Saturday, 16 May 2015 10:59

ሲያጌጡ …. ብርሃንዎን እንዳያጡ!

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(16 votes)

ያለሃኪም ትዕዛዝ የሚደረጉ መነፅሮች ለአይነስውርነት ሊያጋልጡ ይችላሉ

    ፒያሣ ነኝ፡፡ ሲኒማ ኢትዮጵያ ፊት ለፊት፤ ቼንትሮ ካፌ ጀርባ ከሚገኘው የደራ የመነፅር ገበያ ውስጥ። እዚህ መነፅር ለመግዛት ከየሥፍራው የሚመጡ በርካታ ወንድና ሴት ወጣቶችን ማግኘት ይቻላል። ቦታው ሁሉም እንደየምርጫውና እንደየአቅሙ የሚፈልገውን ማግኘት የሚችልበት ሥፍራም ነው፡፡ ሸማቹ አይኑ የገባችውን መነፅር ያስወርድና አይኑ ላይ ስክት አድርጎ በትንሿ ክብ መስታወት አየት አየት ያደርግና ከሻጩ ጋር ዋጋ ይደራደራል፡፡ በዋጋ ድርድሩ ከተስማሙ ዋጋዋን ከፍሎ መነፅሯን ይዞ ይሄዳል፡፡ የንባብ፣ የፀሐይ፣ የዝነጣ፣ የዋና እና የልጆች እየተባሉ የሚለዩ የመነፅር አይነቶች በብዛትና በዓይነት ለሽያጭ ከሚቀርቡባቸው የከተማዋ የንግድ ቦታዎች የፒያሳው የመነፅር ገበያ ዋንኛው ነው፡፡ ከ70 ብር ጀምሮ እስከ ስድስትና ሰባት ሺህ ብር ዋጋ የወጣላቸው መነፅሮች ለገበያ የሚቀርቡበት ሥፍራም ነው፡፡ ያለ ሃኪም ትዕዛዝ በግምትና በውበታቸው ብቻ እየተገዙ በጥቅም ላይ የሚውሉት እነዚህ የዓይን መነፅሮች ግን ለከፋ የጤና ችግር ሊዳርጉና ለአይነስውርነትም ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡
ለመሆኑ መነፅር ማድረግ የሚያስፈልገን መቼ ነው? ምን ዓይነት መነፅርስ ነው የምናደርገው? ለአቧራና ለፀሐይ መከላከያ እየተባሉ ያለ ሃኪም ትዕዛዝ ከየገበያውና ከየሱቁ እየተገዙ ጥቅም ላይ የሚውሉት መነፅሮች የሚያስከትሉት የጤና ችግር ምንድነው? አንድ ሰው የእይታ ችግር ገጥሞታል የምንለው መቼ ነው? በርቀት ወይም በቅርበት የማየት ችግር ስንልስ ምን ማለታችን ነው?
በዓለም ጤና ድርጅት መመዘኛ መሰረት አንድ ሰው በሁለቱም አይኖቹ ከሶስት ሜትር ርቀት ላይ ጣት መቁጠር ካልቻለ ዓይነስውር ነው፡፡ በዓለማችን 2.3 ቢሊዮን የሚሆኑ ህዝቦች ከእይታ መድከም ጋር የተያያዘ ችግር እንዳለባቸውና ከዚህም ከፍተኛውን ቁጥር የያዙት የእስያ አገራት ህዝቦች መሆናቸውን ይኸው የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ይፋ አድርጓል፡፡ ከጥቁር ህዝቦች ይልቅ ነጮቹ፣ በፆታ ደግሞ ከወንዶች ይልቅ ሴቶቹ በርቀት ለማየት ችግር የተጋለጡ መሆናቸውንም መረጃው ጨምሮ ገልጿል፡፡
ከአመታት በፊት እዚሁ አገራችን በአስራ አንዱም ክልሎች የተደረገ ጥናትን ዋቢ አድርጐ የኢትዮጵያ ጤና ልማት መጽሔት እንደዘገበው፤ ከአጠቃላዩ የአገሪቱ ህዝብ 3.7% የሚሆነው የእይታ ችግር ያለበት ሲሆን 1.6% የሚሆነው ደግሞ አይነ ስውር ነው፡፡ አራት ሚሊዮን የሚጠጉ የአገሪቱ ህዝቦች እይታቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ በመሄድ ላይ ነው። ይህ ቁጥር በኢንፌክሽንና በድንገተኛ አደጋዎች ሳቢያ አይናቸው የታወረን ሰዎች አይጨምርም። ጥናቱ አክሎ ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረትም፤ ከአይነስውራኑ መካከል 50 በመቶ የሚደርሱት እይታቸውን ያጡት በዓይን ሞራ ግርዶሽ ሳቢያ ሲሆን 19 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ከትራኮማ ጋር ተያይዞ በሚከሰት የአይን ጠባሣ ምክንያት፣ 11 በመቶ የሚሆኑት ከመነፅር ጋር በተያያዘ በሚከሰቱ ችግሮች እንዲሁም 6 በመቶ የሚሆኑት በግላኮማ ሳቢያ የአይን ብርሃናቸውን ያጡ ናቸው፡፡
