Saturday, 23 August 2014 11:42

ዓለም አቀፍ የሰላም ጉባኤ በደቡብ ኮሪያ ይካሄዳል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ከ162 አገራት ‘ከግጭት ነጻ’ የሆኑት 11 ብቻ ናቸው ተባለ

ግጭት ባሉባቸው የዓለም አካባቢዎች ጦርነትን የማስቆምና ዓለምን ሁሉም ሰው ያለስቃይና ያለጦርነት ፍርሃት የሚኖርባት ሰላማዊ ስፍራ የማድረግ ዓላማ ያለው ዓለምአቀፍ የሰላም ጉባኤ በመጪው መስከረም መጀመሪያ በደቡብ ኮሪያ ሴኡል ከተማ እንደሚካሄድ አዘጋጆቹ ለአዲስ አድማስ አስታወቁ፡፡
የኡራጋይ፣ የኖርዌይና የኮስታ ሪካን ፕሬዚዳንቶች ጨምሮ የተለያዩ የአለም አገራት መሪዎችና የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች እንደሚሳተፉበት የሚጠበቀውን ይህን አለማቀፍ የሰላም ጉባኤ የሚያዘጋጀው፣ “ሄቨንሊ ካልቸር፣ ዎርልድ ፒስ፣ ሪስቶሬሽን ኦፍ ላይት” (HWPL) የተባለ የሰላም ባህልን በማህበረሰቦችና በዓለም አቀፍ ደረጃ በማጎልበት ጦርነትን ለማስቆም የሚሰራ መንግስታዊ ያልሆነ ዓለም አቀፍ ተቋም ነው፡፡
በመላው ዓለም በሃይማኖቶች መካከል ያሉ አለመግባባቶች ትላልቅ ግጭቶችን እንዳስከተሉ ለዝግጅት ክፍላችን በላከው መግለጫ የጠቆመው ተቋሙ፤ ሰላምን ለመፍጠር አስቀድሞ በሃይማኖቶች መካከል ሰላምና መግባባት ማስፈን የሚል ተልዕኮ እንዳለው አስታውቋል። ከመላው ዓለም ከ40 አገራት የተወከሉ ተሳታፊዎች በሚገኙበት የሴኡሉ ታሪካዊ የሰላም ጉባኤ ግጭቶችን በማስቆም ላይ ያተኮሩ ውይይቶች፣ ባህላዊ ትርኢቶችና የሰላም የእግር ጉዞ እንደሚደረጉ ይጠበቃል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ በፊሊፒንስ በሃይማኖት ልዩነቶች በግጭት በምትታመሰው ዛምቦዋንጋ ከተማ ተጨባጭ የሰላም መፍትሄ ለማምጣት ያለመ ዓለም አቀፍ የሰላም ጉዞ ማካሄዱን ተቋሙ አክሎ ገልጿል። ባለፈው ነሐሴ 5 ለ3 ቀናት ተጀምሮ በተካሄደው 13ኛው የሰላም ጉዞ በዛምቦአኛ ከተማ በሚንዳናኦ ደሴት የፊሊፕንስ መንግስት ከፍተኛ አመራሮችና የሃይማኖት መሪዎችን ጨምሮ 12ሺ የሚገመት ህዝብ የተሳተፈበት የሰላም የእግር ጉዞ የተካሄደ ሲሆን 300 የፊሊፒንስ ፖሊሶች የተካፈሉበት የሰላም ፎረም መካሄዱን ተቋሙ በመግለጫው ጠቁሟል። የተቋሙ ፕሬዚዳንት ሚ/ር ሊ፤ 3ሺ ለሚደርሱ ተማሪዎች ሰላም ላይ ያተኮረ ትምህርት እንደሰጡም ለማወቅ ተችሏል፡፡ የሰላም ልኡኩ ከዚህ ቀደምም ወደ ፊሊፒንስ ተጉዞ እንደነበር ያስታወሰው ተቋሙ፤ የካቶሊክና የሙስሊም ሃይማኖት ተወካዮችን አገናኝቶ የወንድማማችነት ስምምነት በማፈራረም በሚንዳናኦ ከ40 ዓመት በላይ የዘለቀውን የሁለቱን ሃይማኖቶች ግጭት እንዳስቆመ ጠቁሟል፡፡ የሰላም  ተቋሙ በመላው ዓለም ከሚገኙ 81 አገራትና ከ321 ከወጣቶች ጋር ትስስር ካላቸው ድርጅቶች ጋር በትብብር እንደሚሰራ ታውቋል፡፡
