Sunday, 01 July 2018 00:00

“ፈልተህ ከምትገነፍል፣ እያደር ብሰል!”

Written by 
Rate this item
(6 votes)

 አንድ የቱርኮች ተረት እንዲህ ይላል፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን፤ አንድ ዛፍ ጥላ ሥር ተቀምጠው እናትና ልጅ ይወያያሉ፡፡


ልጅ:- እማዬ?
እናት:- ወዬ
ልጅ:- ስንት አባቶች ናቸው ያሉኝ?
እናት:- ሰባት ናቸው
ልጅ:- መቼ መቼ አገባሻቸው?
እናት:-የመጀመሪያውን ሰኞ ለታ
ልጅ:- ሁለተኛውንስ?
እናት:- ማክሰኞ
ልጅ:- ሦስተኛውንስ?
እናት- ዕሮብ ለታ
ልጅ:-አራተኛውንስ?
እናት:-ሐሙስ ለታ
ልጅ:-አምስተኛውንስ?
እናት:-ዓርብ ለታ?
ልጅ:- ስድስተኛውንስ?
እናት:-ቅዳሜ ለታ
ልጅ:- ሰባተኛውንስ?
እናት:- እሑድ ለታ
ልጅ:- እማዬ ትንሽ አልቸኮልሽም?
እናት:- ምን ይደረግ፤ ጊዜው ነው
ልጅ:- የመጀመሪያውን አባቴን ለምን ፈታሽው?
እናት፡- ሁለተኛውን ላገባ
ልጅ፡- ሁለተኛውንስ ለምን ፈታሽው?
እናት፡- ሦስተኛውን ላገባ
ልጅ፡- ሦስተኛውንስ?
እናት- አራተኛውን ላገባ
ልጅ- እሺ አራተኛውንስ?
እናት፡- አምስተኛውን ላገባ
ልጅ- አምስተኛውንስ?
እናት- ስድስተኛውን ላገባ
ልጅ- ስድስተኛውን ለምን ፈታሽው?
እናት- የመጨረሻውን ላገባ
ልጅ፡- አልተጣደፍሺም እማዬ?
እናት- ጊዜው የፈቀደው ነው
ልጅ- ከመጨረሻው ጋር ለምን ቆየሽ/ ታዲያ?
እናት፡- የመጀመሪያውን እስካገኝ
ልጅ፡- ብታገኚው ልታገቢው?
እናት፡- አዎን!
ልጅ፡- ዞረሽ ዞረሽ ያው እዚያው ተመለስሽኮ? ያው ባልሽ አይደለም እንዴ?
እናት፡- አይ ያው አይደለም
እናት፡- እንዴት?
እናት፡- እሱ ያው ባል አይደለም፡፡ እኔም ያቺው ሚስት አይደለሁም
ልጅ፡- እንዴት አስረጂኝ!!
እናት፡- አየህ ልጄ፤ አሁን እሱ ፊት ሆኖ፣ ያለ ሚስት የመኖር ልምድ ያለው ባል ሆኗል፡፡ ተለውጧል፡፡ እኔ ደሞ አሁን ብዙ ባሎች የማግባት ልምድ ያላት ሚስት ሆኛለሁ፡፡ ተለውጫለሁ፡፡ ጊዜ የማይለውጠው ማንም የለም! ዋናው ይሄንን ማሰብና ከስህተት መማርና መገንዘብ መቻል ነው!
*    *    *
ጊዜ የለውጥ መዘውር ነው! ሁኔታዎች አይለወጡም ብሎ መዘናጋት የመጨረሻ የዋህነት ነው፡፡ የሰው ልጅ ጭንቅላት ውስን መሆኑን የምናውቀው፤ አይሆንም ያልነው ሲሆን፣ ይሆናል ያልነው ሲሆን፣ ነው። ሁሉም ነገር የራሱ ዘመን አለው!
“አይመጣምን ትተሸ ይመጣልን ጨምሪበት” የሚለው የአበው አባባል፤ ሁልጊዜ በቀጥታ የምናስበውን ብቻ እንደ መጨረሻ መደምደሚያ አለመውሰድና ትንሽ ቀዳዳ መተው፣ “ያ ባይሆንስ ምን አደርጋለሁ”? ብሎ ለሀሳብ መንሸራሸሪያ ቦታ ማስቀመጥ ተገቢ መሆኑን የሚያፀኸይልን ነው፡፡ በፖለቲካ ህይወታችን ውስጥ በተለይ ጊዜንና ከሱ ጋር የሚመጣውን ለውጥ ማስላት ተገቢ ነው፡፡ ማቀድ የጊዜ ተገዢ ነው፡፡ ማናቸውንም ዕቅድ ዳር ማድረሳችንን ማረጋገጥ ዋናው የመንቀሳቀሻችን አውታር መሆኑን ልብ ማለት አለብን፡፡ ዕቅዳችንን፣ መመሪያችንን፣ መሪ ፍልስፍናችንን ለህዝብ አበክሮ ማሳወቅ፣ ማንቃትና የራሴ ብሎ አምኖ እንዲጨብጠው ማድረግ ወሳኝ ነው፡፡ ቀጥሎ እንግዲህ፤ የጨበጠውን አስተምህሮት እንደምን በተግባር በሥራ ላይ ያውለዋል? የሚያደርገውንስ እነማን ይመሩታል? ያርቁታል? ይመክሩበታል? የሚለውን በቅጡ ማውጠንጠን ይገባል፡፡