ከመነጽር ጋር በተያያዘ የእይታ ችግር ከገጠማቸው ሰዎች መካከል አብዛኛዎቹ ያለሃኪም ትዕዛዝ ከየገበያው እየገዙ በሚጠቀሟቸውና ልካቸው ባልሆነ የአይን መነጽር ሣቢያ ጉዳት የደረሰባቸውና የቅርበት ወይም የርቀት መነፅር የሚያስፈልጋቸው ሆነው ይህንን ሳያደርጉ ቀርተው አይናቸው የሰነፈባቸው ሰዎች ናቸው፡፡
የአይን እይታ መድከም በዘር የመተላለፍ እድል ያለው ሲሆን በተለይም በርቀት የማየት ችግር፣ ግላኮማና የአይን መንሸዋረር በዘር የመተላለፍ እድላቸው ከፍተኛ ነው፡፡ በአገራችን ለቅድመ ጥንቃቄ የሚደረጉ የህክምና ምርመራዎች አለመኖራቸው በርካታ በቀላል ህክምና ሊድኑ የሚችሉ የዓይን ጤና ችግሮች ወደተባባሰ ደረጃ እንዲደርሱ በማድረግ አይነስውርነት እያስከተሉ መሆናቸውን የጤና ባለሙያው ይገልፃሉ፡፡ ዶ/ር ሻረው መንግስቱ ይህንኑ ጉዳይ አስመልክተው ሲናገሩ፤ “በአገራችን ካሉና እይታቸው እየቀነሰ ከመጣ ሰዎች መካከል አብዛኛዎቹ ችግሩ እንዳለባቸው እንኳን አያውቁም። የዓይን ምርመራና ሕክምና ማድረግ በሚገባቸው ወቅት ባለማድረጋቸው ሣቢያም የእይታ አቅማቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ በመሄድ ለአይነስውርነት ያጋልጣቸዋል። የዓይን እይታ መድከም ከተለያዩ በሽታዎች ሌላ በዕድሜ ምክንያትም ሊከሰት ይችላል። በአብዛኛው ዕድሜያቸው አርባ አመት የሆናቸው ሰዎች በቅርብ የማየት ችግር የሚያጋጥማቸው ሲሆን ማንኛውም ዕድሜው ከ40 ዓመት በላይ የሆነ ጤናማ ሰው በሃኪም ተመርምሮ የሚታዘዝለትን መነፅር ማድረግ ይኖርበታል” ብለዋል፡፡
መነፅር ማድረግ አይንን የበለጠ ያደክመዋል የሚለው አጉል አስተሳሰብ መሠረተቢስ የሆነና በሣይንስ ያልተደገፈ ነው ያሉት ዶክተሩ፤ ይልቁኑም መነፅር ማድረጉ የአይን እይታ ችግሩ እንዲስተካከል የሚረዳ ከመሆኑም በላይ ያለመነፅር በሚነበብበት ወቅት የሚከሰተውን የአይን ውጥረትና የራስ ምታት ችግር ለማስቀረት በእጅጉ ጠቃሚ ነው ብለዋል፡፡
በአብዛኛው ከዕድሜ ጋር በተያያዘና ከሃኪም ትዕዛዝ ውጪ በሚደረጉ መነጽሮች ሣቢያ የሚከሰቱት የእይታ ችግሮች በሁለት እንደሚከፈሉ የገለፁት ባለሙያው፤ እነዚህም ማዮፒያ (Short sightedness) ወይንም የሩቁን አለማየትና ሃይፐርአፒያ (Long sightedness) በቅርብ ያለን ነገር ለማየት አለመቻል እንደሆኑ ጠቁመዋል፡፡
ማዮፒያ (Short sightedness) የሚባለው የእይታ ችግር የሚፈጠረው ብርሃን ወደ አይናችን ውስጥ ገብቶ ሬቲና (Retina) ከሚባለው ምስል ፈጣሪ የዓይን ክፍል ላይ ከማረፍ ይልቅ ከሬቲናው ፊትለፊት በሚያርፍበት ወቅት ነው፡፡ ይህ የእይታ ችግር ከቤተሰብ በዘር ሊወረስ የሚችል ሲሆን የደበዘዘ እይታ ባላቸው ነገሮች ውስጥ ረዘም ላለ ጊዜ መቆየት ለችግሩ መከሰት መንስኤ ሊሆን ይችላል፡፡
