Saturday, 01 June 2013 12:41

ዊል ስሚዝ፣ የስንት ቢሊዮን ሰው ህይወት አድኗል?

Written by 
Rate this item
(2 votes)

በራፕ የሙዚቃ ስልት የሰው ጆሮ ውስጥ ለመግባት የቻለው ዊል ስሚዝ፤ አሁን በሚታወቅበት የፊልም አለም የሰው አይን ውስጥ የገባው በአጋጣሚ አይደለም። በአገራችን እንደተለመደው፤ “የጥበብ አድባር ጠርታኝ…” ምናምን ብሎ ነገር የለም - በሆሊውድ። ዊል ስሚዝ፣ አይቶና አስቦ፣ አስልቶና ቀምሮ ነው ወደ ሆሊውድ መንደር የዘለቀው። “በተመልካች ብዛትና በትፋማነት፣ በተወዳጅነትና በኦስካር ሽልማት ሪከርድ የሰበሩ ፊልሞች ምን አይነት ናቸው?” የሚል ጥያቄ ነው የዊል ስሚዝ መነሻ። የብዙ አመት መረጃዎች ተሰበሰቡ። ከአንድ እስከ አስር የወጡት ፊልሞች፣ አንድ በአንድ ተመረመሩ። ከአስሩ መካከል ሰባቱ፣ “የሳይንስ ፊክሽን ፊልሞች ናቸው። ከእነዚህም መካከልም በርካታዎቹ ፊልሞች ውስጥ፣ ልዩ ፍጡራን ወይም የሌላ አለም “ሰዎች” ይታያሉ።

በተወዳጅነትና በትርፋማነት ብቻ ሳይሆን፣ ብዙ የኦስካር ሽልማት በማግኘትም፣ የሳይንስ ፊክሽን ፊልሞች ቀዳሚ መሆናቸውን የተመለከተው ዊል ስሚዝ፣ ለኤጀንቱ የሰጠው “መመሪያ” አጭርና ግልፅ ነበር - “የሳይንስ ፊክሽን ፊልም ውስጥ መስራት ይኖርብናል” የሚል። ልክ ያጣ ድፍረት ይመስላል። ምክንያቱም፣ ዊል ስሚዝ በወቅቱ፣ በአንድ የቴሌቪዥን ድራማ ላይ ቢሰራም፣ በሆሊውድ ፊልም ላይ አንድም ጊዜ ሳይሳተፍ ነው፣ ፊልም አማርጦ ለመስራት የፈለገው። ግን እንዳሰበው ተሳካለት። ‘ባድ ቦይስ’ ከተሰኘው አክሽን ፊልም በመቀጠል፣ ዊል ስሚዝ በሰፊው ለመታወቅ የበቃው ‘ኢንዲፐንደንስ ዴይ’ በተሰኘው የሳይንስ ፊክሺን ፊልም ላይ ነው። ከሌላ አለም የመጡ ፍጡራን የሰው ዘርን ለማጥፋትና አለምን ለማውደም ዘመቻ ሲያካሂዱ በሚታዩበት በዚሁ ፊልም አለምን ከጥፋት፣ የሰው ልጅን ከእልቂት የሚታደጋቸው ዊል ስሚዝ ነው። ከዚያም ‘ሜን ኢን ብላክ’ በተሰኙ ሶስት ፊልሞች ላይ፣ ከሌላ አለም የሚመጡ ልዩ ፍጡራንን እየተጋፈጠ ምድርንና የሰው ዘርን ከጥፋት ሲያድን ይታያል።

በዚህም አላበቃም፤ ‘አይ ሮቦት’ ፊልም ላይ እንደገና አለምን ከክፉ ሮቦቶች ያድናታል። ‘አይ አም ሌጀንድ’ በተሰኘው ፊልም፤ የሰው ዘር በክፉ የበሽታ ወረርሽን ጨርሶ እንዳይጠፋ የሚያደርገው ዊል ስሚዝ ነው። ‘ሃንኩክ’ ፊልም ላይም፣ የሰው ልጅን ከጥፋት ይታደጋል። የዊል ስሚዝ ሚስት ጃዳ በበኩሏ፣ በሁለት የ‘ማትሪክስ’ ፊልሞች የድርሻዋን ትወጣለች። የ14 አመቱ ልጃቸው ጃደን ደግሞ፣ በሶስት ፊልሞች የአባትና የእናቱን መንገድ ተከትሎ እየሰራ ነው። ትንሿ ልጃቸው ዊሎው እስካሁን በአንድ ፊልም ላይ ሰርታለች። ለመሆኑ ዊል ስሚዝ እስካሁን በሰራቸው ፊልሞች የስንት ሰው ህይወት አድኗል? ታዋቂው ዋየርድ መጽሔት ሰሞኑን እንደዘገበው ከሆነ፣ ዊል ስሚዝ ከነቤተሰቡ፣ እስካሁን ከ63 ቢሊዮን በላይ ሰዎችን ከእልቂጥ አድኗል ብሏል።

ከአለም የህዝብ ቁጥር በዘጠኝ እጥፍ የሚበልጡ ሰዎች፣ በዊል ስሚዝ ቤተሰቦች ጀግንነት ከእልቂት ተርፈዋል - በፊልም ውስጥ። በእውነተኛው አለም ደግሞ፣ ዊል ስሚዝና ቤተሰቦቹ የተሳተፉባቸው ፊልሞች፣ 6 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ገቢ እንዳስገኙ ዋየርድ ገልጿል። ዊል ስሚዝና የ14 አመት ልጁ ጃደን የሰሩበት አዲሱ “አፍተር ኧርዝ” የተሰኘው ፊልም ላይ ግን፣ አለማችን ኦና ሆናለች። የሰው ዘር የላትም - የሰው ዘርን በሚያጠፉ አውሬዎች ተሞልታለች። ዊል ስሚዝና ጃደን፣ በዚህ ፊልም ሌሎች ሰዎችን ሳይሆን የራሳቸውን ሕይወት ከሞት ለማዳን ይታገላሉ።

Read 4430 times