋዜጠኛ ተለቀቀና  ሂዱ ተባልን፡፡
ከከተማው 42 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ምንም አይነት ተሽከርካሪ በሌለበት ገደላማና ፒስታ መንገድ ላይ ምሽቱ ሲቃረብ ሂዱ ተብለን መለቀቃችን ቢያስደነግጠንም፣ ከእነሱ እጅ መውጣታችን እፎይታ ሰጥቶን ነበር፡፡ ከሰዓታት የእግር ጉዞ በኋላ የመንገዶች ባለስልጣን ንብረት የሆነ አንድ ፒክአፕ መኪና ሊፍት ለምነን፣ ሊተባበሩን ፈቃደኛ በሆኑ ሰዎች እርዳታ ጋምቤላ ከተማ አመሻሹ ላይ ገባን፡፡ ሁኔታው እጅግ አስፈሪ ነበር፡፡ ጋዜጠኞች ባረፍንበት ሆቴል ተሰባስበን የማግስቱ ምሽት ጉዞአችንን ወደ ጠዋት በማስቀየር ማለዳ ላይ ከከተማው መውጣት እንዳለብን ወሰንና፣በማግስቱ ማለዳ ላይ አየር መንገድ ሄደን፣ የምሽት ጉዞአችንን ወደ ጠዋት ቀይረን አዲስ አበባ ገባን፡፡
አዲስ አበባ ከገባን በኋላ የነጠቁንን የካሜራ ባትሪ ቻርጀሮችና ልዩ ልዩ ንብረቶች እንዲመልሱልን በስልክ ስንጠይቃቸው፤ “ገና ምን አይታችሁ፣ እናንተንም መልቀቃችን ይፀፅተናል” የሚል ምላሽ ሰጡን፡፡ ይህ በወረዳው አስተዳደርና በፀጥታ ክፍል ሃላፊው  እንዲሁም በሌሎች የሥራ ኃላፊዎች የተፈፀመብን ህገ ወጥ ድርጊት፤ የጋምቤላ ክልል ሃላፊዎችን ማን አለብኝነትና  ከህግ በላይ መሆን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው፡፡ ለመሆኑ እንዲህ ዓይነት ህገ ወጥ ድርጊት በክልል ሃላፊዎች ሲፈጸም ለማን ነው አቤት የሚባለው? ጋዜጠኞችን እያስፈራሩና አየደበደቡ መረጃ እንዳይወጣ የሚያፍኑትስ እስከ መቼ ይሆን? አዲሱ የጋምቤላ አመራር ብዙ ሥራ ይጠብቀዋል። አስተዳደሩ ለውጡን በፍጥነት ወደ ታች ማውረድ ይኖርበታል፡፡  

Read 1055 times