Saturday, 01 September 2018 15:38

ጊዜውን ያልጠበቀ “የማስጠንቀቂያ ደወል”

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

  (ሁለተኛ ክፍል)
አርክቴክት ሚካኤል ሽፈራው “የማስጠንቀቂያ ደወል” በሚል ርዕስ ያሳተመውን መጽሐፍ፤ “የዶ/ር ዐቢይ አህመድን ህዝባዊ መሠረት የካደው መጽሐፍ” በሚል ባለፈው ሳምንት የመጀመርያውን ክፍል ሂሳዊ ጽሁፍ አቅርቤ ነበር፡፡ ሁለተኛውን ክፍል እነሆ፡
አቶ ሚካኤል ይግባቸው አይግባቸውም የኢሕዴን የቀድሞ መዝረክረክ ምንጩ፣በፓርቲው ውስጥ ያሉት ሰዎች የተወከሉበትን ብሔር ሕይወት ለመለወጥ ያልተዘጋጁና ፓርቲውም በአክሲዮን የተያዘ እንጂ ነፃ ያለመሆኑ ነው፡፡ ከጅምሩ ኢትዮጵያዊ ሆኖ መታገሉን ያልወደዱት የሕወሓት አመራሮች የበታተኑትም ለራሳቸው ጥቅምና አጀንዳ፣በስሙ የሚነግዱበት የብሔር ቡድን ለመፍጠር ተመኝተው መሆኑን የቀድሞው የኢሕዴን መሥራችና አመራር አቶ ያሬድ ጥበቡ፤ “ወጥቼ አልወጣሁም” በሚለው አዲስ መጽሐፋቸው ላይ ይገልጻሉ፡፡
ኢሕአዴጋዊ ፍቅር የተጠናወተው፣ ይልቁንም ሕወሐታዊ አድናቆት የያዘው የሚካኤል መጽሐፍ እንደሚለው፤ ብሔር-ተኮር ስራ ይሰራ ዘንድ እንዳይችል ያደረገው ጨቋኝ ለተባለው አማራ መጨቆኛ ይሆናሉ ያላቸውን የራሱን ሰዎች መሰግሰጉ እንደሆነ ማንም አያጣውም፡፡ ሌላው ቀርቶ በየትኛውም ክልል ባልታየ ሁኔታ የክልሉ ቢሮ ኃላፊዎች ሳይቀር ከዕድለኛው ቡድን መጥተው ሲሾሙበት ለምን ነፃ አይሆንም? ብሎ የጠየቀ የለም፡፡ ለመሆኑ ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት የነበረው የአማራ ፓርቲ ሰዎች፣ ምን ያህሎቹ የክልሉ ተወላጆች ነበሩ?
ምንም እንኳ የብሔር ፖለቲካ መዘዙ ሺህ ቢሆንም በዚሁ ቅኝት በተቃኘ አስተዳደር ውስጥ ሆኖ በማይመለከተው ሰው መተዳደር የሚያመጣውን ጣጣ አይተናል፡፡ ወጣቱ በስራ አጥነት መንገላታቱ ሳያንስ በእስራት ሲሰቃይና በጥይት ሲደበደብ፤እወክለዋለሁ የሚለው ድርጅት ጥይት አቀባይ እንዲሆን ያደረገው፣ ህዝቡን ልክ ለማስገባት የተመደበው ፓርቲ ነው፡፡
የአቶ ሚካኤል መጽሐፍ በርካታ ርዕሰ ጉዳዮችን ቢያነሳም በጣም ጥቂት በሆኑ ገፆች ሊነካ የፈለገው አዲሱን የለውጥ መንገድ ነው፡፡ ይህ የለውጥ መንገድ ብዙዎቻችን ከአሰቃቂ ግፍ፣ አድልዎ ከበዛበት አስተዳደር፣ ዐይን ካወጣ ዘረፋ፣ ከእስራትና ከግድያ የታደገን ቢሆንም ደራሲው ሚካኤል የታየው ግን ስጋቱና አደጋው ነው፡፡ ወደ ሚካኤል ጎርባቾቭ የወሰደውም ያ ነው፡፡  
“የማስጠንቀቂያ ደወል” በሚለው መጽሐፉ፤ሚካኤል ጎርባቾቭ ሶቪየት ህብረትን እንደበታተኑ ዶክተር ዐቢይም አገራቸውን ሊበታትኑ ይችላሉ የሚል ስጋቱን አጋርቶናል፡፡ ለመሆኑ ዶክተር ዐቢይ ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት ከተሰሩት በደልና ግፎች የባሰ ምን ሰርቶ ነው አደጋ ያመጣብን? ይልቅስ ሰው በየአደባባዩ ሲታረድ፣ በእስር ቤት ሲታጎርና ጥፍሩ ሲነቀል፣ ሲኮላሽ-- ያልተፈጠረው ስጋት አሁን እንዴት ሊመጣ ቻለ? ..መንግሥት እንደ ተራ ወንበዴ ሕዝብን ከሕዝብ፣ ብሔርን ከብሔር ለማጋጨት ሀውልት ሲሰራ፣ ሸንጎ እየጠራ ፀብ ሲቀሰቅስ---ያልነበረው ስጋት፣ ዶክተር ዐቢይ መጥቶ “እንታረቅ፣ ይቅር እንባባል፣ እንደመር” ሲል እንዴት ሊፈጠር ቻለ?
