Saturday, 18 May 2013 10:51

ማንንም ሰው በሙስና ለመያዝ ጠ/ሚኒስትሩን አንጠይቅም

Written by 
Rate this item
(7 votes)

የሰሞኑ የከተማችን አብይ አጀንዳ የገቢዎችና የጉምሩክ ባለስልጣን ዋና ሃላፊዎችና ትላልቅ ባለሃብቶች በሙስና ተጠርጥረው መያዛቸው ነው፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ሰላም ገረመው የፌደራል ሥነ ምግባር እና ፀረ - ሙስና ኮሚሽን፣ የስነምግባር ትምህርት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ከሆኑት አቶ ብርሃኑ አሰፋ ጋር በወቅታዊ የሙስና ጉዳዮች ዙሪያ ቃለምልልስ አድርጋለች፡፡ የሙስና ድርጊቶች እየተባባሱ መምጣታቸውን የሚናገሩ ወገኖች አሉ፡፡ እርስዎ ምን ይላሉ? የሙስና ተግባር በአለም አቀፍ ደረጃ ነው የሚታየው፡፡ ድንበር ተሻጋሪ ነው፡፡ በአንድ አገር ብቻ ተወስኖ የሚቀርብ ችግር አይደለም። ከሽብርተኝነት ቀጥሎ ሙስና አገርን የሚጐዳ እና እያሳሰበ ያለ ተግባር ነው፡፡ ዛሬ በዓለም ላይ የሚከናወኑ የእርዳታ እና የብድር ጉዳዮች እንዲሁም የንግድ ኢንቨስትመንቶች ሁሉ ከፍተኛ የገንዘብ እንቅስቃሴ የሚካሄድባቸው ናቸው፡፡ ከዚህ አኳያ ሙስና እንዳይስፋፋ አለም በደንብ ተጠናክሮ መስራት አለበት፡፡ ከዛ ውጪ በሙስና የተገኙ ገንዘቦች ህገወጥ በሆነ መንገድ ለተለያዩ ስራዎች የሚውሉበት ጊዜ አለ፡፡ አንዳንዴ ለሽብር ተግባር ሊውል ይችላል፡፡

ስለዚህ ከአለም አኳያ ስናየው የአለምን አጠቃላይ ሁኔታ ሊያናጋ የሚችል መሆኑን ሁሉም ተረድቶታል፡፡ በርካታ ስምምነቶች እየወጡ እየተሠሩበት ይገኛል፡፡ እኛ አገርም ስንመጣ ይሔ የሙስና ተግባር ትኩረት ካላገኘ አደጋ መሆኑ በመንግስት ታምኖበታል፡፡ የመንግስት የመልካም አስተዳደር ግንባታ ስራዎች ስኬታማ ሊሆኑ የሚችሉት ሙስናን መከላከል ስንችል ነው፡፡ ከድህነት ለመውጣት የምናደርገውን ጥረት ያደናቅፋል፡፡ ሙስና ለመብራት፣ ለውሀ፣ ለስልክ፣ ለት/ቤት በአጠቃላይ ለመሠረተ ልማት ግንባታና ለህብረተሠቡ የኑሮ መሻሻል የምናደርጋቸውን እንቅስቃሴዎች በተለያየ መንገድ ይጐዳል፡፡

የዲሞክራሲ ስርአት፣ የህግ የበላይነት፣ የመንግስት ተጠያቂነትና ሁሉም በህግ ፊት እኩል እንዳይሆን የማድረግ ተጽእኖም አለው። አንዳንድ ግለሰቦች በሀቅ ማግኘት ካለባቸው ውጪ ያለ አግባብ እንዲበለጽጉ ያደርጋል፡፡ ይሔ ሁሉ ተደምሮ ከድህነትና ከችግር እንዳንወጣ መሰናክል ይሆንብናል፡፡ መንግስት ይህንን በመመልከት ነው በክልል ደረጃ ዘጠኝ የሚሆኑ ቅርንጫፎችን በመክፈት፤ በፌደራል ደረጃ የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ያቋቋመው፡፡ ኮሚሽኑ ማስተባበር እና መምራት ነው እንጂ ሁሉን ነገር ተክቶ አይሠራም፡፡ ከሚዲያ፣ ከሀይማኖት ተቋማት፣ ከሙያ ማህበራት፣ ከንግዱ ማህበራት፣ እንዲሁም መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር ግንኙነት እየፈጠርን መንግስትና ህዝቡ በጋራ የሚሠሩበትን ሁኔታ እያመቻቸን ነው፡፡ የባለሥልጣናትን ሃብት መዝግቦ ይፋ የማድረግ ሂደቱ ዘግይቷል ይባላል? ሀብትና ንብረትን ማሳወቅ ሲሆን ሙስናን ከመከላከል ተግባራት አንዱ ነው፡፡ እንግዲህ ከሁለት አመት ተኩል ጀምሮ ወደ 50ሺህ የሚሆኑ ሀብት ንብረታቸውን ማስመዝገብ የሚገባቸው ሠዎችን መዝግበናል፡፡ መረጃቸውን በሀርድ ኮፒ (በማንዋል) ለማዘጋጀት አስበን እየሠራን ነው፡፡

