Monday, 06 October 2014 07:35

የኦባማ ደህንነቶች በ“የቅሌት ማዕበል” እና የኢትዮጵያ ኤምባሲ በ“ዳያስፖራ አምባጓሮ”

Written by  ዮሃንስ ሰ.
Rate this item
(18 votes)

የኦባማ ደህንነቶችና የኢትዮጵያ ኤምባሲ ምን አገናኛቸው? በደንብ ይገናኛሉ። የኦባማ ደህንነቶች፣ የሰሞኑ ዋነኛየአለማቀፍ ዜናዎች ርዕስ ሆነው ሰንብተዋል። ከ15 ቀናት በፊት፣ ኦማር ጎንዛሌዝ የተባለ የቀድሞ ወታደር የኋይት ሃውስን አጥር ጥሶ ከገባ በኋላ፤ በየእለቱ አዳዲስ “የቅሌት መረጃዎች” ሲወጡ ሰንብተዋል።የዜናዎቹ ብዛትና ፍጥነት ሲታይ፣ በጥቅሉ “የዜና ማዕበል”ብንላቸው ይሻላል። ማዕበሉ ከጣራ በላይ የመጠቀው ረቡዕ እለት የደህንነቶቹ ዋና ሃላፊ ከስልጣን ሲሰናበቱ ነው። በማግስቱ ከዜና ተርታ ወጣ፤ ፀጥ ረጭ አለ።በሌላ በኩል፣ ከኋይት ሃውስ በ7 ኪሎሜትር ርቀት በኢትዮጵያ ኤምባሲ ሰኞ እለት ገዢውን ፓርቲ ከሚቃወሙ ዳያስፖራዎች ጋር በተከሰተው አምባጓሮ ዙሪያ፣ አለማቀፍ የሚዲያ ተቋማት አልዘገቡትም - ከሮይተርስ ብጣሽ ዜና በስተቀር። በአምባጓሮው ላይ ሽጉጥ የተኮሰ የኤምባሲው ሰራተኛ፣ ያለመከሰስ መብቱን ተጠቅሞ ወደ ኢትዮጵያ እንደተመለሰ የዘገበ አለማቀፍ ሚዲያ የለም። “ነገሬ” አላሉትም።
በዚህ በዚህ፣ ሁለቱም ክስተቶች አንዳችም ዝምድና የላቸውም ማለት ይቻላል። ግን ደግሞ፤ በግድ ልናዛምዳቸው እንችላለን። የፕሬዚዳንት ኦባማን እና የኋይት ሃውስን ደህንነት የመጠበቅ ስልጣን የተሰጠው Secret Service የተሰኘው የፀጥታ ተቋም፤ በአሜሪካ የሚገኙ ኤምባሲዎችን ደህንነት የመጠበቅ ሃላፊነትም አለበት። በኢትዮጵያ ኤምባሲ ዙሪያ የተከሰተውን አምባጓሮ ለማጣራት ወደ ቦታው የመጡትም፣ የዚሁ ተቋም ሰራተኞች ናቸው - የኋይት ሃውስ (የአሜሪካ ቤተመንግስት) ደህንነቶችና የፀጥታ ሰራተኞች።
በእርግጥ፣ በአምባጓሮው ሰበብ በሰው ላይ የደረሰ ጉዳት የለም። ኢህአዴግን ለመቃወም የመጡት ዳያስፖራዎች ከኤምባሲው ሰራተኞች ጋር ከተፋጠጡ በኋላ ነው፣“ወደ ኤምባሲው እንገባለን፤ አትገቡም” የሚል አምባጓሮ የተፈጠረው። አንድ የኤምባሲው ሰራተኛ ሽጉጥ ወደ ላይ ተኩሷል፤ የተወሰኑ ተቃዋሚዎች ደግሞ ወደ ግቢው ገብተው ባንዴራ አውርደዋል። የአምባጓሮው አጭር ታሪክ ይህን ይመስላል። አምባጓሮውን ለማጣራት የአሜሪካ Secret Service መምጣቱ ሳይዘነጋ ማለት ነው።
