Saturday, 08 March 2014 12:14

ምግብና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ

Written by  አልአዛር ኬ
Rate this item
(3 votes)

“የታሰረን ምላስ ወይን ጠጅ ይፈታዋል”

በአለም ላይ የሚፈጠሩትን ግጭቶችና ፈጠራ የታከለባቸውን ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴዎች በተመለከተ ምግብ ምን አይነት ትምህርት ሊሠጣችሁ ይችላል ተብላችሁ ብትጠየቁ ምን አይነት መልስ ትሠጣላችሁ?
ሳሎን ቤት ውስጥ ተቀምጠው የተለያዩ ግላዊ፣ ማህበረሠባዊና ሀገራዊ ጉዳዮችን እያነሱ እርስ በእርስ እየተጫወቱ ያሉትን ከተለያየ ቦታ የመጡ፣ የተለያየ ወግ፣ ባህል፣ ሀይማኖትና ዘር ያላቸውን እንግዶችዎን ቤት ያፈራውን ምግብ አዘጋጅተው ሊጋብዟቸው ሽር ጉድ የሚሉባትን ማድቤትዎን ወይም ኩሽናዎን እስኪ ለአንድአፍታ ያስቧት! መቼም መጥበብና መስፋቷ፣ ባህላዊ አሊያም ዘመናዊ የመሆኗ ነገር ከሁሉም ቀድሞና ፈጥኖ ወደ አዕምሮዎ ሊመጣልዎ እንደሚችል ምንም አያጠራጥራም፡፡ ማድቤትዎ ወይም ኩሽናዎ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ከሚቦካባቸው ቦታዎች መካከል አንዱ ይሆናል የሚል ሀሳብ ግን ወዲያውኑ እንደማይመጣልዎ በእርግጠኝነት መገመት ይቻላል፡፡
እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ማድቤቶች ወይም ኩሽናዎች በተለይ ደግሞ ምግብ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ሁኔታ የአለም ዲፕሎማሲ ሰርክ እየተጠነሰሰ ከሚጠመቅባቸው ዋነኛ ነገሮች አንዱ ሆኗል፡፡
ምግብ የሰው ልጅ በህይወት ለመቆየት ከሚተነፍሰው አየር ቀጥሎ የሚያስፈልገው መሠረታዊ ፍላጐቱ ነው ብሎ መናገር መቼም የአንባቢን ንቃተ ህሊና ዝቅ አድርጐ እንደ መገመት ተደርጐ ሊቆጠር ይችላል፡፡ ለምን ቢባል? ማንኛውም የሰው ልጅ ከሊቅ እስከ ደቂቅ ጠንቅቆ የሚያውቀው ጉዳይ ስለሆነ ነው፡፡
ከዚህ መሠረታዊ እውነት ባለፈ ግን ምግብ ሁሌም ቢሆን የሚቀርበው በውስጡ የአቅራቢውን ዘርና ባህል ይዞ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለሰው ልጆችና ለውጭ ግንኙነታቸው እጅግ አስፈላጊ የሆነና ጠንካራው ቅመም ወይም ግብአት ነው፡፡ ይህ መሠረታዊ ጉዳይ በሌላ አነጋገር ሲገለጽ ምግብ የተለያየ ዘርና ባህል ያላቸው ሰዎችም ሆኑ ማህበረሰቦች እርስ በርሳቸው የሚገናኙበት የግንኙነት መስመር ነው ማለት ነው፡፡
ምግብ ለውጭ ጉዳይ ፖሊሲና ፖሊሲው በተግባር ለሚገለጽበት የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ ታሪካዊ አስፈላጊነት እድሜውን አሀዱ ብሎ መቁጠር የሚጀምረው ከጥንታውያኑ ግሪኮችና ሮማውያን ስልጣኔ ዘመን ነው፡፡ ጥንታውያኑ ግሪኮችና ሮማውያን በዘመናቸው ምግባቸውን እየተመገቡ፣ ከተለያዩ ሀገራት እንግዶች ጋር በተለያዩ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ድርድሮችን ያካሂዱ ነበር፡፡ የተለያዩ ግጭቶችን ለማስወገድም ሁነኛ መላ ያበጁ ነበር፡፡
