Monday, 23 July 2018 00:00

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(15 votes)

“ለብቻ ለመኖር ወይ እግዜር አሊያም ሰይጣን መሆን ያስፈልጋል”
              
     በድሮ ቀልድ እንጀምር፡- ሦስት ጓደኛሞች ናቸው። አንደኛው ሃኪም፣ ሌላው  አርኪቴክት፣ አንዱ ደግሞ ፖለቲከኛ ነው፡፡ የሙያ ነገር አንስተው ሁሉም የየራሳቸው ሙያ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ቀዳሚ መሆኑን ለማሳመን ይጥራሉ፡፡  
“እግዜር አርፍ ሃኪም ነበር፣ የመጀመሪያውን ቀዶ ጥገና ያደረገው እሱ ነው፡፡”…አለ ሃኪሙ፡፡
ጓደኞቹም፤ “መቼ?” ብለው ይጠይቁታል፡፡
“ድሮ፣ድሮ … ሰው እንደተፈጠረ” አላቸው፡፡
 ከአዳም ግራ ጎን አንድ አጥንት በኦፕራሲዮን አውጥቶ፣ ሄዋንን መስራቱንም አብራራላቸው፡፡
በዚህም ጊዜ አርኪቴክቱ፤ “እግዜር ሃኪም ከመሆኑ በፊት አርኪቴክት ነበር”…አለ፡፡
አዳምና ሄዋን ከመፈጠራቸው በፊት እግዜር ምድርና ሰማይን በመዘርጋቱ አርኪቴክቸር ቀዳሚ ሙያ ሊሆን እንደሚገባውም ተከራከረ፡፡ ለማስረጃነትም እግዜር ዲዛይን ሲሰራ የሚያሳየውን የታላቁን የዊልያም ብሌክ “GOD” የተሰኘውን… ስዕል ኮፒ አሳያቸው፡፡…
የፖለቲከኛው ተራ ደረሰ፡፡ እሱም እግዜር፤ ሃኪምም አርኪቴክትም ከመሆኑ በፊት ፖለቲከኛ መሆኑን አሳመናቸው፡፡… ምን ብሏቸው ይሆን?
* * *
አሜሪካዊው ፈላስፋ ጆን ዴዊ፤ የትምህርት ፍልስፍና ምን መሆን እንዳለበት፣ የትምህርት ካሪኩለም እንዴት መዘጋጀት እንደሚኖርበት፣ የወጣቶች ባህሪ በተሻለ መንገድ ሊቀረፅ የሚችልበትን ሁነኛ ሃሳቦች በኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና ዴፓርትመንት መሪ በነበረበት ጊዜ ተናግሮ ነበር፡፡ …“ትምህርት ውጤት ካላሳየ፣ በድርጊት ካልተገለፀ ከንቱ ነው” የሚል ፕራግማቲስት አቋም ነበረው፡፡… ‹ትምህርትና ዴሞክራሲ›  በሚለው መጽሐፉ፤ እውነተኛ ትምህርት የሚቀሰመው ከልምድ እንደሆነ አበክሮ ይመክራል፡፡
ትምህርት ቤቶች ለማወቅና ለመረዳት የሚያግዙንን ዲሲፕሊኖች የምንማርባቸው ቦታዎች መሆናቸውን፤ ዕውቀት የሚዳብረውና ፋይዳ የሚኖረው ግን በዓይናችን የምናየውን፣ በጆሮአችን የምንሰማውንና የምናነባቸውን መጽሐፍቶች ከራሳችን ልምድ ጋር እያወራረስን ወደ ጠቃሜታነት የመተርጎም ወይም የመለወጥ አቅም ስናፈራ ነው ይላል፡፡ ዴሞክራሲም ቢሆን ሊያገለግለንና የፈለግነውን የምናደርግበት ነፃነት ሊሆነን የሚችለው በደንብ የማሰብና የማገናዘብ አቅም በግል፣ በጋራም ሆነ በተቋም ደረጃ ሲገነባ ነው ባይ ነው፡፡ ያ…ካልሆነ የሚተርፈን ቅዥትና ውዥንበር  ይሆናል፡፡ (We naturally associate democracy with freedom of action, but freedom of action, without freedom capacity of thought behind is only a cheos) በማለት ይመክራል፡፡