በነገራችን ላይ፣ ስያሜው ከሚኒሊክ ዘመን በኋላ በኢትዮጵያ ከነበረው “የሚስጥር ፖሊስ” ከሚለው ስያሜ ጋር ይቀራረባል። ግን ማንነታቸውም ሆነ ስራቸው፣ “ሚስጥር” አይደለም። ቆባቸው ላይ “የሚስጥር ፖሊስ” የሚል ፅሁፍ እየታየ፤ እንዴት “ሚስጥር” ይሆናሉ? የአሜሪካ ፕሬዚዳንትንና ምክትላቸውን ከነቤተሰባቸው፣ የቀድሞ ፕሬዚዳንቶችንና ቤተሰቦችን፣ እንዲሁም ለጉብኝት የሚመጡ የሌላ አገር መሪዎችንና ኤምባሲዎችን ደህንነት የመጠበቅ ስልጣን የተሰጠው Secret Service የተሰኘው ተቋም፣ ድብቅ ሚስጥር አይደለም።
በኋይት ሃውስ ግቢ ውስጥና በዙሪያው ዩኒፎርም ለብሰው ጥበቃ ሲያካሂዱ እያየን “ሚስጥራዊ” ልንላቸው አንችልም። ሙሉ ሱፍ ከነከረቫቱ ለብሰው፣ ጥቁር መነፅር አጥልቀው፣ ፕሬዚዳንት ኦባማን ከግራና ከቀኝ፣ ከፊትና ከኋላ አጅበው ዙሪያቸውን ሲቃኙ የምናያቸው ረዣዥም ሰዎችም፣ የተቋሙሰራተኞች ናቸው - በአሜሪካ ብቻ ሳይሆን በአለም ወደር የለሽ እንደሆኑ የሚነገርላቸው የፀጥታ ባለሙያዎች።
በ1.5 ቢሊዮን ዶላር አመታዊ በጀት የሚንቀሳቀሰው ኤጀንሲም እንዲሁ፤ በአለም አቻ የለውም የሚባልለት ዝነኛ የፀጥታ ጥበቃ ተቋም ነው - “ሚስጥራዊ” ሳይሆን “ዝነኛ”። ባለፉት ሁለት ሳምንታት ግን፣ የተቋሙ ዝና ተዋርዶ አፈር ለአፈር ሲጎተት ሰንብቷል - “የተቋሙን ጉድ” እየፈለፈሉ የሚያወጡ ጋዜጠኞች በሚዘግቡት እንደ ናዳ ፋታ የማይሰጥ፣ እንደ ማዕበል አገር ምድሩን የሚያዳርስ የዜና ስርጭት።
የናዳው እና የማዕበሉ መነሻ፣ ከሁለት ሳምንት በፊት የ44 አመቱ ጎንዛሌዝ አጥር ጥሶ ወደ ዋይት ሃውስ መግባቱ ነው። ለአስር ቀናት የዘለቀው ማዕበል፣ የኤጀንሲው ዳሬክተር ኋይት ሃውስን ለቅቀው ሲወጡ ተጠናቋል። ለ30 አመታት በተቋሙ ውስጥ የሰሩት ዳሬክተሯ ጁሊያ ፒርሰን፣ የጎንዛሌዝ መዘዝ እዚህ ደረጃ ላይ ይደርሳል ብለው አልጠበቁም ነበር - ስልጣን እስከለቀቁበት ዋዜማ ድረስ። እንዲያውም፣ የጎንዛሌዝ ነገር ተድበስብሶ ይቀራል በሚል ግምት፣ ክስተቱን በዚያው እለት ለፕሬዚዳንቱ ሪፖርት አላደረጉም።ግን ጋዜጦች ጉድ አደረጓቸው። ዳሬክተሯ መረጃዎችን ለመደበቅ ሲሞክሩ፣ ጋዜጠኞች መረጃ እየፈለፈሉ ሲያወጡ ከሰነበቱ በኋላ ነው፤ ነገሩ ግልፅ እየሆነ የመጣው። የአእምሮ ህመምተኛው ጎንዛሌዝ፣ ለካ አጥር ከመዝለልም አልፎ ሕንፃ ውስጥ ገብቷል። ለካ፣ ሕንፃው ውስጥ እንደገባ ወዲያው አልተያዘም። በፕሬዚዳንቱ መኝታ ቤት ስር አልፎ፣ የመሰብሰቢያ አዳራሽና የእንግዳ መቀበያ ክፍሎች ድረስ ዘልቋል... እንዲህ ከእለት እለት መረጃው እየጨመረ ሲመጣ፣ ከዚሁ ጋር አብሮ የቀድሞ “ስህተቶች” እና “ቅሌቶችም” በየእለቱ ሲዘገቡ ሰንብተዋል። ዋና ዋናዎቹን ልጥቀስላችሁ።
