Saturday, 21 October 2017 13:30

በፔርሽያን ቋንቋና በኢራኖሎጂ የሰለጠኑ ተማሪዎች ተመረቁ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(3 votes)

 በኢትዮጵያ የኢራን ኤምባሲ የባህል ክፍል፣ በፔርሽያን ቋንቋና በኢራኖሎጂ ያሰለጠናቸውን 13ኛ ዙር ተማሪዎች የዛሬ ሳምንት በባህል ማዕከሉ አስመረቀ፡፡
በምረቃው ሥነ - ሥርዓት ላይ የባህል ክፍሉ ኃላፊ ሚ/ር ሰይድ ሐሰን ሃይድሪ ባደረጉት ንግግር፤ ኢራን፣ ጥንታዊ ሥልጣኔና ባህል ያላት ሀገር መሆኗን ጠቅሰው፣ የተፃፈ ታሪኳ ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ3 ሺ 900 የሚጀምረውን ባህልና ሥልጣኔ ማወቅ ለሚፈልጉ ኢትዮጵያውያን መልካም አጋጣሚ ነው ብለዋል፡፡
ኢራንና (ፔርሽያ) ኢትዮጵያ ብዙ ዘመን ያስቆጠረ የጥንት ወዳጆ ናቸው፡፡ ከአክሱም ዘመን በፊት የቆየ ታሪክ አለን፡፡ ይህንን ታሪክ ኢራናውያንም ሆነ ኢትዮጵያውያን አያወቁትም፡፡ ይህን ለብዙ ዘመን ሲተላለፍ የቆየ ታሪክና ስልጣኔ፤ ለወደፊት አገር ተረካቢ ወጣቶች ማስተማርና ማስተላለፍ ነው ዓለማችን በማለት ገልፀዋል፡፡
ኢራን በአዲስ አበባ ኤምባሲዋን የከፈተችው በ1954 (እ.ኤ.አ) እንደሆነ ጠቁመው፣ ይህም ግንኙነታቸው ረዥም መሆኑን ያመለክታል ያሉት ሚ/ር ሰይድ፤ ከ1991 (እ.ኤ.አ) አንስቶ የሁለቱ አገሮች ግንኙነት በባህል ዙሪያ አተኩሮ፣ በመጻሕፍት፣ በሶፍትዌሮች፣ በራዲዮና በቴሌቪዥን ውጤቶች፣ በአርት በቱሪዝምና በስፖርት፣ በባለሙያዎች ልውውጥ፣ ባህላዊና የፊልም ፌስቲቫል በማዘጋጀት፣ በዩኒቨርሲቲዎችና የምርምር ተቋማት ትብብር፣ በዩኒቨርሲቲ መምህራንና በሳይንስ ተመራማሪዎች እንዲሁም በአስተማሪዎችና ተማሪዎች ልውውጥ፣ ኢራኖሎጂና የፔርሽያን ቋንቋ ማስተማር፣ … በሚል፤ ባህል ነክ በሆኑ ነጥቦች ላይ በ2003 (እ.ኤ.አ) መፈራረማቸውን ተናግረዋል፡፡
በዕለቱ 37 ወጣቶች የፔርሽያ ቋንቋና ኢራኖሎጂ ለ3 ወር ተከታትለው በሰርተፊኬት የተመረቁ ሲሆን መምህሩ ዶ/ር አርካ አቦታን፣ ኢራኖሎጂ ምን ማለት ነው? ብዬ ጠይቄአቸው ሲመልሱ፣ ኢራኖሎጂ የኢራን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ባህላዊ፣ አስተዳደራዊ፣ ዓለም አቀፋዊ ግንኙነት፣ ጂኦግራፊያዊ፣ … በአጠቃላይ የአገሪቱ ሁለንተናዊ መገለጫ ነው፡፡ ፔርሽዮሎጂ ደግሞ የጥንቷ ፔርሽያ፣ በዓለም ሥልጣኔ ከየት ተነስታ የት እንደደረሰች፣ የሕዝቦቿ ዝርያ ከየት እንደመጣ፣ የሚያሳውቅ ትምህርት ነው ሲሉ አብራርተዋል፡፡
