Monday, 25 November 2013 11:03

“አልፋ የትምህርትና ሥልጠና አክስዮን ማኅበር” ከየት ወዴት?

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(2 votes)

                ሀገራችን ኢትዮጵያ የረዥም ዘመናት ታሪክ ባለቤት ብትሆንም ሐብትንና ዕውቀትን አቀናጅቶ፣ በጋራ ሰርቶአብሮ በማደግ ረገድ ግን ብዙ ይቀረናል፡፡  ለዚህም ይመስላል “ኢትዮጵያዊያን አብሮ መብላት እንጂ አብሮ መሥራት አይሆንላቸውም” የሚባለው፡፡
ዛሬም በ21ኛው ክ/ዘመን እንኳን በሀገራችን በአክስዮን ማኅበራት በመሰባሰብ መሥራት  በተግዳሮቶች የተሞላ ሆኗል፡፡ ለዚህ ዋነኛው ምክንያት ደግሞ የተቋማት ተገቢው ዕውቀት ባላቸው አካላት አለመመራት ይመስለኛል፡፡ አልፋ የትምህርትና ስልጠና አክሲዮን ማኅበር ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡
በኢትዮጵያ ትምህርትና ሥልጠና ታሪክ ውስጥ የተለየ ቦታ ያለው አልፋ የትምህርትና ሥልጠና አክስዮን ማኅበር፤ መሠረቱ “ብሔራዊ ሙያ-ነክ የተልዕኮ ትምህርት ድርጅት” የተባለው በአንድ ግለሰብ ንብረትነት በ1974 ዓ.ም የተቋቋመ ድርጅት ነው፡፡ ተቋሙ የተመሠረተበት ዓላማ፣ የዳበረ ልምድ እያላቸው የቀለም ትምህርታቸውን ያላሻሻሉ በርካታ ዜጐች፤ የንድፈ ሃሣብ እውቀታቸውንና የሙያ ክህሎታቸውን በርቀት ትምህርት አሳድገው ሕይወታቸውን እንዲለውጡ ለማስቻል ነበር፡፡
ይህ ተቋም በ1986 ዓ.ም ከግል ንብረትነት ወደ ብዙሃን ሐብትነት ተሸጋገረ፡፡ ስሙም “አልፋ የትምህርትና ስልጠና አክስዮን ማህበር ተሰኘ፡፡ ኩባንያው በ32 መሥራች አባላት የተቋቋመ ሲሆን እነዚህ አባላት መምህራን፣ የትምህርት ባለሙያዎችና የንግድ ማኅበረሰቡን ያካትታሉ፡፡ የዚህ ስብስብ አባላት ዓላማ በሀገራችን የትምህርትና ሥልጠና ሥራ በስፋትና በጥራት እንዲከናወን ተገቢውን የሙያ አስተዋጽኦ ለማድረግና በሂደቱም በሚገኝ ትርፍ ተጠቃሚ ለመሆን ነበር፡፡
ዛሬ ላይ ሆነን ስናሰላው “ብሔራዊ ሙያ ነክ የተልዕኮ ትምህርት ድርጅት” ከተመሠረተ 32 ዓመታት፣ “አልፋ የትምህርትና ሥልጠና አክሲዮን ማህበር” ከተመሠረተ ደግሞ 20 ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ኩባንያው በ1990ዎቹ መጨረሻ ዓመታት “የት ሊደርስ ነው” እንዳልተባለ ሁሉ በአሁኑ ወቅት ያለበት ደረጃ ግን በእጅጉ አሳዛኝና አሳሳቢ መሆኑ የማህበሩ አባላት ሁሉ የሚያውቁት እውነት ነው፡፡ በተለይም ከ1997 ዓ.ም እስከ 2000 ዓ.ም መግቢያ ድረስ የታየው ለውጥ “ተአምራዊ” የተባለ ነበር፡፡ ይህ ወቅት የአልፋ “ወርቃማ ዘመን” ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ለዚህ አኩሪ ውጤት መገኘት በወቅቱ የነበረው ቦርድ፣ የአልፋ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ማኔጅመንት የአመራር ብቃትና የሠራተኛው ታታሪነት ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ይሁንና