ሃይፐርአፒያ (long sightedness) የሚባለው የእይታ ችግር ደግሞ በቅርብ ያሉ ነገሮችን በቀላሉ ለመለየት አለመቻል ሲሆን ይህም አነስተኛ መጠን ያላቸውን ጽሑፎች ለማንበብ አለመቻልን የሚያካትት ነው፡፡ ይህ ችግር የሚከሰተው ብርሃን አይን ላይ አርፎ ምስል የሚፈጥረው ከሬቲና ላይ ሳይሆን ከጀርባው ነው፡፡ ይህ ችግር በሚያጋጥም ጊዜ ህመምተኛው የተለያዩ ምልክቶችን ሊያሳይ ይችላል፡፡
የአይን ጡንቻዎች መድከምና ራስ ምታት በተደጋጋሚ ሲከሰት ይህ ችግር እየተባባሰ መሆኑን ጠቋሚ ነው፡፡ እነዚህ ችግሮች በሚያጋጥሙ ጊዜም የዓይን ሃኪም ዘንድ በመሄድ ችግሩ ሳይባባስ በቀላሉ መፍትሔ ለማግኘት እንደሚቻልም ዶክተር ሻረው ተናግረዋል፡፡ ለዓይን እይታ መድከም ችግሮች ከሚሰጡ ህክምናዎች መካከል መነጽር፣ ኮንታክት ሌንስና የቀዶ ጥገና ህክምናዎች ዋንኞቹ መሆናቸውን የሚገልፁት ዶክተሩ፤ በዓይን ሃኪም በሚደረጉ ምርመራዎች የሚታዘዙ መነጽሮች የእይታ አቅምን ከማሳደጋቸውም በላይ ህመምተኛው ለአይን ጡንቻዎች ውጥረትና ለራስምታት እንዳይጋለጥ ያደርጉታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የአይን እይታ አቅም እየሰነፈና እየደከመ እንዳይሄድ እንደሚያደርጉት ይገልፃሉ፡፡ ያለ ምርመራና ያለ ሃኪም ትዕዛዝ የሚደረጉ የማንበቢያም ሆነ የፀሐይ መነጽሮች ከጥቅማቸው ይልቅ ጉዳታቸው እጅግ ያመዝናል ብለዋል፡፡ ሌላው ለአይን እይታ መድከም የሚደረገው ህክምና ኮንታክት ሌንስ የተባለው ነው፡፡ ይህ ህክምና በተለያዩ ምክንያቶች መነጽር ለማድረግ የማይፈልጉ ወይም የማይችሉ (እንደ ስፖርተኛ ላሉ ሰዎች) የሚደረግ ህክምና ሲሆን፤ ህክምናው ለየት ያለ ጥንቃቄና የዕለት ተዕለት ክትትልን የሚፈልግ ነው፡፡ በአይን ውስጥ እንዲገባ የሚደረገው ሌንስ በመኝታ ሰዓት እያወጡ አጽድቶ መመለስ የሚቻል ሲሆን በዚህ የማውጣትና የማስገባት ሂደት ውስጥ ህመምተኛው ከፍተኛ ጥንቃቄ ካላደረገ በቀላሉ ባክቴሪያዎች ወደ ዓይኑ ውስጥ እንዲገቡና ኢንፌክሽን እንዲፈጥሩ ሊያደርጋቸው ይችላል፡፡ ሶስተኛውና ሌላው የህክምና ዘዴ የቀዶ ጥገና ህክምና ሲሆን ይህም በኮርኒያ ላይ የሚደረግ የቀዶ ህክምና ነው። ህክምናው ከፍተኛ የገንዘብ ወጪና ልዩ ባለሙያን የሚጠይቅ የህክምና ዓይነት እንደሆነ ዶክተር ሻረው አስገንዝበዋል፡፡
በተለምዶ” ካሮት መብላት ለአይን ጥራት” እየተባለ ስለሚነገረው ብሂል ዶክተሩ ሲናገሩ፤ “ካሮት በተፈጥሮው በውስጡ በርከት ያለ የቫይታሚን ኤ ንጥረ ነገሮችን የያዘ ነው፡፡ ይህም በቫይታሚን ኤ እጥረት ምክንያት የሚከሰተውን ዳፍንት እየተባለ የሚጠራውን የአይን በሽታ ለመከላከል ያስችላል። ከዚህ በተጨማሪ የብርሃን መቀበያ (Retina) እየተባለ የሚጠራውና ለእይታ ችግር መከሰት ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያደርገው የአይናችን ክፍል በአግባቡ ሥራውን እንዲያከናውን ያደርገዋል፡፡
በአጠቃላይ የአይናችንን ጤና ለመጠበቅ በጊዜውና በአግባቡ ምርመራ ማድረግ፣ በየገበያውና በየሱቁ ያለሃኪም ትዕዛዝ እየገዛን ከምናደርጋቸው መነጽሮች መቆጠብና በሃኪም የታዘዘን መነጽር በአግባቡ ማድረግ ይኖርብናል፡፡ “ማንኛውም ዕድሜው ከ40 ዓመት በላይ የሆነው ሰው የሃኪም ምርመራ በማድረግ የሚታዘዝለትን መነጽር ማድረግ ይገባዋል፡፡ መነጽር አለማድረግ ከዕድሜ ጋር በተያያዘ የሚከሰተውን የአይን እይታ መስነፍ ያባብሰዋል እንጂ አያስቀረውም፡፡” ሲሉም ዶክተሩ አስገንዝበዋል፡፡  

Read 10220 times