Saturday, 13 October 2018 11:54

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር --- ይሰሙኛል?

Written by  አያሌው አሰረስ
Rate this item
(4 votes)

አበው፤ ‹‹ውኃ የጥቅምት ማን ቢጠጣሽ፣ ምክር የድሃ ማን ቢሰማሽ›› ይላሉ፡፡ ነገሬን ከተራ ሰው የመጣ ነው ብለው እንደማይንቁብኝ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
ትምህርት ሚኒስቴር ሕዝብ ግንኙነት ክፍል ውስጥ የሚሠሩ ጓደኞች ነበሩኝ፡፡ ሚኒስትሩ፤ ጋዜጦች  በምን ጉዳዮች ላይ እንደሚጽፉ አንብበው መረጃ እንዲሰጧቸው መድበዋቸው ነበር፡፡ በትምህርትም ሆነ በሌሎች አገራዊ ጉዳዮች ላይ በ”ነጋድራስ” ጋዜጣ ላይ ከረር ያለ ነገር ስናነሳ፣ ነግረዋቸው ይሆን ነው ብዬ   እጠይቃቸው ነበር፡፡ ጠንከር ጠንከር ያሉ ሃሳቦች የያዙ እትሞቻችን ለሚኒስትሩ የሚገለጽላቸው፤  “የዛሬው እንኳ አይረባም” እየተባለ እንደነበር ነግረውኛል። ወዳጆቼ ይህን የሚያደርጉት የእንጀራ ገመዳቸው እንዳይበጠስ ስለሚሰጉ ነው፡፡ እርስዎ የንባብ ችግር እንደሌለብዎ፣ አስቀድሞ የመፈረጅ ልምድም እንደልተጫንዎ አምናለሁ፡፡ በተመቸዎትና በቻሉት ጊዜ ሁሉ መረጃ ከምንጩ የማግኘቱን ነገር አደራ። የተሳሳተ መረጃ ከተሳሳተ ውሳኔ ላይ ሊያደርስ እንደሚችል አሳምረው ያውቁታልና፡፡
አሁን በሥራ ላይ ባለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና ፈቃድ አዋጅ፤ የክልል ፓርቲ ለማቋቋም 750፣ ለአገር አቀፍ ፓርቲ ደግሞ 1500 ሰዎች በፈራሚነት (በመሥራች አባልነት) መያዝ ያስፈልጋል። ይህ ነው ፋይዳው የማይባልለት የፖለቲካ ፓርቲዎች ድርድር፣ ይህ ቁጥር በእጥፍ እንዲያድግም ሃሳብ መቅረቡን አስታወሳለሁ፡፡ ቁጥሩ ወደ ላይም ወጣ ባለበትም ቀረ፣ ስም እያንጠለጠሉ፣ ፓርቲ መመሥረት ችግር አይደለም፡፡ እያንዳንዱ ሰውም መደራጀት ሕገ መንግሥታዊ መብቱ በመሆኑ፣ ይህን ማድረጉ የተወገዘ  አይደለም ፤ግን በጽድቅ ስም የሚመጣውን ጥፋት መከልከልና መከላከል ይገባል፡፡
ከውጭ የገቡትና በመመዝገብ ፈቃድ ለማግኘት ጉድ ጉድ እያሉ ያሉትን ሳንጨምር፣ አሁን ስልሳ ሁለት የክልልና የአገር አቀፍ ፓርቲዎች አሉ፡፡ ሀ ብለው እራሳቸውን የመሠረቱ ጥቂቶች ናቸው። እጅግ የሚበዙት ከየፓርቲው በወጡ ሰዎች የተመሠረቱ ናቸው፡፡