ከ1999 ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ ግን የተለመደውና የተጠበቀው እድገቱ ሳይሆን የኋሊት ጉዞ ተጀመረ፡፡ ለዚህም ውድቀት መነሻ ከሆኑት ጉዳዮች አንዱ የዩኒቨርሲቲ ኮሌጁን ፈጣን እድገት ማስቀጠል ያስችላል ተብሎ በባለሙያዎቹ ለ5 ወራት ያህል በጥንቃቄ የተጠናው የአደረጃጀት ማሻሻያና መዋቅር ተግባራዊ እንዳይሆን መደረጉ ነው፡፡ ሌላው በዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ ሰፊ እውቀትና ልምድ የነበራቸው መምህራንና ባለሙያዎች ተቋሙን ለቀው እንዲሄዱ በመደረጉ የዩኒቨርሲቲውን እንቅስቃሴ በእጅጉ ሊጎዳው ችሏል፡፡
በአሁኑ ዘመን ሕዝባችን የትምህርትና ሥልጠናን ጠቀሜታ በከፍተኛ ደረጃ ተገንዝቦ ቅድሚያ ራሱንና ቤተሰቡን በትምህርት ለማነጽ ያለውን አቅም ሁሉ ለመጠቀም ወደ ኋላ በማይልበት በአሁኑ ወቅትና ሌሎች በኪራይ ቤት ሠርተው አትራፊ እየሆኑ ባሉበት ሁኔታ የአልፋ ግዙፍ ሕንፃዎች ተማሪ አልባ ሆነው ማየት እንኳን ሀብቱንና እውቀቱን ላፈሰሰበት ባለ ሐብት ለተላላፊ መንገደኛም በእጅጉ የሚያስቆጭ ነው፡፡
ለአክሲዮን ማህበሩ መውደቅ  “የመንግስት ፖሊሲ እና መመሪያዎች አላሰራም ማለት” እንደሆነ በተደጋጋሚ ይገለጻል፡፡ እውነቱ ግን ኩባንያው ያለውን የሰው፣ የቁሳቁስ እና የድርጅት ሀብት ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ያለ መምራት ችግር ነው፡፡ ይህ ሁሉ አሳዛኝ ሂደት ያሳሰባቸው የተወሰኑ የአክሲዮን አባላት፣ የኩባንያው ፈጣን የቁልቁለት ጉዞ ያቆም ዘንድ ከአመራሩ ጋር ለመመካከር መድረክ እንዲመቻች በተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርቡም ጥረታቸው ሰሚ በማጣቱ፣ የንግድ ሕጉ በሚያዝዘው መሠረት 10% ድርሻ ያላቸው ባለአክሲዮኖችን ፊርማ በማሰባሰብ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ እንዲጠራ ሰኔ 12 ቀን 2005 ዓ.ም ለቦርዱ ጥያቄ አቅርበው ነበር፡፡
ይሁን እንጂ ሌላ የመደበኛና ድንገተኛ ጉባዔው ስብስብ በመጀመሪያ ነሐሴ 27 ቀን 2005 ዓ.ም እንዲካሄድ ተወሰነ፡፡ ከዚያም እንደገና ይህ ውሣኔ ተሽሮ መስከረም 12 ቀን 2006 ዓ.ም እንዲካሄድ ከተባለና አባላትም በተለያየ መንገድ ጥሪውን እንዲያውቁ ከተደረገ በኋላ፣ ለ3ኛ ጊዜ ሃሣባቸውን በመለወጥ፣ መስከረም 5 ቀን 2006 ዓ.ም ስብሰባው እንዲካሄድ በሪፖርተር ጋዜጣ ጥሪ ተደርጎ ነበር፡፡ ከእነዚህ የስብሰባ ቀናት መለዋወጥ መረዳት የሚቻለው፣ አመራሩ በኩባንያው ላይ የተከሰተውን ችግር በቅንነት ለመፍታት ልባዊ ተነሳሽነት እንዳልነበረው ነው፡፡
