Saturday, 05 September 2015 08:33

የመልካም አስተዳደር ጉድለት በፐርሰንት ይነገረን !!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(18 votes)

ኢህአዴግ ከተቃዋሚዎች ጋር እሰራለሁ ያለው ከአንጀቱ ነው ከአንገቱ?
በመጪው ጉባኤ የኪራይ ሰብሳቢነት ችግር ባይፈታስ? (ሂስ ያደርጋላ!)
ተቃዋሚዎች አንዳንዴ በኢህአዴግ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ይጋበዙ እንጂ!!


ኢህአዴግ በመቐለ ከተማ ባደረገው 10ኛው ጠቅላላ ጉባኤ ማጠናቀቂያ ላይ የግንባሩ  ሊቀመንበር ሆነው በድጋሚ የተመረጡት ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፤ (በድጋሚ ያልተመረጠውን ንገሩኝ?!) ከተቃዋሚዎች ጋር በጋራ ለመስራት እንደሚፈልጉ ጠቅሰው  ለተቃዋሚዎች ልባዊ የሚመስል ጥሪ ሲያስተላልፉ ሰማሁ፡፡ አንዳንዶች ግን ከአንጀት ይሁን ከአንገት ገና አልታወቀም ይላሉ፡፡ በእርግጥ ምክንያት አላቸው፡፡
ለምሳሌ አንዳንድ ተቃዋሚዎች----- በ2002 ምርጫ ማግስት፣ኢህአዴግ እንዲሁ ተመሳሳይ ቃል ገብቶ እንዳልፈጸመው በማስታወስ፣ያሁኑም ከቀድሞው አይለይም በማለት ነገሩን ዋዛ ፈዛዛ ያደረጉት ይመስላሉ፡፡ (በነሱም መፍረድ ይቸግራል!) ቀኝ ዘመም የሆኑ የፖለቲካ ተንታኞችም፤ኢህአዴግ በየ5 ዓመቱ እንዲህች ያለች “ፉገራ” ለምዷል ሲሉ በነገር ወጋ አድርገውታል፡፡ (የሂስ ሃንግኦቨር ላይ ስለሆነ ግን አይሰማቸውም!)
ኢህአዴግ የ2002 ምርጫን በ96. ምናምን ፐርሰንት ባሸነፈ ማግስት፤ “ተቃዋሚዎች ፓርላማ ባይገቡም (ያኔ እንኳን አንድ ለመድኀኒት ያህል ገብቶ ነበር!) በአገሪቱ ወሳኝ ጉዳዮች ላይ የሚሳተፉበት መድረክ ይፈጠራል” ሲል አውራው ፓርቲ በአደባባይ ቃል ገብቶ ነበር፡፡ “ባለፉት 5 ዓመታት ግን እንኳንስ በአገሪቱ ጉዳዮች ላይ የመሳተፍ ዕድል ሊሰጠን ቀርቶ ህገ መንግስታዊ መብታችን ተጥሶ፣ህልውናችን ለአደጋ የተጋለጠበት ጊዜ ነበር; በማለት አንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ ገዢውን ፓርቲ አምርረው ይወቅሳሉ (አምርረው ይረግማሉ ቢባል ይቀላል!)
በአጭር ቋንቋ “እንኳን በአገሪቱ ጉዳዮች ሊያሳትፈን በዓይኑ እንኳን ሊያየን አይወድም ነበር” ይላሉ፤ተቃዋሚ ፓርቲዎች፡፡ እናም በኢህአዴግ 10ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ማጠናቀቂያ ላይ ጠ/ሚኒስትሩ ያስተላለፉትን ጥሪ “ፌዝ” ነው ባይ ናቸው፡፡ (ነቄ ነን እንደማለትም ይመስላል!) እስቲ ለማንኛውም ጠ/ሚኒስትሩ በጉባኤው መጠናቀቂያ ላይ ያሉትን ሙሉ ቃል እንመልከተው፡-
“ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በህጋዊና ሰላማዊ መንገድ ከኢህአዴግ ጋር ለመስራት በፈቃዳችሁ ልክ፣ ኢህአዴግ ከእናንተ ጋር ተባብሮ በሚያስማሙን ጉዳዮች ላይ አብሮ ለመስራት፣ በሚያለያዩን ጉዳዮች ላይ ለመተጋገል የወሰነ በመሆኑ፣ በዚህ አጋጣሚ መላው የአገራችን ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለአገራችን የህዳሴ ጉዞ የበኩላችሁን ድርሻ እንድትወጡ ጥሪዬን ለማቅረብ እወዳለሁ”
እንግዲህ እንደምታዩት… ጥሪው በሸጋ ቋንቋ የቀረበ፣በትህትና ቅላጼ የተቃኘ ነው፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን ተቃዋሚዎች የኢህአዴግን ባህሪ በልተነዋል እያሉ ነው (ዳግም አንሸወድም ነው ነገሩ!) እኔ ደግሞ አሁን የምሩን ቢሆንስ? ስል ጥርጣሬ ገባኝ፡፡ (ቋንቋ መግባቢያ መሆኑ ቀረ?!)
እኔ የምለው ግን ኢህአዴግ በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ራሱን ሲገመግምና በራሱ ላይ ሂስ ሲያደርግ፣ የተቃዋሚ ፓርቲዎችን ጉዳይ አንስቶ ይሆን? (አንስቶም ከሆነ አልነገረንም ብዬ ነው!) እርግጥ ነው ------ የመልካም አስተዳደርንንና የኪራይ ሰብሳቢነትን ችግር ያህል ቅድሚያና ትኩረት ይሰጠዋል ብለን አንጠብቅም፡፡ ግን መነሳቱ የግድ ነው (ኢህአዴግ---የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት መሰረት እንዲይዝ እተጋለሁ ሲል ሰምቼ እኮ ነው!) … እናላችሁ ተቃዋሚዎች በየጊዜው የሚያሰሙትን ምሬትና እሮሮ------ የሚያወጡትን መግለጫ------ ራሱ ሲወስዳቸው ከነበሩት እርምጃዎች (ምላሾች) አንፃር ገምግሞ “ትክክል ነኝ… በጀመርኩት እቀጥላለሁ” አሊያም “በተቃዋሚ አያያዝ ላይ የማሻሽለው ነገር አለኝ” ብሎ ሂስ ማድረግ ያለበት ይመስለናል (እኛ ከኢህአዴግ ባናውቅም!)
በነገራችን ላይ… የተቃዋሚዎች እሮሮና ምሬት እኮ በአገራዊ ጉዳዮች ላይ ለምን አልተሳተፍንም የሚል አይደለም፡፡ (እዬዬ ሲዳላ ነው አሉ!) ይልቁንም በአመራሮቻችንና በአባላቶቻችን ላይ ከፍተኛ ወከባና ድብደባ… እስርና ግድያ እየተፈፀመብን ነው የሚል ውንጀላ ነው፡፡ ይሄን ተከትሎ ደግሞ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት … መንግስትን/ኢህአዴግን በመብትና ነጻነት አፈና እንዲሁም በሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ደጋግመው በመውቀስ በዓለም ፊት እያሳጡት ነው፡፡ (የኒዮሊበራል አቀንቃኝ መሆናቸው አልጠፋኝም!) አነሰም በዛም የአገር ገጽታን እንደሚያጠለሽም ኢህአዴግ አይስተውም፡፡ (አሁንም ቢሆን ለግምገማ አልረፈደም!)
