Saturday, 30 November 2013 11:10

“ብቻዬን ነኝ ፈራሁ…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(5 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
አዎን ብቻዬን ነኝ ፈራሁ
እሸሸግበት ጥግ አጣሁ
እምፀናበት ልብ አጣሁ
እማማ ኢትዮዽያን መንፈሴ ተፈቶ እንዳይፈታት ሰጋሁ
ብሎናል ሎሬት ጸጋዬ በአቡነ ዼጥሮስ አንደበት። ከብዙ ዘመናት በኋላም “እሸገግበት ጥግ አጣሁ…” የሚያሰኝ መከራ

ሲወርድብን ያሳዝናል፡፡ እንጀራ በየሰዉ አገር እያንከራተተን የየዕለቱ ግፋቸው አልበቃ ብሎ “መቅደስ እንደገባች ውሻ…”

መንገድ ለመንገድ ሲያሳድዱንና በነፍስ ደርሶ “አይዞህ የአገሬ ልጅ፣ አለሁልህ…” የሚል ስናጣ… አለ አይደል… ምነዋ

“እሸገግበት ጥግ አጣሁ... አንል!
የጠጣሁት ጠጅ ምን አላረገኝ
እንጀራው አዙሮ በሰዎች ፊት ጣለኝ
ይሉ ነበር አባቶቻችን፡፡ አዙሮ እየጣለን ያለው ‘እንጀራ’ ነው፡፡ ለበረሀ ወንበዴ፣ ለባህር አውሬ፣ ለከተማ ‘ባሪያ ፈንጋይ’

ሲሳይ ያደረገን በቁራጭ እንጀራ የአንጀታችንን ጩኸት እናስታግሳለን ብለን ነው፡፡ በኢምግሬሽን በር ላይ ቁርና ብርድ

እየተፈራረቀብን ተሰልፈን ውለን እንድናድር የሚያደርገን ‘እንጀራ’ ነው፡፡
አንድዬ አገር ለአገር የመንከራተት ዘመን ይብቃችሁ ይበለንማ!
በዕውቀት ሳይሆን በዘይት ትከሻቸውን ያሰፉ፣ ጎናቸውን ያደነደኑ፣ ከእኛ በላይ ለአሳር በሚሉ፣ በገንዘባቸው ኃይል

መንግሥታትንና ሚዲያዎችን ‘በኪሳቸው በከተቱ’ የሳውዲ ባለ ጊዜዎች ያ ሁሉ መከራ የደረሰባቸው ወገኖቻችን ዋነኛው

‘ወንጀላቸው’…እንጀራ መፈለጋቸው ነው፡፡
የእናት አገር ቀሚስ የአባት አገር ሸማ
ነጠላ አይደለም ወይ የሰው አገርማ
ይባላል፡፡ የሰው አገር ነጠላ ለሆነባቸው ወገኖቻችን አንድዬ ይብቃችሁ ይበላቸውማ!
ተባረው ወደ ሀገራቸው የተመለሱ 30 የፊሊፒንስ ሠራተኞች አገራቸው ሲገቡ የደረሰባቸውን ተናግረዋል፡፡ አንዷ “እንደ

እንስሳ ነው የሚቆጠሩን…” ነበር ያለችው፡፡ ለእኛ ዜጎችም ያላቸው አመለካከት ይኸው እንደሆነ ስንሰማ ኖረናል፡፡

በሰሞኑ ቪዲዮዎችም ላይ ስድቦቻቸውን ሁሉ ሰምተናል፡፡
እንዲህ ሁሉ ሲሆን ፈጥኖ … “አይ አሁንስ ወጥ ረገጣችሁ…” የሚል ‘ጋሻ’ ማጣታችን ያሳዝናል፡፡
እናላችሁ..እነኚሁኑ የፊሊፒንስ ዜጎች ለአራት ቀን አስረዋቸው ከቆዩ በኋላ ወደ አውሮፕላን ጣቢያ ሲወስዷቸው

እግሮቻቸውን በሰንሰለት አስረዋቸው ነበር፡፡ መካከለኛው ምሥራቅ ያሉ አንድ የእስልምና ኃይማኖት አባት “እነዚህ

ሙስሊሞች እስልምናን የተማሩት የት ነው? እስልምና በሠራተኞች ላይ እንዲህ አይነት ድርጊት አይቀበልም፡፡  

ሠራተኛውን  በሚደበድብ ላይ በፍርድ ቀን በቀል ይወሰድበታል፣” ብለዋል፡፡
ይሄኔ ነው “ነጠላ አይደለም ወይ የሰው አገርማ…” የሚያሰኘው፡፡ እና በርካታ ወገኖቻችን ‘እንጀራ’ እያንከራተታቸው

