Saturday, 07 December 2013 13:08

የድሬዳዋ የጉዞ መደምደሚያ!

Written by  ነቢይ መኰንን
Rate this item
(0 votes)

“ድሬ ወላድ-ነሽ፤ ሽለ-ሙቅ”

በሀይቅ ከተከበበችው ደብረዘይት ጀምሬ በአዳማ የአሸዋ እምብርት አቋርጬ፣ አዋሳ ገባሁ፡፡ ከዚያ ወደ ደብረ ብርሃን ዘለቅሁና ድሬ ላይ አረፍኩ። የማህበረሰብ አቀፍ የሆኑትን ዕድሮች ህበርታቸውን፣ የሸማቾች ማህበራትን አቅም፣ እናት አባታቸውን ያጡ ህፃናትና ጧሪ - አልባ አረጋውያን የሚረዱበትን መንገድ፣ አየሁ፡፡ የአካባቢያቸውን ህዝባዊ አቅም (Resource)  እንዴት ፈልፍለው፣ አደራጅተው የልማት አቅም እንደሚገነቡ አስተዋልኩ፡፡ ትምህርት ጤና፣ የከተማ ግብርና እንዴት ከህዝቡ ክንድ እንደሚበቅል ተማርኩ፡፡ እናቶች፣ ሴቶች የገዛ ኑሮዋቸውን ለማሻሻል በገዛ እጃቸው ሲፍጨረጨሩ ተመለከትኩ፡፡ ከብት ከማርባት፣ በከብት ተዋጽኦ እስከገመገልገልና ራሳቸውን እስከ መቻል፤ ብሎም ዘላቂ ህልውናቸውን ለማረጋገጥ ሲጣጣሩ አይቼ ተማረኩ፡፡  ወጣም ወረደም፤ ህዝብ በራሱ ሲተማመን እንደማየት አስደሳች ነገር የለም!! ህዝብን እንደመውደድ፣ በራሱ ሲተማመን እንደማየት አስደሳች ነገር የለም፡፡ ህዝብን መውደድ፣ ህዝብን ማመን፣ ራሱን እንዲችል የተቻለንን ሁሉ ማድረግ፤ ከማንኛውም ነገር የተሻለ ተጨባጭ ጉልበት ማፍራት ነው፡፡ በሀገር ላይ ለውጥ ማየትን አፈሩ ላይ ሆኖ መመስከር መታደል ይመስለኛል። የህዝብን ዕውነተኛ ኑሮ በማናቸውም አጋጣሚ ተጠግቶ ማስተዋል ቢያንስ ከሃሣዊ - አዋቂነትና ከአዛኝ ቅቤ አንጓች የይስሙላ ፕሮፖጋንዳ ያድናል፡፡
የእየሩሳሌም ህፃናትና ማሕበራዊ ልማት ድርጅት፤ በልማት ላይ ትኩረት አድርገው ለረዥም ጊዜ ሲንቀሳቀሱ ከነበሩና ካሉ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች አንዱ ነው። ከላይ በተዘረዘሩት ፍሬ - ጉዳዮች ዙሪያ አያሌ ተግባራትን አከናውኗል፡፡ ሀገራችን ለሚቀራት ረጅም ጉዞ የበኩሉን አስተዋጽኦ አድርጓል፤ ያደርጋልም፡፡
የድሬዳዋ ጉዞ ማስታወሻዬን በሚከተለው ግጥም ደምድሜ ወደ ባህርዳርና አውራ አምባ ጉዞዬን እቀጥላለሁ፡፡ (የፀጋዬ ገ/መድህንን “እንኳን ለዓመት ጉድ አበቃን” የሚለውን ግጥም በዚሁ እትም ገፅ 17 ይመልከቱ) “መጓዝ ማወቅ ነው” ይላሉ ፈረንጆች፡፡ ማሳወቅም ትልቅ ፀጋ ነው ብዬ ስለማምን፤ ያየሁትን፣ የሰማሁትን፣ ያጋጠመኝን ሁሉ ባመቸኝ ሰዋዊ መልኩ እነቁጣለሁ፡፡   
