Saturday, 23 January 2016 13:34

መልካም አስተዳደር የማስፈን ዘመቻ ፊሽካው ተነፍቷል!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(15 votes)

• “እነኢቢሲ፣አየር መንገድ፣ባንክ፣ዩኒቨርሲቲ፣አፍሪካ አንድነት---ሲመሰረቱ- ንጉሱ ነበሩ”
•“የኢትዮጵያ መብራት ኃይል የሚሰራውን አያውቅምና ---- በህግ ይጠየቅ!;   

    ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከሁሉም የኢህአዴግ ባለሥልጣናት አፍ ላይ የማይጠፋ አንድ ዝነኛ ቃል ጥራ ብባል፣ ቅንጣት ሳላቅማማ “የመልካም አስተዳደር ችግር” ማለቴ አይቀርም፡፡ ደግሞም አልተሳሳትኩም፡፡ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ እስከ በታች ሹማምንት ድረስ…ፍሬሽ ካድሬዎችም ሳይቀሩ ይሄንን ቃል ሲያስተጋቡት፣ ሲደጋግሙት፣ ሲያሽሞነሙኑት ----- እንደ ጉድ እየሰማን ነው፡፡ (ብቻ “ስሙ ከብዶት ሞተ እንዳንባል”!!)  
የመንግስት ባለስልጣናት (ኢህአዴጋውያን) ብቻ ሳይሆኑ እኛም ሲቪሎቹ (ሥልጣናችንን ለመንግስት በአደራ ያስረከብን!) ሳንቀር … ይሄን ቃል ቢያንስ በቀን አንድ ጊዜ ሳንጠራው አንውልም፡፡ ወደነው ወይም ቅኔያዊ ውበቱ አማልሎን ግን አይደለም፡፡ የመልካም አስተዳደር ችግር አንገብግቦን እንጂ፡፡ በእርግጥ ከትላንቱ ፖለቲካዊ ተሞክሮ (ከትላንቱ ተምረን አናውቅም እንጂ!) በመነሳት እንናገር ከተባለ፣ የቃሉ እንደ አቡነ ዘበሰማያት መደገም ብቻውን የመንግስትንም ሆነ የሌላውን ቁርጠኝነት ጨርሶ አያሳይም፡፡ (ጊዜው ግን “ሜክ ኢት ኦር ብሬክ ኢት” ነው!)
ፋሽኑ አልፎበት እንጂ ከመልካም አስተዳደር በፊት የሁሉም ሹማምንት ተወዳጅ ቃል፤ “ኪራይ ሰብሳቢ” የሚለው ነበር፡፡ (ቀላል ተቀባበሉት!) እስቲ አንድ ጥያቄ ላሽራችሁ፡፡ ከሚከተሉት ውስጥ ኪራይ ሰብሳቢ ያልሆነው የትኛው ነው? ሀ) ደላላ  ለ) ህንጻ እየገነባ የሚያከራይ ሐ) ቻይና ተመላላሽ ነጋዴ መ) ካድሬ   ሠ) ሁሉም  ረ) መልሱ አልተሰጠም
 (የተሻለ መልስ አለኝ የሚል፣ (ሰ) ብሎ የራሱን መልስ ሊሰጥ ይችላል!)
እናላችሁ ----- አንድ ሰሞን ጋዜጠኛ፣ የመንግስት ኃላፊዎችን በጥያቄ ሲያፋጥጣቸው ሁሉ፤ “አንዳንድ ኪራይ ሰብሳቢዎች ----” ምናምን እያሉ መሸወድ ጀምረው ነበር፡፡ በነገራችን ላይ ----- የልማታዊ መንግስት ተቃራኒ፣ኪራይ ሰብሳቢ መንግስት ነው --- አይደል? የልማታዊ ነጋዴ ተቃራኒ ደግሞ ኪራይ ሰብሳቢ ነጋዴ? (ከቃሉ ጽንሰ ሃሳብ ጋር በቅጡ ለመተዋወቅ ብዬ እኮ ነው!) ትዝ ይላችኋል ---- አንድ ሰሞን ሰራዊት በሰራዊት ሆነን ነበር እኮ! (ሠራዊት ፍቅሬን አላልኳችሁም!) የልማት ሠራዊት ---- የኮብል ስቶን ሠራዊት ---- የግብር ሰብሳቢ ሰራዊት ------ የጤና ኤክስቴንሽን ሠራዊት ------ ወዘተ --- ማለቴ ነው፡፡ “የሥልጣን ሠራዊት” ሲባል ግን ሰምቼ አላውቅም፡፡ (ሥልጣንና ሠራዊት እንኳን ይስማሙ ነበር!)