ይህንኑ እያሉ ነው፡፡
‘ኤዥያ ኒውስ’ የተባለ ዜና ምንጭ ባለፉት 12 ዓመታት ሳውዲ ዓረቢያ ውስጥ በአስቸጋሪ የሥራ ሁኔታዎችና የጉልበት

ብዝበዛ የተነሳ ከ3000 በላይ የኔፓል ዜጎች ህይወታቸውን አጥተዋል ይላል። አብዛኞቹ ህይወታቸው የሚያልፈው

በድብቅ በሚጠመቁ የአልኮል መጠጦች ነው ይላሉ፡፡ ወደ መጠጥ የሚገፉትም እጅግ አስቸጋሪ የሆነውን የሥራ ሁኔታ

መቋቋም እያቃታቸው በብስጭት ነው ተብሏል፡፡ በአልኮል የተነሳ በየወሩ ከ30 በላይ ሰዎች ይሞታሉ ተብሏል፡፡
እናላችሁ…ለመሆኑ ሳውዲ ዓረቢያም ሆነ ሌሎች የዓረብ ሀገራት ሄደው እንደወጡ የሚቀሩ ዜጎቻችንን ሁኔታ

የሚከታተለው ማን ነው? እዚህ እንደምንሰማው በተለያዩ ህገወጥና ተግባራትና ብልሹ ምግባሮች ውስጥ ይገባሉ

የሚባሉት ምክንያታቸውን ተከትሎ የሚጠይቃቸው ማን አለ?
ፊሊፕንሶቹ በየአገሩ በርካታ ኤጀንሲዎች ስላሏቸው የእያንዳንዱን ዜጋቸውን ዕጣ ፈንታ ይከታተላሉ፡፡ የምር ግን…መቼ

ነው እኛስ በየምንሄድበት የሰው አገር “በጎ አደርክ ወይ?” “የከፋሀ ነገር አለ ወይ?”  የሚሉን ‘የአገር ልጅ’ ተቋማት

የምናገኘው! መቼ ነው ገንዘብ ማግኛና ማስገኛ ብቻ መሆናችን ቀርቶ እኛ ራሳችን በምንም አይነት ዋጋ የማይተመን

ሰብአዊነት ያለን የአንዲት ታላቅ የነበረችና ከዕለታት አንድ ቀን ታላቅነቷን የምትመልስ አገር ዜጎች መሆናችንን የሚያምኑ

‘አድራጊ፣ ፈጣሪዎች’ የምናገኘው?
ሌላው የእኛ ችግር ‘ጉዳዩ እንዳይደለ’ ማወቁ አሪፍ ነው፡፡ በቀደም ቢቢሲ ‘Have Your Say’ ፕሮግራም ላይ ጋዜጠኛዋ

ስለእኛው ጉዳይ እያወያየች ነበር፡፡ እንግዶቿ ሁለት ኢትዮዽያውያንና አንዲት የሳውዲ ሴት ነበሩ፡ እናላችሁ…የቢቢሲዋ

ጋዜጠኛ በጣም ስትደጋግመው የነበረው ነገር የሚታዩት ቪዲዮና የፎቶ ምስሎች “ያልተረጋገጡ…” መሆናቸውን ነበር፡፡

“ያልተረጋገጡ…” መሆናቸውን መግለጹ በጋዜጠኝነት ስነ ምግባር ተገቢም ትክክልም ነው፡፡ ጨዋታዋ ያለው የቱ ላይ

መሰላችሁ… ተደጋግመው እዛው በዛው የሚታዩ  ምስሎችን ደጋግሞ “ያልተረጋገጡ…” ማለቱ ላይ ነው፡፡ (ድሮስ

እንግሊዝ! ቂ…ቂ…ቂ…)
አንደኛው ኢትዮዽያዊ በጉዳዩ ላይ በዝርዝር ሀሳቡን እየሰጠ እያለም ስለተካሄዱት የተቃውሞ ሰልፎች አንዳንዶቹ የኃይል

ተግባራተ የታዩባቸው  (‘ቫዮለንት’) ነበሩ አለች፡፡ እዚህ ቦታ ትልቁ ስዕል ያለው በሳውዲ በዓለም ህዝብ ፊት እየተፈጸመ

የነበረው የጭካኔ ተግባር ሆኖ ሳለ፣ ዓቢዩ ጉዳይ ለሌሎች ሲሆን በሚጢጢው ነገር ‘ያዙኝ ልቀቁኝ’ የሚሉት የዓለም

አቀፍ ሚዲያዎች ‘ጭምትነት’ ሆኖ ሳለ፣ የተቃውሞ ሰልፎቹ ቢሆኑም አብዛኞቹ ፍጹም ሰላማዊ የነበሩ መሆናቸው ሆኖ

ሳለ፣ አንዳንድ ቦታ ስሜታቸው ንሮ ራሳቸውን መቆጣጠር ያልቻሉ ግለሰቦችን ነቅሶ ማውጣቱ ‘ጨዋታ’ ይኖረዋል ብሎ

ማሰቡ ብልህነት ነው፡፡ (ድሮስ እንግሊዝ! ቂ…ቂ…ቂ…)
መጨረሻ ላይ ሀሳቡን ይገልጽ የነበረው ኢትዮዽያዊ ሌላ ጊዜ እንደሚደረገው የሁለትና ሦስት ደቂቃ ማሳሰቢያ