ድሬ ወላድ ነሽ፤ ሽለ-ሙቅ
ድሬ ወላድ የጭንቅ ቀን
ጐርፍ ምጥሽ፣ ፈውስሽ እርከን፤
ዥንጉርጉር የቀለም ድንኳን፣ ህብረ - ቀለም የፀባይ ዳስ
የፍቅር አዋይ፣ የውበት ዳንስ
የምድር ከለላ ዛፍ ጥላ
የሁሉ አገር፣ ሁለት ባላ፤
የድህነት የዕድገት - ማላ!
ድምር ፅዋ ድሬዳዋ፣
ድሬ የሳቅ ቀን ደመራ፣ ችግር - ፈዋሽ የለውጥ - ግት
የጐርፍ ሥጋት ምጥ እናት
ድሬዳዋ የአደጋ ሥር፣ የነግ-ተጓዥ የልባም-ቋት
የጫት አድባር የሰላም ጣት፣ የመፈቃቀር ቅን ጥለት፤
ጭንቅ - አምካኝ የመሬት ጽላት
ድሬዳዋ የፍቅር ርስት
የድንገቴ  ወዳጅ እንኳ፣ ዘላለም የሚያሽርብሽ
ገንደ - ደሀሽ ሜዳ ሁዳድ
ተቸጋሪሽ ዙሪያ መንገድ
ገንደ - ጋራሽ ተራራ አናት፣ ድሬ ፈትል የመላ-ምት
ድሬዳዋ ያገር እናት፡፡
ስሚኝ ድሬ…
የማይገታ ጐርፍ የለም፣ የማይታለፍ እንቅፋት
የማይሸኝም ቀን የለም፣ የማይሻር ያሰት - ሹመት!
የማይለማ ጪንጫ የለም፣ የማይከስም ሀሳዊ - ዕድገት!
ድሬ ጣሪ፣ ድሬ ኑሪ፣ ራስሽን ቻይ ድሬ ምሪ
ተራሮችሽን ተርትሪ፣ የጋራ ሰምበር ፍጠሪ
ድሬ፤ “ዛላ-አንበሳ” ያልሺው፣ ጐርፍ-ገድቡ ግንብሽ
በምጥ-ቀንሽ ያበጀሽው፣ ውድ ጋሻ ነው አጥርሽ!
ምራቅን ከንፈር ነው እሚያጥረው፣ በይ እርከንሽን አሳምሪ
ማዶ ለማዶ “ሞረሽ” በይ፣ በሞባይል ተጠራሪ
ህዝብ ነው ምንጊዜም ክንድሽ፣ እድርሽን አጠንክሪ፡፡
የከተማ አትክልትሽን፣ ወዶ - ልማትሽን ቀጥዪ
የቀን ሐራራሽን ሻሪ፣ ምስኪንሽን ውለሽ አውዪ!
ህዝብሽ ልብ ውስጥ ነው ተስፋሽ፣ ሲያምን የሚረታ እሱ ነው
በግድ የትም አይደረስ፣ በፍቅር ነው ሰው ዕድገቱ
ያንቺ መቀነት መጥበቅ ነው፣ ሀሞትሽ ነው መዳኒቱ
“ከቶም ያልተዋጉበት ቀንድ፣ ከጆሮ አንድ ነው” ይላሉ
ቅርስ-ቅሪትሽን ቀስቅሰሽ፣ አብስይው ይድረስ ለሁሉ!
ድሬ ወላድ ነሽ፣ ሽለ ሙቅ፤ የሚቀናብሽ ይጨነቅ
የማይመርቅሽ ይውደቅ፣ የክፉ - ቀን ጠርሽ ይራቅ!!
እና ድሬ፤ ሞትሽ ይሙት፤ መቀመቅ ይግባ ድህነት
የማይገታ ጐርፍ የለም፣ የማይታለፍ እንቅፋት
የማይሸኝ ቀን የለም፣ የማይሻር ባለ ሹመት …
ሳቂ ድሬ ጐርፍሽ ይድረቅ
ድሬ ቡሬ ያባድር ጨርቅ
ድሬ ፍቅር የአገር ደማቅ! ..
ድሬ ወላድ ነሽ፤ ሽለ-ሙቅ!
(ለድሬዳዋና ጐርፉን ለረታው ህዝብ)
ህዳር 26 -2006 ዓ.ም

Read 1587 times