ዶክተር ዐቢይ ባይመጣስ በሀገሪቱ ይፈጠር የነበረው ሁኔታ የዛሬውን ዐይነት ህዝብን የሚያረጋጋና ደስ የሚያሰኝ ይሆን ነበር? ቀጣዩን ሁኔታ የሁላችንም ልብ ያውቀዋል፡፡ ምናልባትም ቢበዛ ከአንድ ሳምንት በኋላ ሀገሪቱ መያዣ መጨበጫ ወደሌለው ችግር ውስጥ ትገባ ነበር፡፡
ይህ ማለት ግን “የኛ ጥቅም ከሚነካ አገሪቱ ትበታተን!” የሚሉ ወገኖች የሉም ማለት አይደለም። የኔ ሙግት ሚካኤልን የሚያህል ትልቅ ሰው፣ ብዙ የሚያውቅና የጥበብ ልብ ያለው ሰው፣ ለምን ያንን የደምና የእንባ ዘመን ከስጋት ሳይቆጥር ቀረ? የሚል ነው፡፡
ሚካኤል በክልል ከተሞች በተለይም የአማራውንና አማርኛ ተናጋሪውን ባይተዋርነት በሚመለከት በስፋት ጽፏል፡፡ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ዕድል የሚለውን የኢሕአዴግ ሀሳብ ይዞ በ1999 ዓ.ም ከተደረገው የህዝብ ቆጠራ ስታቲስቲክስ በመነሳት፣ የተሻለ መንገድ ያሳየበት ነው ማለት ይቻላል፡፡ ለመነሻ የሀገራችን ከተሞች አመሰራረትን በሚመለከት ሚካኤል እንዲህ ይለናል፡-
“የአገራችን ከተሞች አንዳንዶቹ ቀደም ሲል የገበያ ስፍራዎችና የነባሮቹ ገዢዎችና የጎሳ መሪዎች መቀመጫዎች የነበሩ ቢሆንም ባመዛኙ ግን ኢትዮጵያን አንድ አድርገው ለመግዛት በተነሱት አጼ ምኒልክ አዳዲስ የተካተቱ ግዛቶችን በአንድነቱ ውስጥ አዲስ በተካተተው ህዝብ መካከል ሆነው ግዛት እንዲያስጠብቁ በተላኩ የገዢው መደብ የጦር መሪዎች፣ በአሽከሮቻቸውና በወታደሮቻቸው የተመሰረቱ የጦር ሰፈሮች ነበሩ፡፡ በመጪዎቹ ዘመናት ደግሞ ከጦር ሰፈርነታቸው ከፍ ብለው በተጨማሪ ያስተዳደርና የገበያ ማዕከሎች ሆኑ፡፡”
ጸሐፊው ስለ ሀገራችን ከተሞች የሕዝብ ስብጥርና ምስረታ ያነሳው ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ይልቅስ በአንዳንድ የክልል ከተሞች የሚኖሩና የክልሉን “ለባለ ክልሉ” በሚል ብሔርተኛ የፖለቲካ ቅኝት መጤዎቹን ያገለለ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ስልጣን በመንሰራፋቱ ላይ የራሱን ሀሳብ ለመስጠት ነው፡፡