በነገራችን ላይ በቅርቡም እኮ (በግንቦቱ ምርጫ ማግስት ማለቴ ነው!) ኢህአዴግ አንድ ቃል ገብቶ አልፈጸመም፡፡ በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ላይ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን አወያያለሁ ብሎ ነበር፡፡ (እሱም አያርመውም ልበል?!) እስካሁን ግን ውይይቱ ስለመካሄዱ የሰማነው ነገር የለም (መቼም በምስጢር አይካሄድም አይደል?!) ይህቺ የማወያየት ነገር እኮ በቅርቡ በንግዱ ማህበረሰብ ዘንድም ቅሬታ አስነስታ ነበር፡፡ (“ኢህአዴግ የማሳተፍ ተነሳሽነት ይጎድለዋል” ልበል?!) እናላችሁ … የጠ/ሚኒስትሩ የፖሊሲ አማካሪ ዶ/ር አርከበ ዕቁባይ፤ ከንግዱ ህብረተሰብ ጋር ባደረጉት ግልፅነትና ድፍረት የተንፀባረቀበት የውይይት መድረክ ላይ፤ “እውነት እንደ አጋር የምትቆጥሩን ከሆነ፣ ለምን በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎሜሽን ዕቅድ ላይ ለውይይት አልተጋበዝንም?” ሲሉ ጠየቁ (የፈለገ ተሸምድዶ ቢገባ የማይመለስ ቦንብ ጥያቄ እኮ ነው!)
በራሱ ቋንቋ ልጠቀምና ኢህአዴግ በንግዱ ህብረተሰብ ላይ ያለውን ብዥታ በጊዜ አጥርቶ በአጋርነት አብሮ ለመስራት ካልቆረጠ፣የሚፈለገውን ውጤት ያስመዘግባል የሚል እምነት የለኝም (በሱ አለመቁረጥ የምንጎዳው ደግሞ እኛ ነን!) በተመሳሳይ ሁኔታ በሰላማዊ መንገድ በሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ላይ ያለውን ብዥታም ማጥራት ይኖርበታል፡፡ (ብዥታው ሲጠራ ብቻ ነው ጠ/ሚኒስትሩ ያሉት በጋራ የመስራት ነገር እውን የሚሆነው!)
አንዳንዴ የኢህአዴግ ነገር የገባኝ ሲመስለኝ ለራሴ እንዲህ እላለሁ፡፡ ነገርየው አግባብ ባይሆንም  እንኳን-----ተቃዋሚዎችን ጠጋ ብሎ፤“አገሪቷን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ እስከማሰልፍ አታካልቡኝ … ቀዝቀዝ በሉ!” ቢላቸውስ እላለሁ (የስልጣን ፉክክር ከልማት በኋላ እንደማለት ነው!)
ሌላው ደግሞ ምን መሰላችሁ ----- (በእርግጥ አንገብጋቢ ላይሆን ይችላል!) ግን ተቃዋሚ ፓርቲዎች አንዳንዴ እንኳን በኢህአዴግ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ቢጋበዙ ምናለበት? የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲና ሌሎች ወዳጅ የአፍሪካ ፓርቲዎች ይፏልሉበት የለም እንዴ? በዚህም ተባለ በዚያ ግን ኢህአዴግና ተቃዋሚዎች ለአገሪቱ የተሻለ እድገት ለማምጣት እንደሚፎካከሩ ፓርቲዎች እንጂ እንደ ታሪካዊ ጠላት የሚተያዩበት ዘመን ማብቃት አለበት፡፡ በመተካካቱ ሂደትም “የጥላቻ ፖለቲካ በኛ ይብቃ” ብለው ለአዲሱ ትውልድ የሰለጠነ የፖለቲካ ባህል