በዚህ በኩል ብዙ ጥያቄዎች እንዳሉ እናምናለን፤ ነገር ግን ኮሚሽኑም ይሔንን ሀብት ይፋ የማድረጉን ስራ በኢንተርኔት ለማንኛውም ሠው እንዲደርስ ነው ስትራቴጂ የቀየሠው፡፡ ይሔ ሲሆን በቀላሉ ማንም ሠው መረጃውን ማግኘት ይችላል፡፡ መረጃ ለህብረተሠቡ የሚሠጠው ያለ ምክንያት አይደለም። ያልተመዘገቡ ሀብትና ንብረቶች ካሉ፣ ምንጩ ያልታወቀ ሀብትና ንብረት እንዲያሳውቅ ለማድረግ ነው፡፡ ከህብረተሠቡ የሚደበቅ ነገር የለም፡፡ ቢዘገይም ከአለም ባንክ ጋር በመተባበር ይሔንን ስራ ለማካሔድና ግዢ ለማከናወን በእንቅስቃሴ ላይ እንገኛለን፡፡ እስከዛ ግን በማንዋል ደረጃም ቢሆን መረጃ ሲጠየቅ እንሰጣለን፡፡ እስካሁንም የሀያ ሶስት ሠዎችን መረጃ ተጠይቀን የሠጠንበት ሁኔታ አለ፡፡ እኛም ለምርመራ እነዚህን ሠነዶች እየተጠቅምን ነው፡፡

ቀደም ሲል ካሠብነው በላይ ነው የተመዘገበው፡፡ እኛ ያሠብነው 22ሺህ ነበር፤ አሁን ግን 50ሺህ ሠዎች ተመዝግበዋል፡፡ ይሔ አሠራር ለእኛ አዲስ ነው፤ ስለዚህ ከሌሎች አገራት ልምድ በመውሠድ እየሠራን ነው፡፡ በገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ከፍተኛ ሃላፊዎችና ባለሀብቶች ላይ ያደረጋችሁት ምርመራ አንድ አመት ተኩል የፈጀ ነው ተብሏል፡፡ እንዴት ይሔን ያህል ጊዜ ሊወስድ ቻለ? የምርመራው ሒደት እንዴት ተከናወነ፣ ለምን ተከናወነ የሚለውን ብዙም አላውቅም፡፡ ነገር ግን በዚህ ረገድ የሚከናወኑ የሙስና ወንጀሎች በጣም ውስብስብ እንደሆኑ መረዳት ይቻላል። ተጠርጣሪዎቹ ከፍተኛ ባለስልጣናት ያሉበት በመሆኑ ብዙ ጊዜ ይወስዳል፡፡ ከዛ ውጪ ትልቅ የሙስና ድርጊት ነው ብለን ስለምናምን፣ ጉዳዩን በጠንካራ ማስረጃ ላይ ተመስርቶ ለማቅረብ፣ በፍ/ቤትም የተሻለ ውጤት ለመፍጠር ታስቦ የተካሔደ ምርመራ መሆኑን አውቃለሁ፡፡ ከዛ ውጪ የቀድሞ ጠ/ሚኒስትር ክቡር አቶ መለስ ዜናዊ የሚከታተሉት የምርመራ ጉዳይ ነበር፡፡