ሳይሰጠው፣ ሀሳቡን በአጭሩ እንዲያጠቃልል ሳይነገረው የጀመረውን ዓረፍተ ነገር እንኳን ሳይጨርስ መሀል ላይ

መቁረጡ ጨዋታ ሊኖረው ይችላል ብሎ ማሰቡ ክፋት የለውም፡፡
ስሙኝማ…ይሄ ከሁሉ ነገር ጀርባ ምስጢር የመፈለግ ‘ኮንስፒሬሲ ቲየሪ’ የሚሉት ነገር ብዙም አያስደስተኝም፡ ግን ዓለም

አቀፍ ሚዲያዎች ስለ እኛ በሚዘግቡበት ጊዜ ከ‘ሽፋኑ ስር’ (Between the lines… እንደሚሉት) ማንበብ፣ መስማትና

ማየት አሪፍ ነው፡፡
‘እውነት እውነት እላችኋለሁ’… ዓለም አቀፍ ሚዲያዎችን በተመለከተ ብዙ ወዳጆች የሉንም፡፡
አንዱ የሰብአዊ ድርጅት ድረ ገጽ የኢምፔሪያሊስቱ መገናኛ ብዙኃን…የሳውዲው አገዛዝ ለሚፈጽመው ጭካኔ ዝምታን

መርጠዋል” ሲል ይከስና እነሱንም “ወንጀሎኞች” ይላቸዋል፡፡
ዝም ያለው ዘመዴ እኔ ሳጣጥር
ሞተ ቢሉት መጣ አልቅሶ ሊቀብር፡
…….
እንዲህ አልኩት ዘመድ የተባለውን
ታምሜ ነበረ ሳጣጥር ማዘን
“አሁን ክንዴ ቀኝ እጄ ቢሉኝ
“አሁን የእናቴ ልጅ ወንድሜ ቢሉኝ
“ከሞትኩኝ በኋላ ምንም አይገባኝ፡
“ይልቅ ልተኛበት አታደንቁረኝ”
ይህን ተናግሬ አንጀቴን አርሼ
ወደ መጣሁበት ሄድኩኝ ተመልሼ፡፡
ይላሉ መንግስቱ ለማ፣ ለማዳን ወደኋላ የመቅረት፣ ለመቅበር የመትጋት ልምዳችንን ሲኮንኑ፡፡ የሆነውን ምንም ማድረግ

አይቻል ይሆናል፡፡ ነገ፣ ከነገ ወዲያ ዜጎቻችን በባእድ ሀገራት መንገዶች ላይ ተደፍተው እንድናይ፣ የዘርአይ ደረስ ልጆች

በባእድ አገራት አደባባዮች እየተሳደድን አናት አናታችንን ስንባል እንዳናይ ምን ማድረግ እንዳለብን ብንመክር ብልህነት

ነው፡፡
እናላችሁ...ከሁሉም በላይ ግን በወገኖቻችን ስቃይ ‘ጩኸታቸውን ለመቀማት’ የሚደረጉ የሁሉም ወገኖች ‘ሂሳብ

ማወራረጃ’ አይነት  ‘ፖለቲካዊ እገታዎች’ የሚያሳዩት አገር ወዳድነት ሳይሆን ራስን ወዳድነት ነው፡፡
እሺ- በለኝ እሺ እሺ በለኝ
እንቅልፍ ይውሰደኝ፣ እንቅልፍ ይውሰደኝ
አሉ ብርሀኑ ድንቄ በ‘አልቦ ዘመድ’፡፡
የሰሞኑን አይነት ሰቆቃዎች የማናይበትና ሰላማዊ እንቅልፍ የምንተኛበትን… “እንቅልፍ ይውሰደኝ፣ እንቅልፍ ይውሰደኝ…”

የምንልበትን ዘመን ያፍጥልንማ!
አዎን ብቻዬን ነኝ ፈራሁ
እሸሸግበት ጥግ አጣሁ
እምፀናበት ልብ አጣሁ
እማማ ኢትዮዽያን መንፈሴ ተፈቶ እንዳይፈታት ሰጋሁ
እንጉርጉሮ የማንጎራጎሪያ ዘመናችንን አንድዬ በቃችሁ ይበለንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 3930 times