ወደጀመርነው ልመልሳችሁ - ወደ ኪራይ ሰብሳቢነት፡፡ እናላችሁ --- በባህላዊ መንገድ በተደረገ ጥናት መሰረት፤ የመንግስት ቦሶች “ኪራይ ሰብሳቢዎችን እንታገላለን” ብለው ከማሉ በኋላ የኪራይ ሰብሳቢዎች ቁጥር በ300 ፐርሰንት ተመንድጓል አሉ፡፡ (ታግለው ላይታገሉ ጉድ ሰሩን)  
እኔ የምላችሁ…”መልካም አስተዳደር” በሚለው ቃል ዙሪያ አገራዊ መግባባት (consensus) ላይ ተደርሷል እንዴ? (ሳንግባባ የወጠነው… ከግብ አይደርስም ብዬ እኮ ነው!) ለማንኛውም ግን እቺን ሌጣ ጥያቄ እስቲ መልሱልኝ (ሽልማት አልባ ማለቴ ነው!)
ከሚከተሉት ውስጥ የመልካም አስተዳደር ችግር የሆነው የትኛው ነው? ሀ) ሰላማዊ ሰልፍ መከልከል ለ) መሰረተ ልማት አለመሟላት ሐ) ለመሰረታዊ አገልግሎት እጅ መንሽያ መጠየቅ መ) የመብራትና ውሃ መቆራረጥ ሠ) ሁሉም ረ) መልሱ አልተሰጠም፡፡
በነገራችሁ ላይ በየክልሎቹ ሳይቀር መልካም አስተዳደር የማስፈን ዘመቻ ፊሽካው ተነፍቷል፡፡ ዋና ዳኛውና ረዳቱ እንዲሁም አራጋቢው ----- ሁሉም ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ ፍትሃዊና ሃቀኛ ፍርድ የመስጠት ብቃት ይኖራቸው ይሆን? እንደዚህ ቀደሙ ጨዋታው በፎርፌ ተጠናቆ ያሳዝነናል ወይስ ስኬታማ ግጥሚያ የምናይበት አጋጣሚ ይሆናል? መልሱን ጊዜ ብቻ ነው የሚነግረን፡፡ የነገ ሰው ይበለን፡፡
የጥምቀት ዋዜማ ዕለት ምሽቱን፤50ኛ ዓመት የምስረታ ኢዮቤልዩውን ለማክበር ሽርጉድ በሚለው EBC ምን ሰማሁ መሰላችሁ? “የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በመብራት መቆራረጥ መማረራቸውን ገለፁ” የሚል ዜና፡፡ እውነት ለመናገር ዘገባው ብዙም አልመሰጠኝም፡፡ ለምን መሰላችሁ? ህዝቡ በመብራት መቆራረጥ ቅሬታውን ያልገለፀበት ጊዜ የለማ፡፡ (ከሰላማዊ ሰልፍ ውጭ ማለቴ ነው!) ሆኖም መታገስ አቅቶኝ ነው እንጂ ለካስ ዘገባው አላለቀም ነበር (የአዲስ አበባ ከንቲባ ነዋሪው ላሳየው ትዕግስት አድናቆታቸውን መግለፃቸው ትዝ አለኝ!)  