ጥሪው ከልብ አለመሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ለምልአተ ጉባኤው አለመሟላት ከሚጠቀሱት ምክንያቶች ጥቂቶቹ፣ ጉባኤው የተካሄደበት እለት (መስከረም 5 ቀን) የአዲስ ዓመት መባቻ በመሆኑ አብዛኛው ባለ ሀብት ሊገኝ አለመቻሉ፣ ጥሪው በተገቢው ሁኔታ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን፣ በሬዲዮን፣ በጋዜጦች፣ በፖስታ መልዕክትና፣ በሞባይል ስልክ መልዕክት አለመተላለፉ እና ከፍተኛ የአክሲዮን ድርሻ ያላቸው የቦርድ አመራር አባላት ጭምር በጉባኤው ያለመገኘት የመሳሰሉት ናቸው፡፡ በመሆኑም ሕጉ በሚያዘው መሠረት ድጋሚ መጠራት የነበረበት ጉባኤ፣ በ15 ቀናት ውስጥ እንዲካሄድ የተደረሰው ስምምነትም ተግባራዊ ሳይደረግ ቀርቷል፡፡ አስተባባሪ ኮሚቴውም አቤቱታውን ለሚመለከተው የመንግስት መ/ቤት በወቅቱ አቅርቧል፡፡ አቤቱታ የቀረበለት የንግድ ሚኒስቴርም ስብሰባው ለምን በስምምነቱና በደንቡ መሠረት እንዳልተካሄደ ቦርዱን ጠርቶ ማብራሪያ እንዲሰጠው በጠየቀ ጊዜ “ወጪ ለመቀነስ ስለታሰበ” መደበኛውንና ድንገተኛ ጉባዔውን በማጣመር ማስኬድ በማስፈለጉ እንደሆነ ተገልጾለታል።በእርግጥ ስብሰባው ከዓመታዊ ጉባዔው ጋር ተጣምሮ እንዲካሄድ የተወሰነው “ወጪ ለመቀነስ ነው” የሚለው አካል፣ ለአልፋ ገንዘብ ቁጠባ አሳቢ ቢሆን ኖሮ፣ በርካታ ሊቆጠቡ የሚገባቸው ወጪዎች ላይ ጥንቃቄ ማድረግ በተቻለ ነበር፡፡ የንግድ ሚኒስቴር ግን ይህን ሀሳብ ተቀብሎ ጉባዔዎቹን በጥምር ማካሄድ እንደሚቻል፣ ነገር ግን የቅሬታ አቅራቢዎቹ አጀንዳዎች ያደሩ  በመሆናቸው በቅድሚያ ቀርበው ከታዩ በኋላ፣ የቦርዱ አጀንዳ እንዲቀርብ ስምምነት ላይ ተደርሶ ነበር፡፡ ይሁንና ቦርዱ የተደረሰውን ስምምነት እንደገና በማፍረስ የጠቅላላ ጉባኤውን ህዳር 15 ቀን 2006 ዓ.ም ለማካሄድ ባደረገው ጥሪም እና በዚህ ጥሪ ላይ በቀረፀው አጀንዳ ላይ አስተባባሪ ኮሚቴው ያቀረበው አንዱ አጀንዳ ብቻ (በ1.6ኛ ተራ ቁጥር ላይ ያለው) የተቀመጠ ሲሆን ሌላው የድንገተኛ ጉባኤ አጀንዳ ግን ጭራሽ አለመቅረቡን ጥቅምት 30 ቀን 2006 ዓ.ም በወጣው የአዲስ አድማስ ጋዜጣ መመልከት ይቻላል፡፡ ይህንንም ሁኔታ አስተባባሪ ኮሚቴው ለንግድ ሚኒስቴር እንደገና በአቤቱታ መልክ በማቅረብ፣ የቅሬታ አቅራቢ ባለአክስዮኖች አጀንዳ በቅድሚያ እንዲታይ ለቦርዱ ጥብቅ ትዕዛዝ ጽፏል፡፡ ይህ ጥብቅ ማሳሰቢያ ወደፊት በተሰጠው ማሳሰቢያ መሰረት የሚተገበር መሆን አለመሆኑን እድሜ ከሰጠን የምናየው ይሆናል፡፡
ውድ የተከበራችሁ የአልፋ ትምህርትና ሥልጠና አ.ማ ባለአክሲዮኖች፡- አክስዮን ማኅበራችንን ለማሳደግና ተጠቃሚ ለመሆን በዕውቀት፣ በጉልበትና በገንዘብ ተገቢውን ሁሉ ፈጽመን አንቱ የተባለ ኩባንያ መመስረት ችለን እንደነበር ይታወሳል፡፡ ሆኖም ግን ሁኔታዎች ሁሉ በሚፈለገው መንገድ እየሄዱ ባለመሆኑ፣ ሁሉም ባለ አክሲዮኖች ህዳር 15 ቀን 2006 ዓ.ም እንደሚካሄድ በወጣው ማስታወቂያ መሠረት፤ በስብሰባው ላይ በመገኘት በአክሲዮን ማህበሩ ችግሮች፣ መንስኤዎችና መፍትሄዎቻቸው ላይ በዝርዝር በመነጋገር በቀጣይ መወሰድ ስላለበት እርምጃ የበኩላችሁን አስተዋፅኦ ማድረግ ተገቢ ነው የሚል እምነት አለን፡፡ (ከቅሬታ አቅራቢ ባለአክሲዮኖች አስተባባሪ ኮሚቴ)  

Read 2749 times