ወዳጄ፡- ወንዝ ገድበህ አቅጣጫውን ልታስቀይር፤ ተራራውን ንደህ ገደል ልታደርግ ትችላለህ፡፡ ጫካው ተቃጥሎ ምድረ በዳ፣ በረዶው ቀልጦ ውሃ ሊሆን ይችላል፡፡ በጦርነት ብዙ ሕዝብ ሊያልቅ፣ በመፈናቀል ብዙ ሰዎች ሊሰደዱ ይችላሉ፡፡ ተፈጥሮ በተለያየ መዓት ትሰለባለች፡፡ የሆነው እንዳልሆነ፣ የነበረው እንዳልነበረ ማድረግ አያቅትም፡፡ ሰው ለዚህ የሚሆን አቅም አለው። …ኢ-ፍትሃዊ በሚሆንበት ጊዜ!!... የተመሳቀለውን እንደነበረ ማድረግ፤ የጠፋውን መመለስ ግን ከባድ ነው። ምናልባትም አይቻልም፡፡ ወይም ረዥም ዓመታት ያስፈልጋሉ፡፡
ወዳጄ፡- የትውልድ ስብራት በጊዜ ወጌሻ ይጠገናል፣ በፍቅር ሃኪም ይታከማል፡፡ ተፈጥሮም ወደ ራሷ መስመር እንድትመለስ የሚጠግናትና የሚያክማት ትፈልጋለች፡፡ እያንዳንዱ ሰው፣ እንሰሳም ሆነ ዕፀዋት ለዓለማችን ደህንነት የሚያዋጡት ነገር አለ፡፡ ካልተጋገዙ መኖር ያስቸግራል፡፡ ለብቻ ለመኖር ወይ እግዜር አሊያም ሰይጣን መሆን ያስፈልጋል (To live alone one must be either a devil or a god) እንደሚለው ፍሬዴሪክ ኒች፡፡ በተፈጥሮ ዑደት ውስጥ እስካለፈ ድረስ ህይወት ሲወለድ ሆነ ሲሞት፣ ሲዘራም ሆነ ሲነቀል ጥቅም አለው፡፡ ጉዳት የሚሆነው በሰው ሰራሽ ችግር ከመስመር  ሲወጣ ወይም ተፈጥሯዊ ዘውጉ ሲሰናከል ነው፡፡
ወዳጄ፡- ታላላቅ ሙዚቃዎች (grand master pieces) የተቀናበሩት በኦርኬስትራው ውስጥ በተካተቱ የተለያዩ የሙዚቃ መሳሪያዎች ነው፡፡ መሳሪያዎቹ በየራሳቸው ድምፅ የተቃኙና የየራሳቸው መገለጫ ቃና ያላቸው ናቸው፡፡ አንድ ላይ ሲጫወቱ ግን ለዛ ያለው፣ ውብና ማራኪ ሙዚቃ ይፈጥራሉ፡፡ እንደዚሁም ዓለማችንና ሌሎች ዓለማት፣ ከዋክብትና ጨረቃዎችም በየራሳቸው ምህዋር የተቃኙ ናቸው፡፡ ነገር ግን ብርሃንና ጨለማ፣ ክረምትና በጋ፣ ህይወትና ሞት የሚኖረው አንድነታቸው በፈጠረው ወዳጅነት (Harmony) ነው፡፡… የህዝቦች ማህበራዊ ጥቅም የሚገኘውም፣ ፍትህ የምትስቀውም እያንዳንዱ ሰው የግል ነፃነቱ ሲጠበቅለት ነው፡፡” …Justice in a society would be like that…HARMONY OF RELATIONSHIPS where by the planets are held together in their orderly or their musical movement” የሚለን ፕሌቶ ሲሆን ፓይታጎረስም ሃሳቡን አጠናክሮ ጽፎታል፡፡