ማውረስ አለባቸው፡፡ እንግዲህ----በኢህአዴግ 10ኛው ጠቅላላ ጉባኤ መጨረሻ ላይ ከተሰጡ መግለጫዎች እንደተረዳነው፤ በመልካም አስተዳደር ላይ ሥር ነቀል ለውጥ ማምጣት አልተቻለም፡፡ ኪራይ ሰብሳቢነት ልክ አጥቶ ተባብሷል፡፡ ሙስና ተንሰራፍቷል፡፡ አድርባይነት በዝቷል፡፡ ህዝቡ ትዕግስት በደርዘን የታደለ ሆኖ እንጂ በአገልግሎት አሰጣጥ ጉድለት በእጅጉ ተማሯል፡፡ እኔ እንደውም ትንሽ አብርጄው ነው እንጂ የኢህአዴግ አመራሮች ሲናገሩት እኮ በሥልጣን ላይ የሚቀጥሉ ሁሉ አይመስሉም (ራሳቸውን ሲገመግሙ ለነገ አይሉም!) … ለዚህም ነው ኢህአዴግ፤ “የመልካም አስተዳደር ጉዳይ በተለይ ግልፅነትና ተጠያቂነትን ማረጋገጥ የህልውና ጉዳይ በመሆኑ የሞት ሽረት ትግል አደርግበታለሁ” ሲል ያስታወቀው፡፡ ይሄ ግን ለእንደኔ ያለው አገሩን ወዳድ ተራ ተርታ ዜጋ ብዙም አይገባም፡፡ (የችግሩን ጥልቀትና ስፋት አያሳይማ!) በዚያ ላይ በአብዛኛዎቹ የኢህአዴግ ጠቅላላ ጉባኤዎች ማጠናቀቂያ ላይ ተመሳሳይ መግለጫዎችን ስንሰማ ነው የኖርነው፡፡ የኪራይ ሰብሳቢነት … አድርባይነት … ሙሰኝነት … የአመለካከት ---- ወዘተ ችግሮች ብርቃችን አይደሉም፡፡ ጥያቄው----ችግሮቹ ምን ያህል ሥር ሰደዱ? የሚለው ነው፡፡
ለዚህ መላ ይሆነን ዘንድም የስታቲስቲክስ ኤጀንሲ ቢያግዘን ሸጋ ነው፡፡ የኢኮኖሚ ዕድገታችንን በቁጥር እያሰላ ባለሁለት አሃዝ ዕድገት ተመዝግቧል እንደሚለን ሁሉ … (ቁጥር በግድ አስለምዶን የለ!) የመልካም አስተዳደር ጉድለቱን … የኪራይ ሰብሳቢነት ችግሩን መጠን…. የሙስናውን ጥልቀትና ስፋት … የአድርባይነቱን ሁኔታ …. ዲሞክራሲን በማሳደግ ይሁን በማቀጨጭ የተገኘውን ለውጥ … አስልቶ ወይ ለክቶ በፐርሰንት ይንገረን፡፡ (ለወሬ እንኳን አልተመቸንም እኮ ነው!)
ከምሬ እኮ ነው … ቆይ ያለፈውን የመልካም አስተዳደር ጉድለት እንዴት ከዘንድሮው አነፃፅረን ልዩነቱን እንወቅ! አያችሁ----ሌላው ቢቀር የመልካም አስተዳደር ጉድለቱ ባለአንድ አሃዝ ነው ወይስ ባለሁለት የሚለውን ማወቅ እኮ ቀላል አይደለም፡፡ እኔ የምለው ግን --- በመልካም አስተዳደር ሥር ነቀል ለውጥ አልመጣም ነው የተባለው አይደል? (ሥርነቀሉ ይቅር --- ኢምንት ለውጥስ ተመዝግቧል?) ለማንኛውም ----- በቁጥር እንነጋገር እያልኩ ነው (ተጨባጭ ይሆንልናል እኮ!)
አንድ የመጨረሻ ሃሳብ ሰንዝሬ ወጌን ልቋጭ፡፡ ኢህአዴግ በራሱ ላይ በሚያደርገው ምህረት የለሽ ሂስ በእጅጉ አደንቀዋለሁ፡፡ ለሌላ ተቺ እንኳን ክፍተት ሳይሰጥ እኮ ነው ራሱን  የሚቀጠቅጠው፡፡ (የሂስ ተመክሮውን ለወዳጅ አገራት ማጋራት አለበት!) ችግሩ ግን ምን መሰላችሁ? ግምገም ብቻ ነው፡፡ ሂስ ብቻ፡፡ በጥፋቱ ተጠያቂ ተደርጎ የሚባረር ሹመኛ፣ሚኒስትር፣የፓርቲ አመራር ወዘተ----አይተን አናውቅም፡፡ (ያፈጠጡ ያገጠጡ ሙሰኞች ካልሆኑ በቀር!)