በታይላን ከአውሮፕላን የጠፋው የፀጥታ ሰራተኛ
በ2009 ለባራክ ኦባማ የደቡብ ኮሪያ ጉብኝት ዝግጅት እንዲያደርጉ የተመደቡ 70 የተቋሙ የፀጥታ ሰራተኞች፣እግረመንገዳቸውን ወደ ታይላንድ ጎራ ብለው ነበር - ዘና ለማለት። ነገር ግን፣ኦባማ ደቡብ ኮሪያ ከመግባታቸው በፊት የፀጥታ ሰራተኞች ቀድመውመድረስ አለባቸው። ችግሩ፣ አውሮፕላናቸው ጊዜ መብረር አልቻለም። አንድ የፀጥታ ሰራተኛ የት እንደገባ ሳይታወቅ ጠፍቷል። የሰራተኞቹ ተቆጣጣሪ ቢጨንቃቸው፣ ሌሎቹን ሰራተኞች ወደ ደቡብ ኮሪያ ሸኝተው የጠፋውን በግ ፍለጋ የታይላንድ ጎዳናዎችን ለማሰስ ወሰኑ።
ደግነቱ ጊዜ አልፈጀባቸውም፤ የጠፋውን የፀጥታ ሰራተኛ ወዲያውኑ አግኝተውታል። የት? የሴተኛ አዳሪዎች መንደር ውስጥ።በዚያ ላይ፣ ሲጠጣ አምሽቶ ገና ስካር አልለቀቀውም። በመንገደኞች አውሮፕላን ወደ አሜሪካ እንዲመለስ ተደረገ። ምናልባት፣የአንድ ሰራተኛ ጥፋት እንደትልቅ ቅሌት ተጋንኖ መታየት የለበትም ሊባል ይችላል። ነገር ግን፣ ጥፋት የፈፀመው ሰራተኛ አለመቀጣቱ አስገራሚ ነው ብሏል ኤምኤስኤንቢሲ።
ኋይት ሃውስ ላይ የክላሽ እሩምታ
ከሁሉም የከፋ ቅሌት የተከሰተው፤ የዛሬ ሶስት አመት ገደማ ነው። ከኋይት ሐውስ በግማሽ ኪሎሜትር ርቀት የቆመ መኪና ውስጥ የነበረ ሰው፣ የፕሬዚዳንቱ ቤተሰብ መኖሪያ በሆነው የሕንፃው አንደኛ ፎቅ ላይ ሰባት ጥይቶችን አርከፍክፏል።የተኩስ ድምፅ ተሰምቷል፤ የመስተዋት መሰበርና መሰንጠቅ ድምፆችም እንዲሁ። ነገር ግን፣ ኋይት ሐውስ ሰባት ጥይቶች እንደዘነቡበት የታወቀው ከአራት ቀን በኋላ ነው።
ለወትሮው ተኳሹ የነበረበት ቦታ፣ በቤተመንግስት የፀጥታ ሰራተኞች ጥበቃ የሚደረግለት ቦታ ነው። በተለይ ፕሬዚዳንቱ በሄሊኮፕተር ከኋይትሃውስ ሲነሱ ወይም ሲመለሱ፣ በዙሪያው የፀጥታ ሰራተኞቹ ይመደባሉ። ግን ሁልጊዜ አይደለም። አንዳንዴ የፀጥታ ሰራተኞቹ አላግባብ ወደ ሌላ ቦታ እንዲሄዱ ይታዘዛሉ በማለት ዋሺንግተን ፖስት ዘግቧል -የዛሬ ሶስት አመት የተከሰተውን አጋጣሚ በምሳሌነት በመጥቀስ።
የጎረቤት ሽምግልና - የትርፍ ሰዓት ስራ