በቅኝቱ የሐረሪን፣ የኦሮሚያን፣ የቤኒሻንጉልን፣ የአፋርን ክልሎች ማሳያ በማድረግ በከተሞች ውስጥ የሚኖሩት አማርኛ ተናጋሪዎች በቁጥር የበዙ ሆነው ሳለ፣ በአስተዳደር ውስጥ ድምፃቸውን የሚያሰሙላቸው ወኪሎች የሏቸውም፡፡ በዚህም ምክንያት እነዚህ ከክልላቸው ውጭ የሚኖሩ፣ ኢትዮጵያውያንን በስልጣን ላይ ባሉ የክልሉ ተወላጆች የሚደርስባቸውን አስተዳደራዊ በደልና ጫና እንዳይኖር እነርሱን ወክሎ፣ መፍትሄ ለማስገኘት ዕድሉ ስለማይኖረው ውሎ አድሮ በፌደራላዊው መንግስት ላይ የሚኖረው እምነትና አመላካከት የተበላሸ ይሆናል ይለናል” መጽሐፉ፡፡
ለዚህም እንደ ማስረጃ ያቀረበው የ1999 ዓ.ም የህዝብ ቆጠራ መሰረት በማድረግ፣ ከ3.4 ሚሊዮን ህዝብ በላይ ከክልላቸው ውጭ መሆኑን ያሳያል-ሚካኤል፡፡ በዚህ ርዕስ ሥር ባስቀመጠው አጠቃላይ ድምዳሜ፤ ኢሕአዴግን፣ ይልቁንም ብአዴንን ይወቅሳል፡፡ በሌላ በኩል በ1997 ዓ.ም ፓርቲው በከተሞች የመሸነፉ ምክንያት የነዚህ በሚሊየን የሚቆጠሩ ህዝቦች ከስርአቱ መንሸራተትና ማኩረፍ ነው ብሎ ያምናል፡፡ በዚያም አለ በዚህ፣ በከተሞ አካባቢ ተወላጅ ያልሆኑ ነዋሪዎችን ችግር መዝኖ መፍትሄ ይሰጣቸው ዘንድ መጠየቁን በበጎነት አሰምርበታለሁ፡፡
ለችግሩ እንደ መፍትሄ ያስቀመጣቸው ነገሮችም በጎ ናቸው፡፡
1ኛ. ዛሬ ያለበት ምዕራፍ ያለፉትን ዘመናት ጉዞዎች በአዲስ የእይታ መነጽር መርምሮ፣ የሚመራውን የአማራ ህዝብ፣ በተለይም ከክልሉ ውጭ ባሉ ከተሞች ተሰራጭቶ የሚኖረውን የአማራ ህዝብ ፖለቲካዊ መብቶች አስከብሮ ከሌሎች ህዝቦች ጋር ያለውን መልካምና ዴሞክራሲያዊ ግንኙነት ባስተማማኝ መሰረት ላይ የሚያቆምበት፤
ሁለተኛውና ሶስተኛው ነጥብም ከክልል ውጭ የሚኖረው ህዝብ ዋስትና የሚሰጥ የህግ ማዕቀፍ እንዲኖረው፣ በሚኖርበት ቦታ ላፈራውና ለሚያፈራው ሀብትና ንብረት ዋስትና እንደሚያገኝ፤ በሌላም በኩል ታሪካዊ፣ ባህላዊና ሃይማኖታዊ ማንነቱን አውቆ፣ የሚኖረውን የአማራ ህዝብ ፖለቲካዊ መብቶች አስከብሮ ከሌሎች ህዝቦች ጋር ያለውን መልካምና ዴሞክራሲያዊ ግንኙነት ባስተማማኝ መሰረት ላይ የሚያቆምበት፣
ሁለተኛውና ሦስተኛው ነጥብም ከክልሉ ውጭ የሚኖረው ህዝብ ዋስትና የሚሰጥ የህግ ማዕቀፍ እንዲኖረውና፣ በሚኖርበት ቦታ ላፈራውና ለሚያፈራው ሀብትና ንብረት ዋስትና እንዲያገኝ፤ በሌላም በኩል ታሪካዊ፣ ባህላዊና ሃይማኖታዊ ማንነቱን አውቆ፣ በጥንታዊና ነባሩ ማንነት ላይ ዲሞክራሲያዊና ብሔራዊ ማንነቱን ሳያምታታ፣ ድርጅቱን “የራሴ ነው” በሚል ተቀብሎ፣ ድርጅቱን እንደተጠሪው የሚቆጥር ሕዝብ መፍጠር አለበት ብሎ ያምናል፡፡ ይህ የሚካኤል ጥሩ አካሄድና ለወገን ተቆርቋሪነት ነው፡፡