አራተኛና አምስተኛ ትውልድ ላይ ያሉ ስብርባሪ ፓርቲዎች እንዳሉም የታወቀ ነው፡፡ መብዛታቸው እጅግ በሚያማርር ደረጃ መድረሱን እርስዎም ያወቁታል፡፡ እነሱም ቢሆኑ ይህንን አይክዱም፤ ግን አንዳቸውም ከአንዳቸው ጋር ለመተባበር፣ ለመደመርና ጠንካራ ኃይል ሆኖ ለመውጣት ቁርጠኝነት አይታይባቸውም። በየመንደራቸው አውራ ዶሮ ሆነው፣ አኩኩሉ እንዳሉ አሉ፡፡ ከስማቸው ጎን የሚፃፈው የፓርቲ ሊቀ መንበርታቸው፣ ፀሐፊነታቸው፣ ወዘተ-- በራሳቸው ፈቃድ እንዲጠፋ ጨርሶ አይፈልጉም፡፡
በአገር አቀፍ ሆነ በክልል የተደራጁ ፓርቲዎች እርስ በአርስ ተሰባሰበው፣ ተወያይተውና ተደራድረው፣ ቁጥራቸውን ቀንሰው፣ አንድ ወይም ሁለት ሆነው እንዲመጡ፣ እርስዎ የሰጡትን ማሳሰቢያ አስታውሳለሁ፤ ግን ከሁለት ወር በላይ ጊዜ ያለፈ ቢሆንም፣ የታየ ምልክት ወይም ፍንጭ የለም፡፡ እንዲያውም የሚሰማው ያው የተለመደው መበታተን ነው፡፡
ክቡር ሚኒስትር እንደሚያወቁት፤ አጼ ኃይለ ሥላሴ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን ያቋቋሙት በፍቅርና በጉልበት ነው፡፡ በነበራቸው ተሰሚነት መሽራች ጉባኤው አዲስ አበባ እንደካሄድ አደረጉ፡፡ መሪዎቹ መጓተት ሲያበዙ፤ ‹‹ይህን ቻርተር ሳንፈርም ከዚህ አዳራሽ አንወጣም›› ብለው አንቀው ያዟቸው፤ ሁሉም ቀጥ ብሎ ፈረመ፡፡ እርስዎም የተቃዋሚ ፓርቲዎችን ሰብስበው፣ በክልል ደረጃም ሆነ በሀገር አቀፍ ደረጃ የፓርቲ ብዛት ቁጥር እንዲገደብ ያድርጉ። ፈቅደውና ወደው ቁጥራቸውን መወሰን ካልፈለጉ መንግሥት በእጁ ላይ ባለው ካርድ መጫወት አለበት፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሃይማኖትን መሠረት አድርገው መመሥረት አይችሉም ብሎ እንደከለከለው ሁሉ፣ እዚህም ላይ  እጅግ ፈጥኖ ቁጥሩን መወሰን አለበት፡፡
መንግሥት ባለው የሕግ ሥልጣን፣ ይህን ችግር ፈጥኖ እንዲወገድ ካላደረገ የሚከተለው፣ በመጯጯህ 2012 አገር አቀፍ የምርጫ ጊዜ ማራዘም ወይም እንተለመደው ድምጽ በማባከን፣ የአሕአዴግን አውራ ፓርቲነት ማግነን ነው፡፡ ሕዝብ የከፈለው መስዋዕትነት ለዚህ አይደለምና በጥብቅ ሊታሰብበት ግድ ይላል፡፡
የ1997 አገር አቀፍ ምርጫ የአሕአዴግን አእምሮ ክፋኛ ያናጋ መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ በምርጫው ማግስት የወጡ ሕጎች አጠቃላይ ባሕሪ፤ የሕዝብን ነፃነት መግፈፍ፣ ሕዝብ የአኔ የሚለው ነገር እንዳይኖረው መንጠቅ ነው፡፡ ለምሳሌ አርማ የሌለውን አረንጓዴ ቢጫ ቀዩን ሰንደቅ አላማ  ሕገ ወጥ ያደረገው አዋጅ ቁጥር 654/2001 የወጣው በዚህ ጊዜ፣ ለዚሁ አላማና ግብ ነው፡፡ ከእሱ በፊት የወጡት አዋጆች፣ ሕገ መንግሥቱን ያከበሩ እንደነበሩም ይታወቃል፡፡