በቦታው ተመድበው የነበሩ ሁለት የፀጥታ ሰራተኞች፣ ትዕዛዝ የደረሳቸው ከዋና አለቃቸው ነው - የፀጥታ ተቋሙ ዋና ዳሬክተር ከነበሩት ማርክ ሱሊቫን።ለዚያውም ፕሬዚዳንቱ በሄሊኮፕተር ለመነሳት በተቃረቡበት ሰዓት ላይ ነው፤ ሁለቱ የፀጥታ ሰራተኞች የተመደቡበትን የጥበቃ ቦታ ትተው ወደ ሜሪላንድ እንዲሄዱ የታዘዙት። ለምን? የዳሬክተር ሱሊቫን አንዲት ረዳት በሜሪላንድ መኖሪያ ቤቷ ከጎረቤት ጋር ጭቅጭቅ ስለተፈጠረባት።
መደበኛ የፕሬዚዳንት ጥበቃቸውን ትተው፣ የጎረቤት ጭቅጭቅ እንዲሸመግሉ በመመደባቸው የተናደዱትየፀጥታ ሰራተኞች፣ሜሪላንድ ለመድረስ አንድ ሰዓት ፈጅቶባቸዋል። የሽምግልና ስራውንም፤ “ሙንላይት ኦፕሬሽን” ሲሉ በራሳቸው ላይ ቀልደዋል - የትርፍ ሰዓት ተልእኮ እንደማለት ነው።
ከሆቴል አስተናጋጆች ጋር ፍጥጫ
ግንቦት 2013 ሌላየ“ቅሌት” አጋጣሚ የተፈጠረው፤ ከዋሺንግተን ስመጥር ሆቴሎች አንዱ በሆነው ሄይ-አዳምስ ሆቴል። የአንዲት ሴት ክፍል ውስጥ ለመግባት የፈለገ አንድ የፀጥታ ተቋሙ ሰራተኛ፤ “አትገባም” ተብሎ ስለተከለከለ ከሆቴሉ አስተናጋጆች ጋር ውዝግብ ጀምሯል።ኢኚያኮ ዛሞራ ይባላል። በስልጣን አስፈራርቶ ወይም ጉልበት ተጠቅሞ መግባት አይችልም። እንደማያዋጣው ያውቃል። የሆቴሉ አስተናጋጆችና ሃላፊዎች ደግሞ ሊያስገቡት ፈቃደኛ አልሆኑም። ምክንያቱም፣ ሆቴሉ ውስጥ ያረፈችው ሴት፣ ፈቃደኛ እንዳልሆነች ነግራቸዋለች።
ከፀጥታ ተቋሙ ዋና ዋና ሃላፊዎች መካከል አንዱ እንደሆነ ቢያውቁ እንኳ እሺ አይሉትም። የትኛውም ስልጣን ቢኖረው፣ ህግ እየጣሰ በሰዎች ንብረት ላይ እንዳሻው መሆን አይችልም። የሆቴሉ ሃላፊዎች ቢቸግራቸው፣ ወደ ኋይትሃውስ ስልክ ደውለው ችግራቸውን ገለፁ። እንዲያም ሆኖ፣ ዛሞራ መናገሩን አላቋረጠም - “ልግባ አላልኩም፤ ተመልሼ ልግባ ነው ያልኩት። አሁን ነው የወጣሁት። ለአፍታ ተመልሼ ልግባና እወጣለሁ” ይላል እየደጋገመ።
በእርግጥም፣ ዛሞራበሆቴሉ ካረፈችው ሴት ጋር ክፍሏ ውስጥ ቆይቶ ነው የወጣው። ግን ተመልሶ መግባት አለበት። ለምን? ክፍሏ ውስጥ አንድ ጥይት ረስቷል። በመንግስት ተመዝግቦ የተሰጠውን ጥይት ትቶ መሄድ አይችልም። በዚያ ጥይት አንዳች ወንጀል ቢፈፀም፣ በዘመኑ የምርመራ ቴክኖሎጂ የጥይቱ ምንጭ ተጣርቶ መዘዙ ዞሮ ይመጣበታል። በዚያ ላይ፣ ዛሞራ ተራ የፀጥታ ሠራተኛ አይደለም። የፕሬዚዳንቱ ደህንነት ለመጠበቅ በቋሚነት ከተመደቡ ልዩ የፀጥታ ተቋሙ ሰራተኞች አንዱ ነው - ዛሞራ። ይህም ብቻ አይደለም። 24 የፕሬዚዳንት የግል ጠባቂዎችን የሚመራ ተቆጣጣሪ ነው። የኋላ ኋላ፣ ሆቴል ውስጥ የረሳውን ጥይት መልሶ ማግኘቱ አልቀረም። ነገር ግን፣ ከችግር አላመለጠም። ምርመራ ተካሂዶበት፣ ከሃላፊነቱ ተነስቷል፤ ከፕሬዚዳንቱ የግል ጥበቃ ቡድንም እንዲወጣ ተደርጓል።