እሳቸው ምርመራው ወደ መጨረሻ ደረጃ ላይ ሲደርስ ከዚህ አለም በሞት መለየታቸው እና ከዛ በኋላም ደግሞ የመተካካቱ ሒደት ስራው በፍጥነት እንዳይካሔድ የራሱ አስተዋፅኦ ነበረው፡፡ በዚህ ምክንያት ሰባት ስምንት ወር ዘግይቷል፡፡ የሰሞኑ ባለስልጣናትና ባለሀብቶች የተጠረጠሩበት የሙስና መጠን ከፍተኛ ነው ይባላል፡፡ ከፍተኛ ሲባል ምን ያህል ነው? እስካሁን የምርመራ ስራዎቻችንን አላጠናቀቅንም፡፡ ቢያንስ ምርመራውን ሊያጠናክሩና ክስ ሊያስከስሱ የሚችሉ መሠረታዊ ጭብጦችን የሚያስይዙ መረጃዎችና ማስረጃዎች እንደተሠበሠቡ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን ተጨማሪ ምርመራ የሚፈልጉ ነገሮች አሉ፡፡ የሠው ምስክር ሊሆን ይችላል፡፡ እነዚህን በማጠናከር ላይ ነው የምንገኘው፡፡ ስለዚህ ጥፋቶች በማን ተፈፀሙ፣ ማን በምን መልኩ የሚለውን በዝርዝር ምላሽ የምናገኘው ወደፊት ነው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ግን ይሔንን ሁሉ ጊዜ ተወስዶ የተመረመረ መሆኑ በራሱ የጉዳዩን ትልቅነት የሚያሳይ ነው፡፡ ዝርዝር ጉዳዩን ማወቅ የሚቻለው ግን ወደፊት በፍርድ ሒደት ነው፡፡

የተጠርጣሪዎቹ የሀብት መጠን ተመዝግቧል? ሀብት የማስመዝገብ ሀላፊነት የተጣለባቸው ወገኖች፣ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ሠራተኞችን ሃብት እንደመዘገቡ አውቃለሁ፡፡ አካባቢው እና ዘርፉ ለሙስና የተጋለጠ በመሆኑ ሁሉም እንደተመዘገቡ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ሌሎቹ ግን ባለሀብቶች ናቸው፡፡ የግል ንግድ ላይ የተሠማሩት ስለማይመዘገቡ የእነሱ አይታወቅም፡፡ የሀብታቸውን መጠን ማወቅ ይቻላል? በአሁኑ ጊዜ ማሳወቅ ይከብዳል፤ ወደፊት ይፋ ይሆናል፡፡ “ግንዱ አልተነካም ቅርንጫፉም ጥቂቱ ነው የተነካው” የሚሉ ወገኖች አሉ … በመጀመሪያ ደረጃ እኛ የምንይዘው ሠውን አይተን አይደለም፡፡ እኛ የምናየው ምን አይነት የሙስና ወንጀል ወይም ድርጊት ተፈፅሟል የሚለውን ነው፡፡ ኮሚሽኑ ከዚህ በፊትም ቢሆን ከፍተኛ ባለስልጣናት እንዲጠየቁ የሚያደርግበት አሰራር ነበረው፡፡

እነዚህ ሠዎች የሚጠየቁት ከፍተኛ ባለስልጣናት ስለሆኑ ሳይሆን የሙስና ወንጀልን ስለፈፀሙ ነው፡፡ ትንሽም ይሁን ትልቅ ባለስልጣን መነሻችን ይሔ ነው፡፡ ከህግ በላይ የሆነ የለም፡፡ ከዚህ በፊትም ይሔንን ስናደርግ ነበር። ምናልባት በአሁኑ ሠአት በህዝቡ ውስጥ የተለየ ስሜት ፈጥሮ ሊሆን ይችላል፡፡ አሁን በመልካም አስተዳደር ችግሮች ለየት ባለ መልኩ የህዝብ እሮሮ በማየሉ ሊሆን ይችላል። አሁን የተያዙት ቅርንጫፎቹ ናቸው ግንዶቹ አይደሉም ያሉት። እንግዲህ ከሚኒስትር በላይ ግንዱ የቱ እንደሆነ ቢነግሩን ጥሩ ነው፡፡ ዞሮ ዞሮ እኛ የሙስና ወንጀል እስከተፈፀመ ድረስ ማንንም በህግ እንጠይቃለን፡፡ ፀረ-ሙስና ከዚህ በፊት ትልልቅ ባለሥልጣናትን ለምን እንደማይከስ ተጠይቆ፣ በእኛ አገር እየታየ ያለው ሙስና በጣም ጥቃቅን ነው የሚል መልስ ሠጥቷል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታስ ትልልቅ ሙስናዎች እየተፈፀሙ ነው ለማለት ያስችላል? ኮሚሽኑ ትልቅ የሙስና ወንጀል እኛ አገር የለም ብሎ የተናገረበትን ጊዜ አላስታውስም። እኛ አገር ትላልቅ የሙስና ወንጀሎች አሉ፡፡ አጋጥሞን መርምረን ለህግ ያቀረብንበት ጊዜ አለ።

