Saturday, 01 June 2013 14:27

የአውሮፓ ህብረት አምባሳደር ዣቪየ ማርሻል አረፉ

Written by 
Rate this item
(4 votes)

የአውሮፓ ህብረት የኢትዮጵያ ልኡክ ጽ/ቤት ሃላፊ የነበሩት አምባሳደር ዣቪየ ማርሻል ባደረባቸው የአጭር ጊዜ ህመም ቤልጅየም ብራሰልስ በሚገኘው ቅድስት ኤልሳቤጥ ሆስፒታል በህክምና ሲረዱ ቆይተው፣ ባለፈው ቅዳሜ ግንቦት 17 ቀን 2005 ዓ.ም በተወለዱ በስልሳ አንድ አመታቸው ከዚህ አለም በሞት ተለይተዋል፡፡ አምባሳደር ማርሻል ከተሾሙበት እ.ኤ.አ ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ ላለፉት ሶስት አመት ተኩል የአውሮፓ ህብረት የኢትዮጵያ ልኡክ ጽ/ቤትን በአምባሳደርነት መርተዋል፡፡ በአምባሳደርነት ባገለገሉበት በዚህ ወቅትም በአውሮፓ ህብረትና በኢትዮጵያ መካከል ያለው ግንኙነትና የልማት ትብብር በከፍተኛ ደረጃ እንዲጠናከር ያላሰለሰ ጥረት አድርገዋል፡፡ አምባሳደሩ በ1988 ዓ.ም የአውሮፓ ኮሚሽንን የተቀላቀሉ ሲሆን በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ በሞሮኮ እንዲሁም በሶሪያ በሚገኙት የህብረቱ ልኡክ ጽ/ቤቶች በአማካሪነት አገልግለዋል፡፡

ከ1999 እስከ 2010 ዓ.ም ድረስ ደግሞ በሱዳንና በዚምባብዌ የአውሮፓ ህብረት አምባሳደር ነበሩ፡፡ በግብርና ስራ ተሰማርተው ከነበሩ ቤልጅየማዊ ቤተሰቦች በኮንጐ ዲሞክራቲክ ሪፖብሊክ ውስጥ በ1952 ዓ.ም የወለዱትና የግብርና ባለሙያ የሆኑት አምባሳደር ማርሻል፣ ለግብርና ሙያና ለአርሶ አደሮች ልዩና ስስ ልብ ነበራቸው፡፡ የኢትዮጵያን የገጠር አርሶ አደሮች ለመርዳት በሙሉ ሃይላቸውና በከፍተኛ ስሜት ያደረጉት ጥረት የአርሶ አደሮችንና የኢትዮጵያ መንግስትን ድጋፍና ከበሬታ አስገኝቶላቸዋል፡፡

ለኢትዮጵያ ህዝቦች፣ ለዱር እንስሳቶቿና ለተፈጥሮ አካባቢዋ የነበራቸው ፍቅር ወሰን አልነበረውም፡፡ ለዱር እንስሳትና ለአካባቢ ጥበቃ ያደርጉት የነበረው ጥረት፣ የላቀና በምሳሌነት የሚጠቀስ ነበር፡፡ ልማት፣ ሰላምና የአካባቢ ጥበቃ ያላቸውን የእርስ በርስ መስተጋብር እንዲጋሩ የአውሮፓና የሌሎች ሀገራት አምባሳደሮችን በማስተባበር የሰሜን ተራሮችን፣ በምዕራብና ደቡብ ኢትዮጵያ የሚገኙ ደኖችንና የቡና እርሻዎችን እንዲጐበኙ አድርገዋል፡፡ አምባሳደር ማርሻል ምንም እንኳ በቢሮ ውስጥ ከመቀመጥ ይልቅ በባሌ ወይም በሰሜን ተራሮች ላይ ድንኳን ተክለው ቢሰሩ በእጅጉ እንደሚያስደስታቸው የታወቀ ቢሆንም በስራ አመራራቸው፣ የስራ ባልደረቦቻቸውን በማስተባበርና በማነቃቃት ረገድ የባልደረቦቻቸውን አድናቆትና ከበሬታ ያስገኘ ችሎታ ነበራቸው፡፡ አምባሳደር ማርሻል ባለትዳርና የአንድ ወንድና የሁለት ሴቶች ልጆች አባት ነበሩ፡፡

Read 2930 times