Saturday, 14 April 2018 14:41

ቻይና በሞት በመቅጣትና በመግደል አሁንም ዓለምን ትመራለች

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  በአለማችን 22 ሺ ያህል ሰዎች የሞት ፍርድ ይጠብቃቸዋል

    አለማቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ተቋም አምነስቲ ኢንተርናሽናል፤ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ሰዎች በሞት በመቅጣትና በመግደል የምትታወቀው ቻይና፤ አሁንም ከአለማችን አገራት ቀዳሚነቱን መያዟን ከትናንት በስቲያ ይፋ ባደረገው አመታዊ ሪፖርቱ አስታውቋል፡፡
ቻይና ባለፈው የፈረንጆች አመት 2017 በሺህዎች በሚቆጠሩ ሰዎች ላይ የሞት ፍርድ ቅጣት ማስተላለፏን የጠቆመው የተቋሙ ሪፖርት፤ በአመቱ የገደለቻቸው ሰዎች ትክክለኛ ቁጥር ባይታወቅም በተቀረው አለም አገራት የተፈጸሙ ግድያዎች ተደምረው የቻይናን እንደማይደርሱ አመልክቷል፡፡
በአመቱ በርካታ ሰዎችን በሞት በመቅጣት በሪፖርቱ ከተጠቀሱ አገራት መካከል ኢራን፣ ሳኡዲ አረቢያ፣ ኢራቅና ፓኪስታን የሚገኙበት ሲሆን  በእነዚህ አገራት በድምሩ ከ830 በላይ ሰዎች በሞት መቀጣታቸውንም አክሎ ገልጧል፡፡
በአመቱ የሞት ቅጣት ፍርድና ግድያ በመላወ ዓለም በተወሰነ ደረጃ መቀነስ ማሳየቱን ያስታወቀው የአምነስቲ ሪፖርት፤ በ2017 የፈረንጆች አመት ቻይናን ሳይጨምር በአለማችን 23 አገራት የሞት ቅጣት የተፈረደባቸው 993 ሰዎች መገደላቸውን አመልክቷል። በአለማችን በሚገኙ 53 አገራት፣ ምንም እንኳን በሁሉም ላይ ተፈጻሚ ባይደረግም በ2ሺህ 591 ሰዎች ላይ የሞት ፍርድ ተፈርዶባቸዋል ያለው ሪፖርቱ፤ በመላው አለም 22 ሺህ ያህል ሰዎች የሞት ፍርድ ይፈረድባቸዋል ተብሎ እንደሚጠበቅም አስታውቋል፡፡
ከሰሃራ በታች ባሉ አገራት ተስፋ ሰጪ ነገር መታየቱንና 20 ያህል የአካባቢው አገራት የሞት ፍርድ እንዲቀር መወሰናቸውን የጠቆመው ሪፖርቱ፤ አንዳንድ አገራት በአንጻሩ ከልክለውት የነበረውን የሞት ፍርድ ቅጣት በ2017 እንደገና ተግባራዊ ማድረግ መጀመራቸውን ጠቅሶ፤ከእነዚህም መካከል ባህሬን፣ ዮርዳኖስ፣ ኩዌትና የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ እንደሚገኙበት አስረድቷል፡፡

Read 1725 times