Monday, 25 November 2013 11:01

“ኢትስ ጉድ ፎር ቢዝነስ…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(7 votes)

እንዴት ከረማችሁሳ!
ስሙኝማ…ይሄ አሥር በመቶ እውነት፣ ዘጠና በመቶ ሽወዳ በሆነበት የነጻ ትግሉ (WWE) ክትክት ላይ  “ኢትስ ጉድ ፎር ቢዝነስ” (“It’s good for business”) የሚሏት ነገር አለች፡፡ ያው ለ‘ቢዙ’ አሪፍ ነገር ማለት ነው፡፡
እናም…በዚህ በኳሳችን ብሔራዊ ስሜትንና “ኢትስ ጉድ ፎር ቢዝነስ” እየተደበላለቀ ሕዝቤ ደህና ንግዱን ሲያጧጡፍ ከረመ፡፡ በየመንገዱ ቀለም መቀባቱ፣ ካናቴራ፣ ስካርፍ፣ ኮፍያ፣ ባርኔጣ ምናምን መሸጡ በአብዛኛው የ‘ቢዙ’ ጉዳይ ነው፡፡ ይህን ሁሉ ‘ግርግር’ ሙሉ ለሙሉ እንደ ብሔራዊ ስሜት መግለጹ አሪፍ አይደለም፡፡
ስለ ቡድኑ በየኤፍኤሙ እንሰማቸው የነበሩ የሚያስገርሙ፣ አንዳንዴም የሚያስደነግጡ፣ ዘገባዎች… አለ አይደል… እውነተኛ አቋማችን ሆኖ ሳይሆን ነገርዬው “ኢትስ ጉድ ፎር ቢዝነስ” ነው። አሀ…የስፖንሰር ጉዳይ ነዋ! ስፖንሰሮች ደግ፣ ደግ እንዲወራ ይፈልጋሉዋ! የቡድኑ እዚህ መድረስ “የእንትናችን ውጤት ነው…” እየተባለ ነዋ!
የምር ግን…እንግዲህ ጨዋታም አይደል… አንዳንድ ዘገባዎች ‘ልማታዊ የስፖርት ዘገባዎች’ አይነት ሆኑብንሳ! (ስሙኝማ… ‘በቀጥታ ስርጭቱ’ ጊዜ በተደጋጋሚ “የእጅ ውርወራ” “የመልስ ምት” እየተባለ ሲጠቀስ ምን አልኩ መሰላችሁ…ፊፋ ሰሞኑን የለዋወጣቸው ህጎች አሉ እንዴ? ግራ ሲገባኝስ!)
ስሙኝማ…ይሄ የዳኝነት ነገር አስቸጋሪ ነው። የበቀደሙ ዳኛ ሆነ ብሎ በማዳላትም ይሁን፣ ‘ኢኖሰንት ሚስቴክ’ የሚሉትም አይነት ቢሆን አንዳንድ ነገር ላይ የተጫኑን ይመስላል፡፡ የዳኝነት ነገር ካነሳን ይቺን ስሙኝማ፡፡
ሦስት በዕድሜ የገፉ የእግር ኳስ ደጋፊዎች ለየቡደኖቻቸው እየጸለዩ ነው፡፡ አንደኛው ደጋፊ እንዲህ ይላል… “እግዚአብሔር ሆይ፣ ማንቼስተር ሲቲ ለዳኞች ጉቦ መስጠት የሚያቆመው መቼ ነው?”
“በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት” ሲል እግዚአብሔር ይመልሳል፡፡
ሰውየውም “እስከዛማ እኔ እሞታለሁ” ይላል፡፡
ሁለተኛው ደጋፊ እንዲህ ይላል… “እግዚአብሔር ሆይ፣ ማንቼስተር ዩናይትድ ለዳኞች ጉቦ መስጠት የሚያቆመው መቼ ነው?”
“በሚቀጥሉት አሥር ዓመታት” ሲል እግዚአብሔር ይመልሳል፡፡
ሦስተኛው ደጋፊ እንዲህ ይላል… “እግዚአብሔር ሆይ፣ ባርሴሎና ለዳኞች ጉቦ መስጠት የሚያቆመው መቼ ነው?”
እግዚአብሔር ምን ቢል ጥሩ ነው፣ “እስከዛማ እኔ እሞታለሁ፡፡”
እናማ…በተከታታይ ዳኞች ጎል በመከልከልና በጣም፣ እጅግ በጣም አጠያያቂ ፍጹም ቅጣት በመስጠት የተጫኑን ሆነ ተብሎ ይሁን የችሎታ ማነስ ወይም ሌላ አንድዬ ይወቀው፡፡  
እናላችሁ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል… አንድ ግዙፍ የስፖርት ሚዲያ በድረ ገጹ የኢትዮዽያን ቡድን አድንቆ ናይጄሪያን ሊያሸንፍ እንደሚችል ጻፈ የሚባል ነገር በአንዱ የእኛው ሜዲያ ሰማሁላችሁና ወዲያውኑ ተጻፈበት የታበለለትን ድረ ገጹን አየሁት። እናላችሁ… ስለ ጨዋታው ያወራና መጨረሻ ምን ይላል መሰላችሁ… “Definitely the African champions will finish off the Ethiopians in Calabar this Saturday and book their place at the 2014 Fifa World Cup in Brazil.”