እነዚሁ ጥንታውያን ግሪኮችም ሆኑ ሮማውያን “የታሰረን ወይም የተቆለፈን ምላስ ማለፊያ የወይን ጠጅ ደህና አድርጐ ይፈታዋል፡፡” የሚል ዘመን የጠገበ ምሳሌአዊ አነጋገር አላቸው፡፡ እናም ከሌላ ሀገር እንግዶች ጋር ማዕድ ቀርቦ ለመብል በተሰየሙ ጊዜ፣ ከማለፊያው የወይን ጠጅ ፈታ ባለ እጅ፣ ከፍ ባለ ልግስና እንግዶቹን በመጋበዝ፣ በሀገር ፍቅር ወኔና በአርበኝነት ስሜት የተዘጉ ልቦች እንዲለዝቡ፣ የታሰሩ ምላሶችም እንዲፈቱ በማድረግ የእንግዶቹን ሀገር ከፍተኛ ሀገራዊ ምስጢር አስዘክዝከው የአደባባይ ላይ ወግ እንዲሆን ያደርጉ ነበር፡፡
ይህን የመሠለው የጥንታዊያኑ ግሪኮችና ሮማውያን የምግብ ዲፕሎማሲ፣ ዛሬም ቢሆን ጨርሶ አልጠፋም፡፡ በያዝነው ዘመን በተለያዩ የአለማችን ሀገራት አገሮቻቸውን ወክለው የሚገኙ ኤምባሲዎች የየሀገሮቻቸውን ብሔራዊ ቀናት ወይም ሌሎች ከፍ ያለ ቦታና ግምት የሚሠጧቸውን በአላት ምክንያት በማድረግ ተገቢና በቂ ነው ያሉትን የምግብና የመጠጥ ድግስ ደግሰው ታላላቅ የመንግስት ሹማምንት፣ የፖለቲካ፣ የወታደራዊ፣ የሲቪል ማህበረሠብና የንግድ መሪዎችን እንዲሁም የሌሎች ሀገራት አምባሳደሮችን የሚጋብዙበት የዲፕሎማሲ ባህል መነሻ መሠረቱ ሌላ ነገር ሳይሆን ይሄው ነው፡፡
ዋና አላማውም የድርድር፣ የውይይት፣ የአዲስ ግንኙነት ፈጠራ፣ የመረጃ ልውውጥ፣ ስለላና የመሳሠሉትን የውጭ ግንኙነትና የዲፕሎማሲ ስራዎችን አቅም በፈቀደ መጠን ማካሄድ ነው፡፡
ይህ እድሜ የጠገበ የምግብ የውጭ ግንኙነትና የዲፕሎማሲ ስራ አሁን ባለንበት ዘመን አዲስና እንደ ጊዜው የዘመነ አቅጣጫና ይዘት እንዲኖረው ለማድረግ በልባቸውና በመንፈሳቸው የቆረጡ የአዲስ ትንሳኤ አርበኞችን አግኝቷል ተብሏል፡፡
በአለማችን ያለውን የምግብ ኢንዱስትሪ ከፍተኛ ጠቀሜታ አበክረን ተረድተናል ያሉ የአሜሪካ የአለም አቀፍ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲና የዲፕሎማሲ ሊቃውንት፣ ሙያውን በከፍተኛ ደጃ በማሳደግ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ የሚሠጥ አሪፍ የትምህርት ዘርፍ ለማድረግ በቅተናል ብለዋል፡፡
ዋሽንግተን ዲሲ የሚገኘው አሜሪካን ዩኒቨርሲቲም በምግብ ዲፕሎማሲ (Culinary Diplomacy) እግ በግጭት ምግቦች (Conflict Cuisines) በዲግሪ ደረጃ ትምህርት ለመስጠት ዝግጅቱን አጠናቆ ተማሪዎችን ለመቀበል ምዝገባ የሚያካሂድበትን ቀን ቆርጦ አሳውቋል፡፡
የሆኖ ሆኖ ግጭቶች ምንም እንኳ ቀጥተኛ ትርጉማቸው ረጅም ታሪካዊ ሁነቶችን ቢያስታውሱንም በመላው አለም አዲስ የምግብ ዲያስፖራ በመፍጠሩ ረገድ በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት የተፈጠሩት ግጭቶች ያሳደሩት ተጽዕኖ በጣም ከፍተኛ ነው፡፡
አዲስ የተፈጠረው የምግብ ዲያስፖራም የደቡብ ምስራቅ እስያን፣ የመካከለኛው ምስራቅን የካሪቢያንን፣ የተለያዩ የመካከለኛው አሜሪካን ምግቦችና አመጋገባቸውን የአውሮፓውያንን የምግብ ባህል ትከተል ወደነበረችው አሜሪካ አስገብቷል፡፡
የምግብ ዲፕሎማሲ ነገርም የአለም አቀፍ ተጓዦችን እንቅስቃሴ ተከትሎ ማደግ ችሏል፡፡ ምግብ የተለያዩ የዲያስፖራ ማህበረሠቦች ሀገር-በቀል ባህል አንዱና ዋነኛው መገለጫ መሆኑም ለምግብ ዲፕሎማሲ እድገት የራሱን አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ፣ ዛሬ በአሜሪካም ሆነ በአውሮፓ በሚገኙ ታላላቅ ከተሞች ውስጥ የኢትዮጵያው ተወዳጅ ምግብ ዶሮ ወጥና ሽሮ፣ የኔፕልስ የባስማቲ ሩዝ እንዲሁም የቱርክ ሺሽክባብና ሸዋርማ ተሠናድተው ከሚቀርቡባቸው የተለያዩ ምግብ ቤቶች መስኮቶች አለምን በጨረፍታም ቢሆን አሻግሮ መመልከት ይቻላል፡፡