ታላቁ የኮሎምቢያ ቅሌት - ከሴተኛ አዳሪዎች ጋር ውዝግብ
በፀጥታ ሰራተኞች ላይ ምርመራ መካሄዱ አዲስ ነገር አይደለም። የዛሬን አያድርገውና የዛሬ ሁለት አመት፣ ኢኚያኮ ዛሞራ በመርማሪነት ተመድቦ ነበር - ለዚያውም በታላቁ የኮሎምቢያ ቅሌት ላይ -በርካታ የፀጥታ ተቋሙ ሰራተኞችንና የኮሎምቢያ ሴተኛአዳሪዎችንያዳረሰ ታላቅ ቅሌት። ነገሩ እንዲህ ነው። ፕሬዚዳንት ኦባማ ለጉብኝት ኮሎምቢያ ከመድረሳቸው በፊት ቀድመው የገቡ በርካታ የፀጥታ (ሰክሬት ሰርቪስ) ሰራተኞች፣ ከስንት ጊዜ አንዴ በሚያገኟት ትንሽ ትርፍ ጊዜ መዝናናት ቢያምራቸው አይገርምም። በፀጥታና በምርመራ ሙያ አንቱ የተባሉ ሰዎች፣ አሰልቺ ሥራ ላይ አመታትን ሲያስቆጥሩ አስቡት። አንዳንዶቹኮ ከሲአይኤ እና ከኤፍቢአይ ውስጥ በላቀ ችሎታ ነው ወደ ሰክሬት ሰርቪስ የሚገቡት። አብዛኛውን ጊዜ የሚያሳልፉት ግን፣ የቤተመንግስትን ግቢ ወይም የስብሰባ አዳራሾችን ለመጠበቅ ቆመው በመዋል ነው።
እንዲህ በአሰልቺው ስራ የተንገፈገፉ 12 ያህል የፀጥታሰራተኞች ናቸው፣ኮሎምቢያ ውስጥየእርቃን ዳንስ ወደሚታይበት ሰፈር ወርደው ሲጨፍሩና ሲጠጡ ያመሹት። በመጨረሻም ወደ ሆቴላቸው ባዶ እጃቸውን አልተመለሱም። ሴተኛ አዳሪዎችን ይዘዋል። ነገሩ በዚህ ቢደመደም ኖሮ፣ አገር ምድሩን ያዳረሰ ቅሌት ለመሆን ባልበቃ ነበር። በእርግጥ ለፕሬዚዳንት ጥበቃ የተመደቡ የፀጥታ ሰራተኞችና ረዳቶች፣ በስራ ዋዜማ አለቅጥ መጠጣትም ሆነ የውጭ ዜጎችን ወደ ሆቴላቸው ይዘው መምጣት አይፈለቀድላቸውም። እናም፤ ከምርመራና ከዲሲፕሊን ቅጣት አይድኑም ነበር። ትልቅ ችግር የተፈጠረው፣ በዚያ “እብደት” ማግስት ነው። ከሴተኛ አዳሪዎች ጋር የክፍያ ጭቅጭቅ ተፈጠረ። ያው፤ አንዳንድ ሴተኛ አዳሪዎች በአተካራ የሚችላቸው የለም። ሆቴሉን በጭቅጭቅና በስድብ ቀውጢ አደረጉት። ብዙም አልቆየም፤ አለምን የሚያነጋግር ትልቅ ቅሌት ሆኖ አረፈው።ሬቸል ማደው እንደምትለው ግን ይሄ ሁሉ የአጋጣሚ ጉዳይ አይደለም። የቤተመንግስትን ፀጥታና የፕሬዚዳንቱን ደህንነትየመጠበቅ ሃላፊነት የተሰጠው ተቋም፤ ከቅርብ አመታት ወዲህ ስህተትና ቅሌት እየተደራረበበት መጥቷል።ባለፉት አስራ ሁለት ወራት ደግሞ ብሶበታል ትላለች ሬቸል ማደው - የፕሬዚዳንት ኦባማ የደቡብ አፍሪካ ጉብኝትን በመጥቀስ።
ከኦባማ አጠገብ፤ ኮሜዲያን ወይም ወንጀለኛ?