እናላችሁ…የመብራት ኃይል አገልግሎት የአንድ አካባቢን ነዋሪዎች በሰፊ አዳራሽ ሰብስቦ ማወያየቱን ይገልፃል - የኢቢሲ ቀጣይ ዘገባ፡፡ ቆይ ግን መብራት ሃይል ህዝቡን የሰበሰበው ምን እንዲለው ፈልጐ ነው? ነዋሪው አንዳች ተዓምራዊ መፍትሔ ይለግሰኛል ብሎ ሊሆን ይችላል፡፡   ወይም ደግሞ ህዝቡን ከጨለማ ለማውጣት (ምንም እንኳን ባይሳካለትም!) ብዙ መልፋቱ እንዲታወቅለትና ለትውልድ እንዲተላለፍለት ፈልጐ ይሆናል፡፡ ከምሬ ነው የምላችሁ… ከተለመደው የመብራት መቆራረጥ በተለየ በቅርቡ ከፍተኛ የሃይል ችግር እንደተከሰተ ህብረተሰቡም ያውቃል፤ መብራት ሃይልም ያውቃል፡፡ ለዚህ መፍትሔው ግን አዳራሽ በነጻ አገኘሁ ብሎ ህዝብን መሰብሰብ አይደለም፡፡ መብራት ሃይል ስለተከሰተው ችግር በመገናኛ ብዙሃን ይቅርታ ጠይቆ፤ በተቻለ ፍጥነት መፍትሔ ለመስጠት መጣር ነበረበት፡፡  
በእርግጥ የመብራት መቆራረጥ ችግር…የ“መልካም አስተዳደር” ጉድለት መሆኑ እሙን ነው፡፡ ለዚህ ይሆናል ህዝቡን ያወያየው፡፡ ነገር ግን ለእያንዳንዱ የ “መልካም አስተዳደር” ችግር ህዝብን አወያይቶ አይዘለቅም፡፡ በዚያ ላይ ህዝቡ መብራት ማጣቱን እንጂ መንስኤውን አያውቀውም፡፡ እናላችሁ…እኔ መንግስትን ብሆን… መ/ቤቱ ሰሞኑን ከህብረተሰቡ ጋር ያደረገውን ውይይት ገምግሜ ሃላፊዎቹን ወደ ፍ/ቤት እልካቸው ነበር፡፡ (በህዝብ ላይ ማፌዝ እንዲቆም እኮ ነው!)
ታዋቂው ጋዜጠኛና ፀሐፌ ተውኔት ቴዎድሮስ ተ/አረጋይ ሰሞኑን በመብራት መቆራረጥ ተማርሮ በፌስቡኩ ላይ ያሰፈረውን ማስታወሻ ላጋራችሁ፡፡ (ንዴቱን እንድትጋሩት እኮ ነው!) “የመብራት ኃይል (ካለው) ኃላፊን ባገኛቸው” በሚል የሚጀምረው ፀሐፊው፤ ቢያገኛቸው ምን ሊጠይቃቸው እንደሚሻ ይነግረናል፡፡
እኚህ የመብራት ኃይል ኃላፊን ባገኛቸው ብዙ ጥያቄ አይኖረኝም፡፡
•    “መብራቱ በቀን አስሬ መቆራረጡ ለምን ነው?” አልልም፡፡
•    “የእኛ ገና አልፏል፤ የመንግስት አላለፈም?” አልልም፡፡
•    “ምክንያቱንና መፍትሔውን ቢገልፁልኝ!” አልልም፡፡
•    “በመብራት እጥረት በጭለማ ለሚደናበረው ህዝብዎ የሚያስተላልፉት መልዕክት ካለ” አልልም፡፡ አንድ ጥያቄ ብቻ ብጠይቃቸው ደስ ይለኛል፡፡
“ማታ ሲተኙ ሥራውን እንደጨረሰ ሰው እንቅልፍ ይወስድዎታል? አመሰግናለሁ!” ብዬ መልሳቸውን እንኳ ሳልሰማ ከቢሯቸው እወጣ ነበር፡፡
*    *    *