ጊዜን ካጤንን፣ ጊዜ ሊያመጣና ላያመጣ የሚችላቸውን እሳቤዎች ከመረመርን፤ መንገዱ አልጋ በአልጋ አለመሆኑን፣ በየደረጃው የየራሱን መስዋዕትነት መጠየቁን፣ እናስተውላለን፡፡ መገንዘብ ያለብን፤ እንቅፋት ሁሌም ይኖራል፡፡ ዋናው ፍሬ ተግባር ግን የመጣውን ክፉ ሁሉ ተጋትሮና ተጋፍጦ ለማለፍ ስነ ልቡናዊም፣ ፖለቲካዊም ማህበራዊም ዝግጁነት ምንጊዜም መኖር እንዳለበት ማሰብ ላይ ነው፡፡ ካፊያ ዝናብ ሲታይ ከመደናገጥ ይልቅ፣ የተዘጋጀሁት ለዶፍ ዝናብ እኮ ነው፤ ብሎ የሚያስብ ልብ ማንገብ ነው፡፡ ትዕግሥትን፣ ጥንካሬንና ኢ-ስሜታዊነትን እንደ ዕለት ፀሎት ማዘውተር ነው፡፡
እስከ ዛሬ በሀገራችን ለውጥን የሚያመጣው የግራ ፅንፉ ወይም የቀኝ ፅንፍ ወገን ነው የሚል ቀኖናዊ ዕምነት ነበር፡፡ በዚሁ እሳቤ ሳቢያ በማህል ያለውን ሰፊ ህብረተሰብ ከጉዳይ አንፅፈውም ነበር፡፡ ሁሌም ወይ ጥቁር ወይ ነጭ ወገን እንጂ፤ የመካከሉን ግራጫ ክፍል “እህ?” ብለን አናደምጠውም ነበር! ከሰፊው የህብረተሰብ ክፍል የሚገኘው ሰፊ አስተሳሰብ፣ እውቀት፣ ምክር፣ ማስገንዘቢያና “እስቲ ረጋ በሉ” የሚል ማሳሰቢያ፣ ነገሬ አንለውም ነበር፡፡ ዛሬ መካከለኛው ሜዳ ላይ የታደመውን ባህር ህዝብ “ምን ታስባለህ?” የምንልበት ሰዓት መጣ!! ይሄ የለውጥ ደወል፣ የደወል ሰዓት ነው፡፡ እኛም ከደራሲው ሄሚንግዌይ ጋር “For whom the bell tolls?” (ደወሉ የተደወለው ለማን ነው?) እንደማለት ማለት አለብን!
አንድ ነገር ግን ልብ እንበል፡- የብዙሃኑን ፍላጎትና ሀሳብ አበጥሮና አንጥሮ፣ መላ መላ የሚያበጅ ንቁ ተግባራዊ ቡድን (Conscious Action Group) መፍጠር ያሻናል፡፡
ይህ ቡድን ፍፁም አድራጊ- ፈጣሪ ሳይሆን አሳቢና አመቻቺ ኃይል፣ ማለት ነው!
አንድን መሪ፤ የአገሬው ሰዎች፤
“የአገራችን የኢትዮጵያ አብዮት (ለውጥ) ቅመሙ የወጣለት ቡና (decaffeinated) ዓይነት ሆኗል የሚባለውን እንዴት ያዩታል?” ብለው ጠየቁት፡፡
መሪውም፤
“እኔ እንኳን የማየው፤ ቅመሙ የወጣለት ቡና አድርጌ ሳይሆን፤ እየበሰለ በመሄድ ላይ ያለ ወይን አድርጌ ነው (a fermenting wine)” ብሎ ነበር፡፡
ይሄ መልካም መርህ ነው፡፡ ምንጊዜም እየመረቀነ፣ እየጣፈጠ፣ እያማረ የሚቀጥል ለውጥ እንጂ አንድ ጊዜ ፈልቶ፣ በአፍታ ፈንድቶ ሁሉን ደረማምሶ፣ ሥር-ነቀል እና “በእነእገሌ መቃብር ላይ ቆመናል!” የሚያሰኝ አሊያም መፈንቅለ- መንግሥታዊ ክሳቴ አያሻም፡፡ አበው፤ “ፈልተህ ከምትገነፍል፣ እያደር ብሰል!” የሚሉት ይሄንኑ ነው፡፡ የጀመርነውን ሰላም ያብስልልን!!

Read 8215 times