በልዩ ልዩ መንገድ ዲሞክራሲያዊ መብቶችን  የሚገድቡ፣ ሰፋ ባለ አገላለጽ  ሕገ መንግሥታዊ መብቶችን ከጀርባ ገብተው የሚገፉ ሕጎችን ለማረምና ለመሰረዝ የሚሠራ፣ የፍትሕና ሕግ ማሻሻያ ምክር ቤት እንደ ተቋቋመ አውቃለሁ፡፡ በፀረ ሽብር  ሕጉ ላይ ያቀረበውን የማሻሻያ ሀሳብም ከመገናኛ ብዙሃን ተከታትያለሁ፡፡  መንግሥትዎ በአንድ ነገር ቢያምን ደስ ይለኛል ፤ጓያ ነቃይ ገበሬ ‹‹የፊት የፊቱን አለ›› ይባላል። አዋጆቹ በማያዳግም ሁኔታ ተጣርተው ይታወጃሉ ብሎ ማሰቡ መልካም አይደለም፡፡ ነገም እንደሚሻሻሉ አምኖ፣ ጉልተው የሚታዩትን ችግሮች እያረሙ እንዲወጡ ቢደረግ፣ ለእርስዎም ፈጥኖ ለመራመድ፣ ወደ ሥራዎም  ለመግባት ይጠቅምዎታል፡፡  
የኢትዮጵያንና የኤርትራን  ችግር በመፍታትና ከጎረቤት አገሮች ጋር ያለውን ግንኙነት የበለጠ በማቃናት፣ በሌሎች አገሮች ታስረው የነበሩ ወገኖቻችንን በማስፈታት ለወሰዷቸው አርምጃዎች ከፍ ያለ አድናቆት አለኝ፡፡ ውጭ ውጭውን ሲከታተሉ፣ የሀገር ውስጡን ፖለቲካ ቸል እንዳሉት የምናገረውም ጠበቅ አድርጌ ነው፡፡
አሁን የአሕአዴግ ጠቅላላ ጉባኤ ተካሂዶ እርስዎም በከፍተኛ ድምጽ ተመርጠዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትርነትም ቀጥሏል፡፡ ሥልጣንዎም እየተደላደለ ነው፡፡ ይሁን እንጂ የተቀመጡበትን ወንበር ድንገት የሚንጥ ችግር አልፎ አልፎ ብቅ እያለ እንደሆነ አይካድም፡፡
በአንድ በኩል እርስዎና ተከታዮችዎ፤ የዘረኝነትን ጎጂነት እያስገነዘቡ ቢሆንም፣ በሌላ በኩል ደግሞ ዘረኝነትን ጋሻና መከታ ያደረጉ፣ እጃቸውን በሌላው ዘር ላይ እያነሱ ሰላም እየደፈረሰ ነው። አዝመራ በሚሰበሰብበት ጊዜ እየተፈናቀለ ያለው አርሶ አደር፤ከሁሉም በላይ መንግሥትን ሊያሳስበው ይገባል፡፡ አንድ ክረምት የነቀለውን አስር ከረምት አይተክለውምና፣ እባከዎ አንድ  ይበሉ፡፡
ከውጭም የመጡትም ሆነ አገር ውስጥ ያሉት ፓርቲዎች፤ “መንግሥት ለውጥ አለ ይለናል፣ በለውጡ ግን ምን ሚና እንዳለን አያሳየንም፤እንደተለመደው እሱ መሪ፣ እኛ አጃቢ ተደርገናል” እያሉ ነው፡፡ ይህ ቅሬታ ወደ ሕዝብ እንዳይወርድም መላ ይበሉ፡፡
የኦነግ ሊቀ መንበር፤”እኛ ከመንግሥት ጋር ትጥቅ ለመፍታት አልተስማማንም” ብለው መግለጫ ከሰጡ ወዲህ፣ መንግሥትዎ ያደረጋቸውን ውሎች ይግለጥልን የሚል ጥያቄ እየተነሳ ነው፡፡ ጥያቄው ተገቢ ነው፡፡ ሕዝብ በፍቅርና በአክብሮት ለሰጠዎ እምነት የመሸርሸር ምልክት እንዳይሆን እሰጋለሁ፡፡
ክቡር ሚኒስትር፤ የእኔንም የሌላውንም እምነትና ተስፋ እንዲጠብቁልን አደራ እላለሁ፡፡
አመሰግናለሁ!!

Read 1671 times