ለኔልሰን ማንዴላ ስርዓተ ቀብር ወደ ደቡብ አፍሪካ የተጓዙት ፕሬዚዳንት ኦባማ፣ በህዝብ የተሞላ ስታዲዬም ውስጥ፣ ከበርካታ አገራት መሪዎች መካከል ጎልተው፣ መላው አለም በሚከታተለው ቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት፣ ሃዘናቸውን ለመግለፅ መድረክ ላይ ወጥተዋል። መድረኩ ጥይት በማይበሳው መስተዋት የተከለለ ነው። ከፕሬዚዳንቱ አጠገብ፣ ንግግራቸውን በምልክት ቋንቋ ለመተርጎም የተመደበ ግዙፍ ሰው እጆቹን ግራና ቀኝ፣ ላይና ታች ሲያንቀሳቅስ ይታያል። አስገራሚው ነገር፣ ሰውዬው የፕሬዚዳንቱን ንግግር በምልክት ቋንቋ እየተረጎመ አልነበረም። የእጆቹ እንቅስቃሴ እስከነአካቴው ትርጉም አልነበራቸውም።
ማንዴላን በመሰለ ታላቅ ሰው ቀብር ላይ፣ አሜሪካን ከመሰለ ታላቅ አገር የመጣ ፕሬዚዳንት በሚናገርበት መድረክ፣ እንዲህ አይነት “አስቂኝ” ነገር መፈጠሩ ብዙዎችን ማስቆጣቱና ማሳዘኑ አያጠራጥርም። ምን ይሄ ብቻ! የኋላ ኋላ ሲጣራ፣ ለካ ሰውዬው የአእምሮ ህመምተኛ ነው። በዚያ ላይ፣ ከሶስት ቀን በኋላ ኤንፒአር እንደዘገበው፣ ሰውዬው በግድያ ወንጀል የተጠረጠረ ተከሳሽ ነው። እናም፤ ጥይት በማይበሳው መስተዋት ውስጥ ከፕሬዚዳንቱ አጠገብ ቆሟል። የፕሬዚዳንቱን ደህንነት የሚጠብቁ የፀጥታ ሰራተኞች እያንዳንዷን ነገር ማጣራት ሲኖርባቸው፤ ይህንን እንዴት አለፉት? ለማጣራትና እርምጃ ለመውሰድ ቢሞክሩ፤ “አሜሪካዊያን ወደ አፍሪካ መጥተው አዛዥ ናዛዥ መሆን ያምራቸዋል” የሚል የትችት ውርጅብኝ እንዳይደርስባቸው ሰግተው ይሆን?
