Saturday, 03 May 2014 12:38

“በቤታችን ደህና መጥፋቱ ነው ወይ!”

Written by 
Rate this item
(8 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ…ክረምቱም እየመጣ ነው…ብርድ ብርድ ሊለን ነው፡፡ ለነገሩ… አለ አይደል… ዘንድሮ ፀሀዩዋ በሙሉ አቅሟ ወጥታም ‘ብርድ፣ ብርድ’ ይለናል፡፡ ምን ይደረግ! ብዙ ነገሮች ስረ መሰረታቸው እየተናደ፣ የትናንት በጎ ነገሮች አፈር እየለበሱ፣ እንግዳ ሲመጣ እግር አጥቦ የማሳደር ወንድማማችነት ወደ ‘አፈ ታሪክነት’ እየተለወጠ…ምነው ብርድ፣ ብርድ አይለንሳ! ልክ ነዋ…ምቾት በሌለበት ብርድ ‘ሰተት’ ብሎ ነው የሚገባው!  
ሁሉ በሽተኛ ሁሉ ራሴን ባይ
በቤታችን ደህና መጥፋቱ ነው ወይ!
የሚሏት አሪፍ አባባል አለች፡፡ እናማ…አሁን፣ አሁን የምናያቸውና የምንሰማቸው ነገሮች አብዛኞቹ  “በቤታችን ደሀና መጥፋቱ ነው ወይ!” የሚያሰኙ ናቸው፡፡ ከታች እስከ ላይ (ይቅርታ፣ ‘ከላይ እስከታች’ ለማለት ፈልጌ ነው፡) ነገሩ ሁሉ ግራ የተጋባ ሆኗል፡፡ በስርአት መመራት እየቀነሰ አብዛኛዎቹ ነገሮች የሚሆኑትም፣ የማይሆኑትም በእኛ በጎ ፈቃድ ብቻ ነው፡፡ ክፋቱ ደግሞ በጎ ፈቃድ የሚለው ነገር ከውስጣችን ሙልጭ ብሎ እየወጣ ነው፡፡ (በጎ ፈቃድ? የምን በጎ ፈቃድ!)  
እናማ…ህዝባችን የምድሩ ጉዳይ ግራ ሲገባው ቀን ከሌት እየጸለየ ነው፡፡ እባክህ ይቺን አገር ታደጋት እያለ ነው፡፡ “እባክህ እንዲህ የሚያናክስንን፣ የሚያቧጭረንን፣ ውሃና ዘይት ያደረገንን ጋኔን አሸቅንጥረህ ወርውርልን” እያለ ነው፡፡ ጋኔኑ ተሽቀንጥሮ እንዲወረውርልን ግን…ትንሽዬም ብትሆን የራሳችንን አስተዋጽኦ የምናደርግ ብዙ አይደለንም፡፡
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…የፀሎት ነገር ካነሳን አይቀር ይቺን ስሙኝማ…ስኮትላንዳውያን ‘ገብጋባ’ ናቸው ይባላል፡፡ እናላችሁ… አንዱ ስኮትላንዳዊ ከባድ የገንዘብ ችግር ይገጥመዋል፡፡ በጣም ከመቸገሩ የተነሳም እግዚአብሔርን ለመጠየቅ ወሰነ፡፡ “እግዚአብሔር  እባክህ እርዳኝ፡፡ ሱቄ ተወሰደብኝ፡ ገንዝብ ካላገኘሁ ቤቴም ሊወሰድብኝ ነው፡፡  እባክህ ሎተሪ እንዲደርሰኝ አድርግልኝ፡፡” ያን ቀን ሎተሪውን ሌላ ሰው ያሸንፋል፡፡ በተከታዩ ሎተሪ መውጫ ቀን ስኮትላንዳዊው እንደገና ይጸልያል፡፡ “እግዚአብሔር  እባክህ እርዳኝ፡፡ ሱቄ ተወሰደብኝ፤ ቤቴ ተወሰደብኝ፣ ገንዝብ ካላገኘሁ መኪናዬም ሊወሰድብኝ ነው፡፡” አሁንም ለሌላ ሰው ይደርሳል፡፡ ስኮትላንዳዊው አሁንም እንደገና ይጸለያል፡፡ “እግዚአብሔር  እባክህ እርዳኝ፡፡ ሱቄ፣ ቤቴና መኪናዬም ተወሰዱብኝ፡፡ አሁን የምበላው እንኳን አጣሁ፡፡ ብዙ ጊዜ እርዳታ ጠይቄህ አላውቅም፡፡ ደግሞ ጥሩ አገልጋይህ ነኝ፡፡ እባክህ ሎተሪ እንዲደርሰኝ አድርግልኝ!” ይሄኔ ከሰማይ ከፍተኛ ብልጭታ ታየና እግዚአብሔር ምን ቢለው ጥሩ ነው…”መጀመሪያ የሎተሪ ትኬት ሳትገዛ እንዴት ብዬ ነው እንዲደርስህ የማደርገው!” አጅሬው ለካ ከገብጋባነቱ የተነሳ አንድም ቀን የሎተሪ ትኬት ሳይገዛ ነበር የሚጸልየው፡፡
እናላችሁ…አንዳንዴ ነገረ ሥራችንን ስታዩ የሎተሪ ትኬቱን ሳንገዛ “እባክህ፣ ሎተሪ እንዲወጣልኝ አድርግልኝ! አይነት ጸሎት መደጋገም ነው፡፡
ታዲያላችሁ…ቀን አልፎ ቀን ሲተካ ከተስፋ ሰጪ ነገሮች ሁሉ ተስፋ የሚያስቆርጡ ነገሮች ሲበዙ ግራ ይገባችኋል፡፡ ለምን ተስማምተን መኖር እንዳቃተን ግራ የሚገባ ነው፡፡ የምንለያይባቸው፣ የጎሪጥ የምንተያይባቸው ነገሮች መብዛታቸው ምክንያት ለመስጠት እንኳን አስቸጋሪ ነው፡፡ በአንድ በኩል ስለማይገባንና የያዘው አጀንዳ  ‘መርዝ ይሁን ማር’ ገና ባልለየት ‘ግሎባላይዜሽን’ እያወራን በቤታችን እንኳን ተስማማትን መኖር እያቃተን ነው፡፡ የምር እኮ መደማመጥ አልተቻለም፡፡ የምንናገራቸው ነገሮች እንደ አዳማጩ ፍላጎት እየተመተሩ ‘ጠብ አውርድ’ አይነት ነገሮች በየቦታው ታያላችሁ፡፡ የሚከፋፍሉን ነገሮች በብዙ ቁጥር ነገ ተነገ ወዲያ “ምነው ከሳ አልክብኝ!” ያልነው ወዳጃችን  “ከሳ አልክብኝ ያልከው በሽተኛ ነህ ለማለት ነው!” አይነት ‘ቅልጥ ያለ ጠብ’ ሊፈጥር ይችላል፡፡
አንዲት ወዳጄ የገጠማትን ስሙኝማ…ከአዲስ አበባ ወጣ ካለ ከተማ ብቅ ብላ በሚኒባስ ስትመለስ መኪናው ውስጥ ከተፈቀደው በላይ ትርፍ ሰዎች ይገባሉ፡፡ ሾፌርም ትራፊክ እንደሚከሰው ቢለማመን የሚሰማው ጠፋ፡፡ ወዳጄም ነገር ለማብረድ ብላ አንደኛውን ትርፍ የገባ ሰው “መኪናው ሙሉ ሰው ብቻ ነው የሚጭነው…” ብላ ሳትጨርስ ሰውየው ምን ቢል ጥሩ ነው…“እኔ ግማሽ ሰው ነኝ!” እና አልወርድም አለ፡፡ በዛ ቢበቃ ጥሩ ነበር፡፡ ለወዳጆቹ “ሙሉ ሰው አይደለህም አለችኝ…” ብሎ ነገሩ ሁሉ ድብልቅልቁ ወጣ፡፡ እንደምንም በአንዳንድ ሰዎች ጣልቃ ገብነት ወደ አዲስ አበባ ተመለሰች፡፡
አያችሁልኝ አይደል! እንዲሁ በትንሽ ትልቁ ጠብ፣ ጠብ ስለሚለን ነው እንጂ “መኪናው ትርፍ ሰው አይጭንም፣” ማለት “እኔ ግማሽ ሰው ነኝ!” ያሰኛል?