ተማሪዎች የሚመረቁት ጥንታዊ ጽሑፍ (የምርምር ሥራ) አቅርበው ሲሆን ሁለቱ ጽሑፎች ተመርጠው ቀርበው ነበር፡፡ የመጀመሪያው ጥናት አቅራቢ አቶ ዳዊት ተፈራ፤ “ኢትዮጵያና ኢራን በታዳሽ ኃይል ዙሪያ ያላቸው ግንኙነት” በሚል ርዕስ ግሩም ጥናታዊ ጽሑፍ አቅርቧል፡፡
“ዓለም ትኩረቱን በታዳሽ ኃይል ላይ እያደረገ ባለበት በአሁኑ ወቅት፡፡ ኢራንና ኢትየጵያም በታዳሽ ኃይል ልማት ላይ እየሰሩ ነው” ያሉት አቶ ዳዊት፤ “ኢራን ከባቢ በካይ በሆነው የነዳጅ ኃይል የበለፀገች ቢሆንም ይህ ሀብት ከ25-30 ዓመት ባሉት ጊዜያት (ቢበዛ 40) ስለሚያልቅ፣ ለመጪው ትውድ ከወዲሁ አስቦ እየሰራ ነው፡፡ ኢትዮጵያም በዚሁ ዘርፍ ላይ አተኩራ እየሰራች ስለሆነ፣ ከኢራን ጋር በዚህ ዘርፍ ብትተባበር፣ ቀደምት ሥልጣኔ፣ የዳበረ ቴክኖሎጂና ልምድ ካላት ኢራን ብዙ ልትማርና ልትጠቀም ትችላለች” በማለት ገልጿል፡፡
“እኛ ኢትዮጵያውያን የረዥም ዘመን አኩሪ ታሪክ ቢኖረንም ከእኛም የበለጠ ታሪክ ያላቸው አገሮች አሉ። ቻይና የ5 ሺህ፣ ኢራን፤ (ፔርሽያ) ደግሞ የ7 ዓመታት ታሪክ አላቸው፡፡ ረዥም ታሪክና ስልጣኔ ካላት ኢራን ብዙ መማርና ልምድ መቅሰም ይቻላል፡፡ ለምሳሌ ኢራን፣ በጣም ሙያተኛ (Skilled) የሆነ የሰው ኃይል አላት፡፡ በኢንጂነሪንግ ዘርፍ ከዓለም 3ኛ ናት፡፡ ታዳሽ ኃይል መጠቀም የሚያስችል ተስማሚ ሁኔታ አላት፡፡ ከሃይድሮ (ውሃ) 6,572 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል እያመረተች ነው፡፡ 300 ቀናት የፀሐይ ኃይል የሚያገኝ ክፍለ ሀገር አላት፡፡ ከመካከለኛው ምስራቅ አገሮች ጂኦተርማል በማምረት ቀዳሚ ናት፡፡
“በመካከለኛው ምስራቅ ስለሚገኙና የቆዳ ቀለማቸው ስለሚመሳሰል ብዙዎቻችን ዐረቦች እንደሆኑ እንቆጥራለን፤ ግን አይደሉም፡፡ ፔርሽያንስ (ፋርስ) ናቸው፡፡ ቋንቋቸውም ፔርስ ከዐረብና ከሌላ ቋንቋ የተደባለቀ፣ በጣም የዳበረ፣ ለበርካታ ዘመናት ስነ - ጽሑፍ (ሊትሬቸር) ሲቀርብበት የኖረ ነው፡፡ ስለዚህ ከኢራን ብዙ መማርና ልምድ መቅሰም እንችላለን። በታዳሽ ኃይል ዘርፍ ብዙ ችግሮች አሉ፡፡ ለምሳሌ የአየር ለውጥ፣ ድርቅ፣ ረሃብ፣ የውሃ መጠን መቀነስ፣ .. የግድብ በደለል መሞላት፣ የኃይል ማስተላለፍ ሲስተም ችግር፣ .. .በኢንጂነሪንግ፣ በሶፍትዌር፣ በሳይንሳዊ ምርምር፣ … ከዚች አገር ጋር የጠበቀ ትስስር ብንፈጥር ከፍተኛ ተጠቃሚ እንሆናለን” በማለት ሐሳቡን አጠቃሏል፤ አቶ ዳዊት ታፈሰ፡፡
የኢራን የባህል ማዕከል እስካሁን 550 ተማሪችን በፔርሽያን ቋንቋና በኢራኖሎጂ ያስመረቀ ሲሆን ከዘንድሮ ተመራቂዎች መካከል ተመርጠው ኢራናን እንደሚጎበኙ ታውቋል፡፡    

Read 1878 times