ለማንኛውም፤ ከጥቂት ወራት በኋላ መጋቢት ላይ፣ ፕሬዚዳንት ኦባማ ኔዘርላንድን ሲጎበኙ፤ እንደገና የፀጥታ ሰራተኞች የዜና ርዕስ ሆነዋል - ሶስት የፀጥታ ሰራተኞች እስከ ጥግ ሰክረው ስለተገኙ፣ ከስራ መታገዳቸውን ዋሺንግተን ፖስት ተዘግቧል።እንደ ዋሺንግተን ፖስት የመሳሰሉ የአሜሪካ ጋዜጦች፣ አንድ ሁለቴ የሆነ ስህተትና እንከን ካዩ፣ መች ይለቃሉ? የፀጥታ ጥበቃ ኤጀንሲው ላይ ቅሌት እየተደራረበ የመጣበት አንዱ ምክንያትም፤ የጋዜጠኞች ክትትል ስለተበራከተ ሊሆን ይችላል።እውነትም፣ የግንቦት ወር ሌላ ቅሌት ይዞ መጣ።
ሰተት ብሎ ወደ ኋይት ሃውስ
የፕሬዚዳንት ኦባማ ልጅ በመኪና ከፀጥታ ሰራተኞች ጋር በመኪና ወደ ኋይትሃውስ ስትጓዝ፣ ከበስተኋላ ሌላ መኪና እየተከተላቸው ነበር። የፀጥታ ሰራተኞች ይህንን “የአደጋ ምልክት” ሳያስተውሉ ነው፤ የኋይትሃውስ በር ላይ የደረሱት። በር ተከፍቶላቸው ገቡ፤ ከኋላ ሲከተላቸው የነበረው መኪናም አብሯቸው ገባ። በእርግጥ ምንም አደጋ አልደረሰም። ሰውዬው፣ መንገድ ጠፍቶበት ነው፣ “በደመነፍስ” ከፊት ለፊቱ የነበሩ መኪኖችን ተከትሎ እየነዳ የመጣው። ነገር ግን፤ የፀጥታ ሰራተኞች እንዴት አላስቆሙትም? የፀጥታ ጥበቃ ላይ አንዳች ችግር አለ ማለት ነው። ችግር በመኖሩም ነው፤ የዛሬ ሁለት ሳምንት፣ ኦማር ጎንዛሌዝ የኋይትሃውስ አጥር በመዝለል ሰፊውን መስክ በማቋረጥ ወደ ህንፃው ለመሮጥ የቻለው።
በእርግጥ ማንም ቢሆን፣ በአጥር ዘልሎ ሲገባ፣ የቤተመንግስት ፀጥታ ሰራተኞች ተኩሰው ሊገድሉት አይችሉም። አይፈቀድም። የቀድሞ ሃላፊዎች እንደተናገሩት፣ የቤተመንግስት ፀጥታ ሰራተኞች ከፖሊስ የተለየ የሃይል አጠቃቀም መመሪያ የላቸውም። በአጥር የዘለለ ሰው፣ የጦር መሳሪያ ካልያዘና በሰው ህይወት ላይ አጣዳፊ አደጋ ካልደቀነ በቀር፣ የፀጥታ ሰራተኞች የጦር መሳሪያ እንዲጠቀሙ አይፈቀድላቸውም።የተቋሙ ሃላፊዎች በሰጡት የመጀመሪያ መግለጫም፤ “አጥር ጥሶ የገባውጎንዛሌዝ፣ የጦር መሳሪያ አልያዘም”ብለውነበር።የኤጀንሲው ሃላፊዎች ጉዳዩ በዚሁ እንደሚቋጭ ሳይገምቱ አልቀረም። ለነገሩማ፣ ከመነሻው በሚዲያ ተቋማት እስከነጭራሹ ጉዳዩን ላያውቁትና ላይዘግቡት ይችላሉ የሚል እምነት ነበራቸው። ለዚህም ነው የኤጀንሲው ሃላፊ ጁሊያ ፒርሰን፣ በአጥር ዘሎ የገባ ሰው፣ እስከ ህንፃው በር ድረስ መቻሉን፣ ለፕሬዚዳንቱ ሪፖርት ሳያቀርቡ ለመደበቅ የሞከሩት።
