Saturday, 30 August 2014 10:31

ማየትና መስማት የተሳናት ትውልደ ኢትዮጵያዊት ታዋቂውን የአሜሪካ ኩባንያ ከሰሰች

Written by 
Rate this item
(0 votes)

          ከሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ በህግ ሙያ የተመረቀችውና በአሜሪካ በአካል ጉዳተኞች መብት ተሟጋችነት በመስራት ላይ የምትገኘው፣ ማየትና መስማት የተሳናት ትውልደ ኢትዮጵያዊት የህግ ጠበቃ ሃቤን ግርማ፣ በአካል ጉዳተኞች ላይ መድልኦ ይፈጽማል ስትል ስክሪፕድ የተባለውን ታዋቂ የአሜሪካ የድረገጽ ኩባንያ መክሰሷ ተዘገበ፡፡ ቢዝነስ ኢንሳይደር ድረገጽ ባለፈው ሳምንት እንደዘገበው፤ ዲጂታል መረጃዎችን ለአንባብያን በስፋት በማቅረብ የሚታወቀው ስክሪፕድ የተባለው ኩባንያ፣ የሚከተለው አሰራር ማየት የተሳናቸው አንባቢዎችን ፍላጎት ያላሟላና መድልኦ የሚፈጥር ነው በማለት ነው ሃቤን በኩባንያው ላይ ክስ የመሰረተችው፡፡ የ26 አመቷ ጠበቃ ሃቤን ግርማ፤ ‘ናሽናል ፌደሬሽን ኦፍ ዘ ብላይንድ’ እና ‘ብላይንድ ቬርሞንት ማዘር ሄዲ ቪነስ’ የተባሉትን የአሜሪካ የአይነስውራን መብቶች ተሟጋች ተቋማት በመወከል በስክሪፕድ ላይ በመሰረተችው ክስ፣ ኩባንያው የድረገጽ አገልግሎቶቹ ሆን ብሎ ለአይነስውራን አንባብያን ተደራሽ እንዳይሆኑ በማድረግ፣ የአገሪቱን የአካል ጉዳተኞች ህግ በሚጥስ መልኩ ያልተገባ ድርጊት ፈጽሟል ብላለች፡፡

ስክሪፕድ ከ40 ሚሊዮን በላይ በሚሆኑ የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ያጠናከራቸውን መረጃዎች በድረገጹና በአፕሊኪሽኖቹ አማካይነት ለደንበኞቹ 8 ነጥብ 99 የአሜሪካ ዶላር ወርሃዊ ክፍያ በማስከፈል የሚያሰራጭ ሲሆን በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ የሚጽፉ ደንበኞቹን ስራዎች በድረገጽ አማካይነት ታትመው ለንባብ እንዲበቁ በማድረግ፣ በአለማቀፍ ዙሪያ ሰፊ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ የሚገኝ ኩባንያ መሆኑን ዘገባው ጨምሮ ገልጧል፡፡ስትወለድ ጀምሮ ማየትና መስማት የተሳናት ሃቤን፤ ትምህርቷን የተከታተለችው በአሜሪካ ሲሆን የመጀመሪያ ዲግሪዋን ከሊዊስ ኤንድ ክላርክ ኮሌጅ ተቀብላለች፡፡ ከሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲም በህግ የሁለተኛ ዲግሪ ይዛለች፡፡ በአሁኑ ወቅትም በበርክሌይ የአካል ጉዳተኝነት መብት ተሟጋች ጠበቃ በመሆን እያገለገለች ትገኛለች፡፡የቢዝነስ ኢንሳይደር ድረገጽ ‘የ2013 እጅግ አስደማሚ 20 ምርጥ የሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች’ በሚል ባለፈው አመት ከመረጣቸው ተጠቃሽ ተማሪዎች መካከል ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ሃቤን ግርማ አንዷ እንደነበረች ዘገባው አስታውሷል፡፡

Read 3338 times