የቴዲ ጥያቄ ሃላፊነት ለሚሰማው ኃላፊ እንቅልፍ የሚነሳ ነው፡፡ መሬት ላይ ያለው እውነታ ግን ከዚህ የተለየ ይመስለኛል፡፡ “ኃላፊነቴን በአግባቡ አልተወጣሁም” ብሎ እንኳንስ እንቅልፍ የሚቸገር ለአፍታም የሚጨነቅ ሹመኛ ይኖራል ብዬ አልገምትም (ቢኖር ጭምጭምታ እንሰማ ነበራ!) በሰለጠኑት አገራት ቢሆን ሃላፊው ራሱ ሥልጣኑን በገዛ ፈቃዱ ይለቅ ነበር (እዚህ ኢህአዴግ ይፈቅዳል እንዴ?) በልማታዊ መንግስት አሰራር  በግል እንቅልፍ ማጣትም ሆነ መጨነቅ የሚቻል አይመስለኝም፡፡ (ከተጨነቁም በደቦ ነው!) እስከዛሬ እንደምናውቀው በኢህአዴግ ዘንድ፤ ምስጋናም ሆነ እርግማን በግለሰብ ደረጃ የለም፡፡ በጋራ ነው፡፡ በፓርቲ፡፡ ለመብራት መቆራረጡ ወይም መጥፋቱ እንቅልፍ ማጣት ካሰፈለገም፣ ግለሰብ ሃላፊዎች ሳይሆኑ አውራው ፓርቲ ይወጣዋል፡፡ (ኢህአዴግ የግለሰቦች ተሰጥኦና ችሎታ አይመስጠውም!) ለዚያ ይመስለኛል በመ/ቤት… በት/ቤት… በአርሶአደር ልማት… በዩኒቨርሲቲ… በጤና አገልግሎት… በአነስተኛና ጥቃቅን ወዘተ… በ1ለ5 የሚያደራጀው፡፡ አደረጃጀት ይመቸዋል፡፡  (“የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው” ብለናል!!)
የጥምቀት ዕለት ቤት ቁጭ ብዬ ከብሔራዊ ቴሌቪዥናችን በቀጥታ የሚሰራጨውን የጥምቀት በዓል ሃይማኖታዊ ሥነስርዓት እየተከታተልኩ ነበር - በከፊል እየሰራሁ ማለት ነው፡፡ በሙሉ ትኩረት ቲቪውን መመልከት የጀመርኩት የአዲስ አበባ ከንቲባ ጽ/ቤት ቢሮን ወክለው የተገኙ አንድ ሃላፊ ንግግር ማድረግ ሲጀምሩ ነው፡፡
እናላችሁ…በደርግ ዘመን ጥምቀት ተከብሮ የማያውቅ አስመስለውት ቁጭ አሉ (በጥምቀት ይዋሻል?!) የሚገርመው…ኢህአዴግ ዛሬም በ25ኛ የሥልጣን ዓመቱ፣ የሃይማኖት እኩልነት ማስፈኑን ሊያስረዳን የሚታትረው ራሱን ከደርግ ጋር በማነፃፀር ነው፡፡ (እኩያውን አያውቅም ?!) እኔ የምለው ---- መቼ ነው ደርግ ለኢህአዴግ ታሪክ የሚሆነው?
ሌላው ሌላው የደርግ ኃጢአት እንዳለ ሆኖ፣ በጥምቀት በዓል ላይ እገዳ ጥሎ ነበር ወይ የሚለውን ባስበው ባስበው ትዝ አልልህ አለኝ፡፡ ወዳጆቼንም ብጠይቅ ትዝ የሚለው ጠፋ፡፡ ጥምቀት በነጻነት መከበር የጀመረው ከ1983 ዓ.ም በኋላ ከሆነ እኮ የግንቦት 20 ትሩፋቶች ውስጥ መካተት አለበት፡፡ ይሄን ጉዳይ የሰማ አንድ ወዳጄ ምን ቢለኝ ጥሩ ነው? “አንዳንዴ ኢህአዴግ፤ ጦቢያን የቆረቆራት ሁሉ ይመስለዋል፡” እኔ እንደ ወዳጄ አስቤ አላውቅም፡፡ እውነቱ ወዳጄ እንደሚለው ከሆነ ግን በአፋጣኝ ደህና ሃኪም መፈለግ አለብን፡፡ (ህመም እኮ ነው!)