ግን ጉዳዩ በአጭሩ አልተቋጨም። የአሜሪካ ጋዜጦች ተጨማሪ መረጃዎችን ፈልፍለው ማውጣት ጀመሩ። “ሰውዬው ጩቤ ይዞ ነበር” የሚል መረጃ የመጣው በማግስቱ ነው። በሁለተኛው ቀን ደግሞ ሌላ መረጃ - የሰውዬው መኪና ውስጥ፣ 800 ጥይቶች ተገኝተዋል የሚል መረጃ። የተቋሙ ሃላፊዎች፣ መረጃ ለመደበቅ መሞከራቸው አልጠቀማቸውም።የጋዜጠኞች ዘገባ እንደ አሸን እየፈላ፣ የተቋሙ ሃላፊዎችበፍጥነት እንደሚወርድናዳ ቅሌት እየተደራረበባቸው ሲመጣ ማየት፣ ልብ አንጠልጣይ ድራማ ከማየት አይለይም።ጎንዛሌዝአጥር ከመጣስ አልፎ፣ ወደ ህንፃው ገብቶ እንደነበር ጋዜጠኞች መረጃ ያገኙትና የዘገቡት፣ ከሶስት ቀን በኋላ ነው። የተቋሙ ሃላፊዎች ይህንን መካል አልቻሉም። ግን ተጨማሪ መረጃ ለመስጠት አልፈቀዱም።
ሳምንት አልቆየም፤ ጋዜጠኞች ሌላ መረጃ ፈልፍለው አገኙ። ጎንዛሌዝ፣ ያልተቆለፈውን በር ከፍቶ ወደ ህንፃው ከገባ በኋላ አንዲት የፀጥታ ሰራተኛ ልታስቆመው ስትሞክር መትቶ ጥሏታል። ኮሪደር አቋርጦ፣ ወደ ምስራቅ አቅጣጫ ታጥፎ ዋና የመሰብሰቢያ አዳራሽ በር ላይ ሲደርስ ነው የፀጥታ ሰራተኛ በቁጥጥር ስር ያዋለው...በጋዜጠኞች የሚዘገበው አዲስ መረጃ ፋታ የሚሰጥ አልነበረም። ናዳውን መቋቋም ያቃታቸው የኤጀንሲው ሃላፊዎች፣ ከሌላ አቅጣጫም ተጨማሪ ናዳ ሲወርድባቸው ሰንብቷል - በአገሪቱ ኮንግረስ (ፓርላማ)።
በጉዳዩ ላይ ምርመራ የጀመረው የኮንግረስ ኮሚቴ፣ ማክሰኞ እለት የኤጀንሲውን ሃላፊዎች ጠርቶ ቃላቸውን ሲቀበልና በጥያቄ ሲያፋጥጥ ውሏል። የኤጀንሲው ሃላፊዎች ለኮንግረስ ቃል በሚሰጡበት እለት ነው፣ ዋሺንግተን ፖስት አዲስ ዘገባ ይዞ የወጣው። ሕንፃው ውስጥ ጎንዛሌዝ በቁጥጥር ስር የዋለው፣ ለጥበቃ በተመደበ የፀጥታ ሰራተኛ አይደለም። እረፍት የወጣና እንደአጋጣሚ ለሌላ ጉዳይ እዚያ አካባቢ የነበረ የፀጥታ ሰራተኛ ነው ጎንዛሌዝን የያዘው። ይህም ብቻ አይደለም።ከጎንዛሌዝ የአጥር ዝላይ በፊት ሶስት ቀን ቀደም ብሎ፣ ባራክ ኦባማ የኤሜሪካ የበሽታ ቁጥጥር መስሪያ ቤትን ሲጎበኙ የፀጥታ ሰራተኞች ሌላ ስህተት ፈፅመዋል - አንድ የመስሪያ ቤቱ የኮንትራት ሰራተኛ ከፕሬዚዳንቱ ጋር ሊፍት ውስጥ እንዲገባ በመፍቀድ። በጣም አስገራሚው ነገር፣ ሰውዬው ሽጉጥ ታጥቆ ነበር። እነዚህ መረጃዎች ማክሰኞ እለት በዋሺንግተን ፖስት ሲዘገቡ ነው፤ ማዕበሉ ከጣራ በላይ የወጣው። ዳሬክተሯ ስልጣናቸውን ለቀቁ። በአንድ ቀን በኋላ ደግሞ፤ የዜና ማዕበሉ ሙሉ ለሙሉ ጠፋ።

Read 7046 times