ይሁንና ብዙ ነገሮቹን ስንመረምር፣ በሦስተኛው ዓለም፣ በተለይ በአፍሪካ መሪዎች አካሄድ ያየው አይመስልም፡፡ በተለይም ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት የተሸረቡትን የፖለቲካ መንግሥታዊ ሴራዎች የሚያውቃቸው አይመስልም፡፡
ለመሆኑ ብአዴን የአማራውን ህዝብ ይወክል ነበር ወይ? ተብሎ ቢጠየቅ “አዎን!” የሚልበት ምልክቶች ይታያሉ፡፡ ምናልባትም ወቀሳው ከዚሁ ባይተዋርነት የመነጨ ነው፡፡ እውነት ለመናገር ያ በእባብ፣ በእንቁራሪትና በጊንጥ ሊመሰል የሚችለው የፖለቲካ ባህር በውስጡ ከጥቂት ዓሳዎች በስተቀር በጨካኞችና በግፈኞች የተሞላ እንደነበር የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ በአንጻራዊነት ሌሎቹ ክልሎች ጥይትና ሳንጃን ሲቀበሉ፣ አብሮ ጥቂት ልማት ይመረቅላቸዋል፡፡ በብአዴን ግዞት ሥር የነበረው ሕዝብ ግን ትምህርት ቤት እንኳ የሚሰራለት አጥቶ ቁልቁል ወደ ኋላ በመሄድ በየዛፉ ስር ፊደል ሲቆጥር መኖሩን ብዙዎቻችን እናውቃለን፡፡
የአቶ ሚካኤል መጽሐፍ ትኩረትና ማስጠንቀቂያ፤ በብአዴን እጅ ለወደቀው ምስኪን የአማራ ህዝብ ሳይሆን፣ የኢህአዴግን የምር ቀውስ ወደ ፈጣሪው በየክልሉ ላለውና በራሱ ሰዎች ባለመወከሉ ቁጣ ጦስ ነገሮች አስጊ እየሆኑ መምጣታቸውም ይመስላል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ የዋለልኝን የብሔር ጥያቄ አስቀምጦ፣ ኢህአዴግ መሬት ላይ ያወረደበትን መንገድ ማሳየቱ፣ እግረመንገዱን በስስ ልምጭ መንካቱ ጥሩ ነው፡፡  
ቢሆንም ክፋት የለውም … ይሁንና ሌላው ያልተመቸንና መዝጊያው ላይ የተነገረን ማስጠንቀቂያ ነው፡፡ ማስጠንቀቂያው በማህበራዊ ሚዲያ እስኪታክተን ያነበብነው ነው፡፡ “ትግራይ ልትገነጠል ትችላለች!” የሚል፡፡
ይህ ቋንቋ በእጅጉ ይዘገንነኛል፡፡ ለመሆኑ ትግራይን የፈጠራት ማነው? … የተፈጠረችውስ መቼ ነው? … ለምንስ የትናንቱ ወያኔ ጠፍጥፎ እንደሰራት ትቆጠራለች? እውነት ለመናገር የትግራይ አባቶች ኢትዮጵያን ከፈጠሯት ሰዎች ተርታ ያሉ አይደሉም እንዴ? .. ለነፃነት በፈሰሰው፣ ለብሔራዊ አንድነት በተከፈለው ዋጋ ቁንጮ ላይ ያሉ ሰዎች ምድር ታሪክ በሚያዛቡ ሰዎች ትነጠላለች ያለውስ ማነው?