እኛ አገር ደግሞ አንድ ባለሥልጣን የሚመራው መ/ቤት የፈለገ ውድቀትና ኪሳራ ቢደርስበት (እንደሰለጠኑት አገራት) አልቻልኩም ብሎ በገዛ ፈቃዱ ከሃላፊነቱ አይለቅም፡፡ (ነውር ነው!) እናም ከእነ አለመቻሉ እየተገመገመ ይቀጥላል፡፡ ግለ ሂስ እስካደረገ ድረስ የከፋ እርምጃም አይወሰድበትም፡፡ ይልቁንም ሁሌ እንደምንሰማው ----- አመራሩ በጅምላ ኃጢያቱን ተሸክሞት ቁጭ ይላል፡፡ ራሴን ገምግሜአለሁ፣ጥፋቴን አምኛለሁ፣ከስህተቴ ተምሬ---ቀምሬ---በመጪዎቹ 5 ዓመታት አመርቂ ውጤት ለማስመዝገብ በቁርጠኝነት ተነስቼአለሁ ----- ይለናል ፊታችን ቆሞ፡፡ ማን? የኢህአዴግ አመራር! (ሙሉ አመራር ከሥልጣን ይውረድ አይባል?!)
ይሄ ሳይሆን አይቀርም ከዓመት ዓመት እየተጫወተብን ያለው ችግር፡፡
እናላችሁ-----በየጊዜው በኢህአዴግ ጠቅላላ ጉባኤ ማብቂያ ላይ የምንሰማው የአቋም መግለጫ ወይም ውሳኔ ----- ፈረንጆቹ New year’s Resolution እንደሚሉት ዓይነት ነገር እየሆነ የመጣ ይመስላል፡፡ አንድ ሰው አዲስ ዓመት መጥቢያ ላይ ለራሱ የሚገባው የውሳኔ ቃል ሊባል ይችላል፡፡ ለምሳሌ በአዲሱ ዓመት ሲጋራ አቆማለሁ----መጠጥ የደረሰበት አልደርስም----ትምህርት እቀጥላለሁ---ወዘተ---ብሎ ለራሱ ቃል ይገባል፡፡ ነገር ግን በዓመቱ መጨረሻ ላይ ቃል ከገባው ውስጥ አንዱንም ላይፈጽም ይችላል፡፡ ሆኖም የሚጠይቀው------የሚወቅሰው ማንም የለም፡፡ ከህሊናው በቀር፡፡ ቃሉን ባለማክበሩም ቅጣት የለበትም፡፡ ለነገሩ ግለሰቡ ማድረግ ያለበትን ባለማድረጉ የሚጎዳው ራሱ ብቻ ነው፡፡ የኢህአዴግ ሪዞሉሽን ግን ይለያል፡፡ በ95 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ስም የሚደረግ ስለሆነ በአግባቡ ሳይፈጸም ሲቀር፣ ያ ሁሉ ህዝብ ለችግር ይዳረጋል፡፡ ለመልካም አስተዳደር ጉድለት፣ለኪራይ ሰብሳቢነት፣አድርባይነት ለሚያስከትላቸው ዘርፈ ብዙ ችግሮች ወዘተ ይጋለጣል፡፡ በዚህም የተነሳ የኢህአዴግ ሪዞሉሽን ወይም ውሳኔ በልዩ ጥንቃቄ እንዲሁም ተጠያቂነትና ሃላፊነት በተሞላበት መልኩ ተፈጻሚ ሊሆን ይገባል፡፡
ለማንኛውም ግን ያሰብነውን ------ ያቀድነውን ------- የጀመርነውን ------ ሁሉ ያሳካልን፡፡ ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!

Read 5108 times