ወዳጄ፡- ስለ ትምህርት ነፃነትና ሃርመኒ የምናወራው የግለሰቦች የማሰብ፣ የማመዛዘንና አርቆ የማየት አቅም ለሳይንስና ለጥበብ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንዳለው ሁሉ፣ በግለሰብዓዊ እርስበርስ ግንኙነትም ሆነ በሃገራት ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነት ላይ ጠቀሜታው ከፍተኛ መሆኑን ለማስታወስ ነው፡፡ …በተለይ ደግሞ በህዝብ አስተዳደር ፖለቲካ ላይ ለተሰማሩ፡፡ ምክንያቱም ማሰብና ያሰቡትን መፈፀም ወይም ሃሳብን በተግባር መተርጎም ለሁሉም ቀላል አይደለም፡፡ ጋናውያን፤ “መሬት በሃሳብ አይታረስም”  ይላሉ፡፡
መልካም ባለስልጣናት ባገኙት አጋጣሚ የራሳቸውንም ሆነ የሌሎችን ጠቃሚ ሃሳቦች በተግባር ላይ ያውላሉ፡፡ አንዳንዶች ደግሞ አጋጣሚውን ለጠብና ለጦርነት ይጠቀሙበታል፡፡ የስልጣን አጋጣሚውን ፍቅርና መቻቻል ብዙ ቦታ እንዲኖረው በማድረግ ለውጥ ካመጡ የክፍለ ዘመኑ መሪዎች ዋነኛው ኔልሰን ማንዴላ ነው፡፡ ዓለማችን በያዝነው ሳምንት “የማንዴላን ቀን” አክብራለች፡፡ በታላቅ የሙዚቃ ኮንሰርት!!... ማንዴላ የፍቅርና የመቻቻል “ሞዴል” መሪ ነበር፡፡ “በፍቅርና በይቅርታ ሁሉም ቀላል ነው” ባይ ነው፡፡ ይህንን በተግባር አሳይቶናል፡፡ ወዳጆቹ ታስሮ በነበረበት ክፍል ውስጥ አንድ ቀን ለማደር ባለ አምስት ኮከብ ሆቴሎች ከሚያስከፍሉት ዋጋ በብዙ ዕጥፍ ይከፍላሉ፡፡ ፍቅር በተግባር ሲገለፅ እንዲያ ነው፡፡ Love in action speaks more እንዲሉ!!
ወዳጄ፡-…ማንዴላን “ማንዴላ” ያደረገው ከላይ ባየነው መንገድ ራሱን በመስራቱ አይመስልህም?
* * *
ወደ ቀልዳችን እንመለስ፡፡ ፖለቲከኛው ወጣት በተራው ጓደኞቹን… አንድ ጥያቄ ልጠይቃችሁ አላቸውና ፈቀዱለት፡፡ …
“አዳምና ሔዋንም ሆኑ ሰማይና ምድር ከመፈጠራቸው በፊት ምን ነበር?”
ጓደኞቹ እርስ በራሳቸው ተያዩ፡፡…. አሰቡ አሰቡናም…
“እሱ አይታወቅም፤ የሆነ ቅዥት ነገር ነው” አሉት፡፡
“ልክ ናችሁ” አለ አጅሬው፤ “…ታዲያ ያን የማይታወቅ ነገር፣ ቅዥት ያላችሁትን ፖለቲከኛ ካልሆነ ማን ሊፈጥረው ይችላል?” ሲል ጠየቃቸው፡፡ መልሳቸው ‹ዝም› ነበር፡፡
መልካም ቀን ይሁንልህ ወዳጄ!!... በነገራችን ላይ ዊልያም ኮሊንስ … “Peace rules the day where reason rules the mind” እያለህ ነው፡፡ ትስማማለህ?
ሠላም!!

Read 5107 times