እናማ…“በቤታችን ደህና መጥፋቱ ነው ወይ!” የሚያሰኙ ነገሮች እየበዙ ነው፡፡
ንግግሮች እንኳን እየተሰነጣጠቁ ባለበት ወቅት ነገ ከነገ ወዲያ ሰላምታችን እንኳን ተመንዝሮና ተመነዛዝሮ ‘አገር ቀውጢ’ ቢሆን ምን ይገርማል፡፡ በንጹህ ልቦና የተነገሩ ምንም ጉዳት የሌለባቸው አባባሎች ወደ ዘር፣ ኃይማኖት፣ ፖለቲካ ምናምን እየተመነዘሩ “እውነትም የተዘጋ አፍ ዝንብ አይገባበትም…” እንድንል እያደረጉን ነው፡፡
እናላችሁ…“በቤታችን ደሀና መጥፋቱ ነው ወይ!” የሚያሰኙ ነገሮች እየበዙ ነው፡፡
ብዙ ቦታ በጎ መልስ የሚመልስ ማግኘት እያዳገተ ነው፡፡ ሁሉም ብሶቱን እናንተ ላይ ሊወጣ ነው የሚሞክረው፡፡ “ሻዩ ውሀ ውሀ ነው የሚለው” ስትሉ  “ሻይ ቅጠሉን እኛ አላመረትነውም…” የሚሉ አሳላፊዎች የበረከቱበት ዘመን ነው፡፡ በሳንቃ መወልወያና በእጅ መጥረጊያ ፎጣዎች መካካል ልዩነቱ ግራ ገብቷችሁ ስትጠይቁ ግልምጫ የምታኙበት ዘመን ነው፡፡
ገንዘባችሁን ከፍላችሁ ስለምትገዙት አገልግሎትና ምርት ጥራት አፍ አውጥቶ መጠየቅ ‘ድፍረት’ እየሆነ የመጣበት ዘመን ነው፡፡ በማስታወቂያዎች የምንሰማቸውና የምናያቸው ነገሮች ከዋናዎቹ ምርቶችና አገልግሎቶች ጋር አልገጥም እያሉን ግረ ተጋብተናል፡፡ ስሙኝማ…አንዳንዴ ሳስበው ምን ይመስለኛል መሰላችሁ…የአማርኛ ቋንቋ ቅጽሎች በሙሉ ማስታወቂያዎች ላይ በገፍ እየገቡ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ለመዝገበ ቃላት እንኳን የሚበቁ ቅጽሎች እንዳናጣ! ቂ…ቂ…ቂ…
እናማ…“በቤታችን ደሀና መጥፋቱ ነው ወይ!” የሚያሰኙ ነገሮች እየበዙ ነው፡፡
‘የእኛው ሰውዬ’  አንድ ጊዜ “ምን ሲሉት ፋንድያ ይላል…” ምናምን ብለው ሙልጭ አድርገው ልክ ልካችንን ነግረውን ነበር፡፡ ዘንድሮ ‘ፋንድያ’ ምናምን አይባል እንጂ ‘ወንበር’ ማለት ሰፊው ህዝብ ላይ ‘መነስነስ’ የሚመስላቸው መአት አሉ፡፡ እናማ…“በቤታችን ደህና መጥፋቱ ነው ወይ!” የሚያሰኙ ነገሮች እየበዙ ነው፡፡የትራፊክ መብራት ጠብቆ ማሽከርከር የህግ ጉዳይ ሳይሆን የአሽከርካሪዎች ‘በጎ ፈቃድ’ ጉዳይ እየሆነ ነው፡፡
 በየዕለቱ ነገሬ ብላችሁ ካያችሁ መብራት ጥሰው ለማለፍ የሚሞክሩና የሚያልፉ አሽከርካሪዎች ብዛት ይገርረማችኋል፡፡ ኮሚክ እኮ ነው…በመኪና መሪ ጀርባ የተቀመጠ ሁሉ የቸኮለና ‘የተጣደፈ’ እሱ ብቻ ይመስል መብራት ሲጥስ፣ ጡሩምባውን ሲያምባርቅ…“ኧረ ሥነ ምግባር ምን ጉድጓድ ውስጥ ተወሸቅሽ!” ያሰኛችኋል!
እናማ…“በቤታችን ደህና መጥፋቱ ነው ወይ!” የሚያሰኙ ነገሮች እየበዙ ነው፡፡ ከነቢይ መኮንን ግጥም የቀነጨብኳትን አንብቧትማ፡፡
አንዳንዴ
አንጎሌን እንደ ዣንጥላ አጥፌ
አገርን በወግ ሰልችቼ፣ ፍቅሯን ከልቤ አጠንፍፌ
ወደ እሷ የሚያደርሱኝን መንገዶች ሁሉ አጥሬ
    ሌላ ሌላ አገር አያለሁ፡፡
አገሬ ግን…እንደጌታ የስቅለት ቀን
በአራት አቅጣጫ ተወጥራ
እመስቀል ላይ ተቸንክራ
ጣሯን ቁልቁል በማሰማት
ነገዋን በእኔ ለማየት “ላማ ሰበቅታኒ?” አለችኝ “ለማን ተውከኝ በዚህ ሰዓት?”
አዎ…አገር “ላማ ሰበቅታኒ? ለማን ተዋችሁኝ በዚህ ሰዓት?” እያለች ነው— የሚሰሟት ጥቂት፣ ጆሯችን ላይ የተኛን መአት ሆንን እንጂ!
እናማ…“በቤታችን ደህና መጥፋቱ ነው ወይ!” የሚያሰኙ ነገሮች እየበዙ ነው፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 3902 times