ምንም ‘የፈረንጅ አፍ’ ቢቸግረን ይቺ አትጠፋንማ! ናይጄሪያ “በእርግጠኝነት…” ቡድናችንን እንደሚያሸንፈው የሚናገር መሰለኝ። (“‘የፈረንጅ አፍ’ እንደፈቺው ነው…” ተብሎ ሌላ ትርጉም ካልተሰጠው በስተቀር፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…)
እናማ “ዓለም አደነቀን…”፣ ወይም “ዓለምን እያስደመመን ነው…” እየተባለ ድረ ገጾች ያልጻፉት ነገር እንደጻፉት ሲነግሩን የሰማንባቸው ጊዜያት አሉ። ምክንያቱም እንደዚሀ አይነት አዘጋጋብ “ኢትስ ጉድ ፎር ቢዝነስ” …አንደኛ ስፖንሰር አያስከፋም፣ ሁለተኛ ልማታዊ ነገርም ይሆናል፣ ሦስተኛ የኔኦ ሊበራሊስቶችን ወሽመጥ ይበጥሳል! ቂ..ቂ…ቂ…፡፡
እናላችሁ… ብሔራዊ ስሜት የሚያስፈልግባቸው በርካታ ነገሮች አሉ፡፡ ለብዙ ችግሮች ያጋለጠን የብሔራዊ ስሜት መጥፋት ነው፤ እርስ በእርስ መደማመጥ ያቃተን የብሔራዊ ስሜት መጥፋት ነው፣ ዘረኞች ያደረገን፣ ጎጠኞች ያደረገን “በእርግጠኝነት” የብሔራዊ ስሜት መጥፋት ነው። ሁሉን ነገር በአመቻ ጋብቻ እንድንሠራ እያደረገን ያለው የብሔራዊ ስሜት መጥፋት ነው፡፡ በአገሪቷ የልጅና የእንጀራ ልጅ አይነት አገልግሎት አሰጣጥ ባህል እንዲሆን ያደረገው የብሔራዊ ስሜት መጥፋት ነው፡፡ እናማ… በአንድ ልብ ማሰብ፣ በአንድ ድምጽ መጮህ ምን ያህል እንደሚያረካ ‘ሳምፕሉን’ እንድናይ ላደረገን ብሔራዊ ቡድናችን ምስጋና ይግባው!
ስለ ብሔራዊ ስሜት ካነሳን አይቀር ይቺን ስሙኝማ…የኤፍ.ቢ.አይ. ሰዎች ሰላይ ለመቅጠር ሦስት ዕጩዎችን በተናጥል ቃለ መጠይቅ እያደረጉ ነው፡፡
የመጀመሪያውን ሰው “ሚስትህን ትወዳለህ?” ተብሎ ይጠየቃል፡፡
“አዎ፣ ጌታዬ እወዳታለሁ”
“አገርህን ትወዳታለህ?”
“ከሚስትህና ከአገርህ ይበልጥ የምትወደው የትኛዋን ነው?”
ከዛ ሽጉጥ ይሰጠውና “እንግዲያው፣ ሚስትህ የሚቀጥለው ክፍል ነች ግባና ግደላት” ይባላል። ሰውየውም ሽጉጡን ያስቀምጥና “ይሄን እንኳን ማድረግ አልችልም…” ብሎ ወጥቶ ይሄዳል፡፡
ሁለተኛው ሰው ተመሳሳይ ጥያቄዎች ይቀርቡለትና ሽጉጥ ይዞ ሚስቱ ያለችበት ክፍል ይገባል፡፡ ለአምስት ደቂቃ ቆይቶ ይወጣል፡፡ “ይህንን እንኳን ማድረግ አልችልም…” ብሎ ሽጉጡን አስቀምጦ ይሄዳል፡፡
ሦስተኛው ሰው ተመሳሳይ ጥያቄዎች ቀርበውለት ሽጉጥ ይዞ ይገባል፡፡ የታፈኑ የተኩስ ድምጾች ይሰማሉ፡፡ ጥቂት ቆይቶ የመንኳኳት ድምጾች ይሰማሉ፡፡ ከዛም ሰውየው ከረባቱ ላልቶ፣ የሸሚዙ እጅጌዎች ተሰብስበው ከክፍሉ ይወጣል፡፡ ሽጉጡንም ጠረዼዛው ላይ ያስቀምጣል፡፡
ቃለ መጠይቅ አድራጊዎቹም “ምን ተፈጠረ?” ብለው ይጠይቁታል፡፡
ሰውየው ምን አለ መሰላችሁ… “ጥይቶቹ የውሸት ስለነበሩ በእጄ አንቄ ገደልኳት፡፡”
ሚስትን አንቆ ‘ጭጭ የሚያስደርግ’ ባይሆንም ትንንሽ እንጥፍጣፊ ብሔራዊ ስሜት ብዙ በጎ ነገሮች ለማድረግ የሚያግዝ ይመስለኛል፡፡
እናማ…ከዚህ በፊት እንዳወራነው የዘንድሮ ብሔራዊ ቡድናችን ሁላችንም ለአንድ ጉዳይ እኩል እንድንጮህ አድርጎናል፡፡ የበይ ተመልካች ሆነን የኖርንበት ዓለም ዋንጫ ደጃፍ ደርሰን በሩን እንድናንኳኳ አድርጎናል፡፡ ታፔላ ሳንለጣጥፍ፣ ሳንወጋገዝ፣ “ቡድኑን እንዲህ የሚሉት የራሳቸው ዓላማ ያላቸው…” ምናምን ሳንባባል…እኩል “ሆ!” እንድንል አድርጎናል፡፡ አ
ንድዬ ይሄን አይነቱ ጸጋ በሁሉም ነገሮች ላይ እንዲገጥመን ያድርግልንማ!