 ከጥቂት ሳምንታት ወዲህ ኢቢሲ…የ50ኛ ዓመት ኢዮቤልዩ በዓሉን ለማክበር ሽርጉድ እያለ መሆኑን እያየን ነው፡፡ ኢቢሲ የዛሬ 50 ዓመት የንጉሰ ነገስቱ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴን የዘውድ  ክብረ በዓል ለመጀመሪያ ጊዜ በቀጥታ በማሰራጨት አገልግሎቱን አሀዱ ብሎ እንደጀመረ፡ ከራሱ ከቴሌቪዥን ጣቢያው ሰምተናል፡፡ እናላችሁ ------ በዚህ ክብረ በዓል ሰበብ ዕውቅና ለተነፈጉት የጦቢያ ንጉስ፣ተገቢውን ክብርና ቦታ በመስጠት ቢዘክራቸው ትልቅ ታሪክ  ያስመዘግብ ነበር፡፡ (ባለውለታው ናቸው) ይሄን በማድረግም ለእውነት ዋጋ የሚሰጥ ሚዲያ ወደ መሆን መሻገሩን ሊያሳይበት ይችላል፡፡ እግረ መንገዱንም ታላላቅ ሰዎቻችንን የማክበርና የመዘከር መልካም ባህልን በማጎልበት ረገድ የበኩሉን አስተዋጽኦ ያበረክት ነበር፡፡  
በነገራችን ላይ… “የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን፣ የብሔራዊ ባንክ ውብ ህንፃ፣ ወደር የለሹ ብሔራዊ ቲያትር፣ አምባሳደር ሲኒማ፣ አንጋፋው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ በዓለም ላይ ስሙ የናኘው የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እና ሌሎችም---ሲመሰረቱ ንጉሱ ነበሩ” ወደድንም ጠላንም የቀዳማዊ ኃይለስላሴ ወይም የንጉሳዊ ሥርዓቱ ትሩፋት (ፍሬዎች) መሆናቸው የማይታበል ሃቅ ነው፡፡
በነገራችን ላይ እኔ መንግስትን ብሆን ----- ምን እንደማደርግ ታውቃላችሁ? የኢቢሲን 50ኛ ዓመት በዓል ምክንያት በማድረግ፣ ንጉሱ የቴሌቪዥን ጣቢያውን እንዴት እንደመሰረቱት የሚያሳይ ጥልቅ ዶክመንታሪ እንዲሰራላቸው አደርግ ነበር፡፡ ይሄን ማድረግ የፈፀሟቸውን ትላልቅ ስህተቶች መካድ አይደለም፡፡ ለበጐ ሥራቸውና ለአገሪቱ ላበረከቱት የጐላ አስተዋጽኦ ክብርና ዕውቅና መስጠት እንጂ፡፡ አገር የምትገነባው ከዜሮ ወይም ከባዶ ሳይሆን በቅብብል ፣አንዱ የጀመረውን ሌላው ተቀብሎ በማሳደግና በማሻሻል መሆኑንም ለአዲሱ ትውልድ ለማስተማር ይጠቅማል፡፡
ለእኔ ንጉሱን ማክበር ኢትዮጵያን ማክበር ነው፡፡ ያለፈው ትውልድ ላከናወነው ተግባር ዕውቅና መስጠትም ነው፡፡ ይሄንን ማድረግ ያለበት ደግሞ በሥልጣን ላይ ያለው ገዢ ፓርቲ ኢህአዴግ ይመስለኛል፡፡ ከፈለገ ደሞ ይችላል፡፡ አዎ ----- የራሱንም የአገሪቱንም ታሪክ የሚለውጥበት መልካም አጋጣሚ ሊሆንለትም ይችላል፡፡ (ሁሉም የዘራውን ያጭዳል!!)

Read 6087 times