እንደኔ ከዚህ ለዘብ ያለ አስተያየትና ቅሬታ ቢነሳ ቅር አይለኝም፡፡ ከዚያ ውጭ ግን መገንጠል ያቃዠውና ከትግራይ ህዝብ ልብ ያልወጣ ጩኸት ሰሚ የለውም። ዮሐንስ የሞተው ሀገር ለመገንጠል አይደለም፣ አሉላ በየጦር ግንባሩ በእሳት የተበላው፣ የጥይት ባሩድ ሲያሸት የመኖሩ ትሩፋት ሕዝብን ለመለየት አይደለም። አንዲት ጠንካራ ሀገር ለመፍጠር ነው፡፡ እንደዛሬዎቹ ሀገር ለመበተን፣ ህዝብ ለመለያየት አይደለም፡፡
ከሚካኤል ሀሳቦች የምጋራው የጋራ ጉዳይ አለኝ። ያም የትግራይ ክልል ተወላጆች የጥቃት ስጋት አለባቸው የሚለነው ነው፡፡ ይህንን በተመለከተ በማህበራዊ ሚዲያ በሌሎች መገናኛ ብዙኃንም ሽንጤን ገትሬ ተሟግቻለሁ፡፡ አሁንም በእጅጉ እታገለዋለሁ፤ እቃወመዋለሁ፡፡ የትግራይ ህዝብ ስጋችን፣ አካላችን ነው፡፡ የአክስት ባል፣ የአጎት ልጅ ወዘተ ሆነናል፡፡ ይህንን ዝምድና ያላገናዘበ ዘረኝነትና ጥላቻ ተቀባይነት የለውም፡፡
ሚካኤል ሺፈራው (ገፅ 269 ላይ)ባሰፈረው ሃሳብ ግን አሁንም ትክክለኛ ያልሆነ ሃሳብ ነው፡፡ እዚህ ላይ አንድን የረጂም ታሪክ ባለቤት የሆነን ህዝብ ትናንት የተፈጠረ ፓርቲ ብቻውን ሊነዳው አይችልም፡፡
አገሪቱን በመምራት ላይ ያለው ኃይል የመገንጠል አማራጭ ሊወስድ የሚችል መሆኑን ሳይረፍድ መረዳት የሚገባ ይመስለኛል” ይላል ሚካኤል፡፡ እኔ ደግሞ ትግራይን ኢትዮጵያዊ አድርጎ የፈጠራት ሕወሓት ስላይደለ የመገንጠል ሀሳቡም ሆነ ስልጣኑ የለውም ባይ ነኝ፡፡ የትግራይ ህዝብ ሀገሩ ትግራይ ብቻ አይደለም፡፡ ሀገራችን የምንለው ሁሉ ሀገሩ ነው። ህዝቡ ለኦጋዴን ሞቷል፣ ለሞያሌ ነፍሱን ሰጥቷል፡፡ በሌሎች ግንባሮችም ዋጋ ከፍሏል፡፡ አሁን ደግሜ ማንሳት ባያስፈልገኝም እንደዛሬ ወያኔ በጎጥ ሳይለየን በፊት ለዚህች ሀገር ዋጋ የከፈሉ የቅርብ ሰዎቼን የአብሮ አደጎቼን ወላጆች ማስታወስ እችላለሁ፡፡
ሳጠቃልል፤ አቶ ሚካኤል የጻፉት መጽሐፍ በተለይ መግቢያና መውጫው ላይ ችኮላ ስለነበረበት፣ የአረፍተ ነገር አጠቃቀም፣ የአንቀፅ አደረጃጀት፣ የቃላት ግድፈት ጎልቶ ይታይበታል፡፡ ሌላው ቀርቶ ገፅ 217 እና 218 ላይ ተመሳሳይ ሀሳብ ማስፈሩን፣ በምስጋናው ገፅ እንኳ ከአምስት በላይ ግድፈቶች መኖሩ፣ ገፅ 192 እና 193 የሚታየው፣ “አይቻለሁ፣ አስተውያለሁ” የሚል የሪፖርት ቋንቋ ያለ ቅጥ መበዛት፣ ጉዳዩን የእነ ቶሎ ቶሎ ቤት አስመስሎታል፡፡
በመጨረሻም ለዶክተር ዐቢይ ብሎ የጻፈውንና ያሰፈረውን ሃሳብ እጋራለሁ! አሁንም ቅር የሚለኝ ግን ያ ሁሉ ግፍ ከሀገሪቱ ሰማይ ስር ሲፈፀም ጥሩ እንቅልፍ አግኝቶ፣ አሁን በለውጡ ጅማሬ “ለማስጠንቀቂያ” መባዘኑ ነው፡፡

Read 2188 times