ሴኔጋላውያን “ምርጡ ዛፍ ጭው ካለው ገደል አፋፍ ላይ ይበቅላል፡፡” ይላሉ፡፡ እነዚህ የተለያዩ የአለማችንን ህዝቦች ባህልና ወግ የሚያሳዩ ምግቦችም አብዛኛውን ጊዜ በግጭቶች የተወለዱ ናቸው፡፡ የእነዚህ ምግቦች አሰራርና የተለያዩ ግብአቶች በአውሮፓውም ሆነ በአሜሪካ ታላላቅ ከተሞች መገኘት የቻሉት የተሻለ ህይወትንና ነፃነትን ፍለጋ የትውልድ ቀያቸውን ጥለው ከተሰደዱት ስደተኞች ጋር አብረው በመሠደድ ነው፡፡ ዛሬ በመላው የአለማችን ሀገራት  በሚሊዮን የሚቆጠሩ ስደተኞች ምግብ ቤት ከፍተው የሀገራቸውን ባህላዊ ምግቦች በማቅረብ በነዋሪው ዘንድ ቀላል የማይባል እውቅና አትርፈዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በተለይ የአንዳንድ ሀገራት ስደተኞች ለግንኙነት ቋንቋ ብቻውን በቂ በማይሆንበት ጊዜ በከፈቱት ምግብ ቤት አማካኝነት ምግብ ምን ያህል ድንቅ የግንኙነት መሳሪያ እንደሆነ መረዳትም ማስረዳትም ችለዋል፡፡
ይህን ጉዳይ በምሳሌ ማስረዳት ምናልባት ጉዳዩን ቀለል ሊያደርግልን ይችላል፡፡ አሜሪካ ከኩባ ጋር ኦፊሴላዊ የዲፕሎማቲክ ግንኙነት የላትም፡፡ ይሁን እንጂ አንድ አሜሪካዊ የኩባን ምግብ ከሚያሚ ግዛት ውጪም ቢሆን እንደፈለገው ማግኘት ይችላል፡፡ የአሜሪካና የቬየትናም የዲፕሎማሲ ግንኙነት በድጋሚ የታደሰው በ1995 ዓ.ም ነው፡፡ በአሜሪካ የሚገኙ የቬትናም ምግብ ቤቶች ግን ከዚህ ጊዜ ቀደም ብሎ ጀምሮ ባህላዊ ምግባቸው ለአሜሪካውያን ደንበኞቻቸው ያቀርቡ ነበር፡፡
ከ1998 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል የተካሄደው አሳዛኝ ጦርነት ለሁለቱ ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መቋረጥ ምክንያት ሆኗል፡፡ ይሁን እንጂ በርካታ ኤርትራውያን በአውሮፓና አሜሪካ በሚገኙ ታላላቅ ከተሞች በሚገኙ የኢትዮጵያ ምግብ ቤቶች ጐራ በማለት የምግብ ናፍቆታቸውን ይወጣሉ፡፡
አንድ ተጨማሪ ምሳሌ እናቅርብ፡፡ በኮሎምቢያ የእርስ በርስ ግጭት በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ ይሁን እንጂ ግጭቱ የኮሎምቢያ የምግብ አብሳዮች የልኡካን ቡድንን ወደ ዋሽንግተን ዲሲ አምርቶ “ምግብና ሰላም” በሚል ርዕስ ንግግር ከማድረግ አልገታውም፡፡
ምግብ እጅግ ባስቸጋሪ ወቅት ህዝቦች እርስ በርስ እንዲቀራረቡ የማድረግ ጠንካራ አቅም አለው፡፡ ይህ ግን ሁልጊዜ እውን አይሆንም፡፡ የእህል (ምግብ) ማዕቀብ በተጣለ ጊዜ ወደ ጦር መሳሪያነት ተቀይሮ ማገልገል ይችላል፡፡ አሳዛኙ የሶሪያ ሰብአዊ ቀውስ ለዚህ አንዱ አብነት ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት አለማችን ምግብን የተመለከተ እንደ ኋላ ቀር ግብርና፣ ድርቅ፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ ድህነት፣ ረሀብ የምግብ ዋስትና ማጣትና የመሳሰሉ በርካታ ችግሮች አሉባት፡፡ ይህም ሁሉ ሆኖ ግን የምግብን የውጭ ግንኙነትና የዲፕሎማሲ ሀይል በመጠቀም፣ ህዝቦች የጋራ የሆነ ጉዳዮችን እንዲያፈላልጉ ማበረታታት ይቻላል፡፡ ፍራንዝ ካፍካ በአንድ ወቅት “ምግብ በአፍህ ውስጥ እስካለ ድረስ ሁሉንም አይነት ጥያቄዎችህን ለጊዜው ፈታኻቸው ማለት ነው፡፡” ያለውም ለዚሁ ነው፡፡

Read 4180 times