ምስጋናና ክብር ለብሔራዊ ቡድናችን!
አንድዬ ደግሞ በር አንኳኩቶ የሚመለስ ብቻ ሳይሆን በሩን አስከፍቶ የሚገባ ቡድንም እንዲኖረን ይርዳንማ፡፡ እንዲህ አይነቱን ቡድን ለማየት ዕድሜና ጤናውን ያድለንማ!
እግረ መንገዴን ይቺን ስሙኝማ…አንድ መልዐክ ይመጣና አንዱን ሰውዬ “የምትፈልገውን አንድ ምኞት ንገረኝና አስፈጽምልሀለሁ! ይለዋል፡፡ ሰውየውም “ለዘለዓለም መኖር እፈልጋለሁ” ሲል ይመልሳል፡፡ መልዐኩም “አዝናለሁ፣ እንደዛ አይነት ምኞቶችን የመፈጸም ስልጣን አልተሰጠኝም፡፡”
ሰውየውም ምን ይላል “እሺ፣ እንደዛ ከሆነ ሊቨርፑል የፕሬሚየር ሊጉን ዋንጫ ሲበላ መሞት እፈልጋለሁ፡፡”
መልዐኩ ሳቅ ብሎ ምን ቢለው ጥሩ ነው… “በጣም ብልጥ ነህ፣ ለብዙ አሥርት ዓመታት መኖር ትፈልጋለሀ ማለት ነው፡፡”
ትልቁ የእግር ኳስ አደባባይ ለመገኘት ለብዙ አሥርት ዓመታት ከመጠበቅ ያድነንማ!
ደግሞላችሁ… ሁሉም ነገር “ኢትስ ጉድ ፎር ቢዝነስ” እየተባለ መቀባባትና መኳኳል ከቀጠለ የመልዐኩ “በጣም ብልጥ ነህ…” ነገር አይለቀንም፡፡
 ሦስት ደጋፊዎች ውጤት ማምጣት ስላቃተውና ስለሚደግፉት የከተማቸው ቡድን እያወሩ ነበር፡፡
አንደኛው ምን ይላል…“ጥፋቱ የአሰልጣኙ ነው፣ የተሻሉ ተጫዋቾች ቢያስፈርም ኖሮ ቡድናችን ትልቅ ይሆን ነበር፡፡”
ሁለተኛው ደግሞ “ጥፋቱ የተጫዋቾች ነው፡፡ የተሻለ ጥረት ቢያደርጉ ኖሮ ብዙ ጎሎች እናስቆጥር ነበር” ይላል፡፡ሦስተኛው ደጋፊ ምን ቢል ጥሩ ነው… “ጥፋቱ የወላጆቼ ነው፣ ሌላ ከተማ ወልደውኝ ቢሆን ኖሮ የተሻለ ቡድን ደጋፊ እሆን ነበር፡፡”
እናላችሁ…የትም እንወለድ የትም ትልቅ የነበረች አገር ዜጎች ነንና…ትልቅ መሆን የምትችል አገር ዜጎች ነንና…ይዋል ይደርም ወደ ትልቅነቷ የምትመለስ አገር ዜጎች ነንና… ብሔራዊ ቡድናችን የተሻለ ሆኖ ለማየት ያብቃንማ!
ብሔራዊ ስሜት…አለ አይደል…“ኢትስ ጉድ ፎር ቢዝነስ” ከሚለው ዳሌን የማስፋትና ሻኛን የመከመር ‘ሆድ—ተኮር’ አስተሳሰብ የላቀ መሆኑን አንድዬ በየልቦናችን ያስርጽብንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 2905 times