በሌላ በኩል፣ ‘ኢንስቲቲዩት ፎር ኢኮኖሚክስ ኤንድ ፒስ” የተባለ ዓለማቀፍ ተቋም በሰራው ጥናት፣ ባለፈው የፈረንጆች አመት በአለም ዙሪያ ከሚገኙ 162 አገራት ‘ከግጭት ነጻ’ የሆኑት 11 ብቻ እንደነበሩ በጥናት ማረጋገጡን ዘ ኢንዲፔንደንት ዘግቧል፡፡በዘንድሮው የፈረንጆች አመት ከተለያዩ የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ ግጭቶች የጸዱ ተብለው በጥናቱ የተለዩት አገራት ስዊዘርላንድ፣ ጃፓን፣ ኳታር፣ ሞሪሺየስ፣ ኡራጓይ፣ ቺሊ፣ ቦትስዋና፣ ኮስታ ሪካ፣ ቬትናም፣ ፓናማ እና ብራዚል ናቸው፡፡
እ.ኤ.አ ከ2007 ጀምሮ ባሉት አመታት የዓለማችን ሰላም ከጊዜ ወደጊዜ እየከፋ መምጣቱን የጠቆመው ዘገባው፣ ጥናቱ ከተሰራባቸው 162 አገራት ግጭት የሌለባቸው 11 ብቻ ሆነው መገኘታቸውም ለዚህ አለማቀፍ ችግር ማሳያ ነው ብሏል፡፡
ምንም እንኳን አስራ አንዱ አገራት በ2013 ከግጭት ነጻ እንደሆኑ በጥናቱ ቢረጋገጥም፣ አገራቱ ለግጭት ሊዳርጓቸው ከሚችሉ ሌሎች ችግሮች ነጻ አይደሉም ያለው ዘገባው፣ ለአብነትም በብራዚልና በኮስታ ሪካ የአገር ውስጥ ግጭቶች ችግር እጅግ በጣም አነስተኛ ቢሆንም፣ የአገራቱ ዜጎች አነስተኛ የጦር መሳሪያዎችን የማግኘት እድላቸው ከፍተኛ በመሆኑ ሃይል የተቀላቀለባቸው ተቃውሞዎች የመካሄዳቸው እድል በአሳሳቢ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱን አስረድቷል፡፡
ጥናቱ በተሰራበት ወቅት ሰላማዊ የነበረችው ብራዚል ከወራት በፊት ባስተናገደችው የዓለም የእግር ኳስ ዋንጫ ውድድር ሳቢያ በተቀሰቀሰባት የህዝብ አመጽ የተነሳ በቀጣዩ አመት ይወጣል ተብሎ በሚጠበቀው የ2014 ከግጭት ነጻ አገራት ዝርዝር ውስጥ እንደማትኖር ዘገባው ገልጿል፡፡
አንድ አገር ከግጭት ነጻ ለመባል፣ ተቋሙ ያወጣቸውን የግጭት መለኪያ መስፈርቶችን በሙሉ ማሟላት እንደሚገባውና በአገሩ የግዛት ክልል ውስጥ በሁለት የታጠቁ ሃይሎች መካከል (ቢያንስ አንዱ መንግስት መሆን አለበት) በተፈጠረ ግጭት በአመት ውስጥ ከ25 በላይ የሞት አደጋ ያልተከሰተበት መሆን አለበት፡፡ በድንበር አካባቢም ግጭት መኖር የለበትም፡፡
አሜሪካ ተቋሙ ባወጣው የሰላማዊነት ደረጃ 101ኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ ዘገባው ጨምሮ ገልጿል፡፡

Read 1837 times