የአሁኑም ተመሳሳይ ነው፡፡ ከዚህ በፊት ከወርቅ ማጭበርበር ጋር ተያያዞ 153 ሚሊዮን ብር፣ በቴሌ የግዢ ጨረታ 1.8 ቢሊዮን ብር እንዲሁም በመሬት አስተዳደር ላይ ያደረግናቸው እንቅስቃሴዎች አሉ፡፡ ከዛ በኋላም የኤሌክትሪክ ሀይልን ቆጣሪ በማዘዋወር ከ60 ሚሊዮን ብር በላይና ከአገር ሊወጡ የነበሩ ወርቆችን የመሳሰሉ ትላልቅ የሙስና ወንጀሎችን መርምረናል። ሠርተናል፡፡ አንዳንድ ጊዜ እንደዚህ አይነት ሙስናዎች በትላልቅ ባለስልጣን መፈፀማቸው ወይም የገንዘቡ መጠን “ግራንድ ኮራፕሽን” ሊያሠኝ ይችላል፡፡ አንዳንዴ በአገሪቱ ደህንነትና ፀጥታ ላይ የሚያደርሠው ጉዳትም “ግራንድ ኮራፕሽን” ያሰኘዋል፡፡ አሁንም ትላልቅ ባለስልጣናት ላይ የሠራናቸው ምርመራዎች አሉ። ቁምነገሩ ትላልቅ ሙስናዎች አይፈፀሙም ሳይሆን የትኛው ይበዛል የሚለው ነው፡፡ ጥናቶች እንደሚያሳዩት፤ በአብዛኛው በኢትዮጵያ ውስጥ አነስተኛ ሙስና የምንላቸው ጐልተው ይታያሉ።

በቅርቡ ያካሔድነው የኢትዮጵያ የሙስና ቅኝት ጥናት የሚያሳየው፤ አነስተኛ ሙስና እንደሚበዛ ነው፡፡ አነስተኛ ሲባል ግን እያቃለልነው አይደለም። አብዛኛውን የህብረተሠብ ክፍል መቀነት የሚያስፈታና መከራ የሚያሳይ፣ በአገልግሎት አሠጣጥ ላይ እንዲጐሳቆል የሚያደርግ የሙስና አይነት ነው፡፡ ስለዚህ አነስተኛው ተብሎ የሚናቅ አይደለም፡፡ ብዙ ጊዜ የሚከሠቱትና ብዙዎቻችንን የሚያስለቅሱት እንደዚህ አይነት ሙስናዎች ናቸው። ሌላም አገር ብትሔጂ ትልልቅ ሙስናዎች በየዕለቱ አይፈፀሙም፡፡ ለዚህ ይሆናል ህብረተሠቡ ትልልቅ ሙስናዎች ላይ አታተኩሩም የሚለው፡፡ እለት በእለት እየተፈፀሙ ያሉት አነስተኛ የምንላቸው ናቸው፡፡ ለሙስና ተጋላጭ ከሆኑ ተቋማት በቀዳሚነት የምትጠቅሱት ጉምሩክን ነው፡፡ ሁለተኛስ? ገቢዎችና ጉምሩክ ለሙስና የተጋለጠ አካባቢ ነው ስንል፣ አንዳንዶች ሠራተኞቹ በሙስና የተዘፈቁ እና በሙስና የተጨማለቁ አድርገው ይወስዱታል። ይሔ ትክክል አይደለም፡፡

ለሙስና የተጋለጡ የምንላቸው፤ ጥንቃቄ ልናደርግባቸውና አይናችንና ሁለንተናችን ሊያርፍባቸው የሚገባ አሳሳቢዎቹ ቦታዎች ለማለት ነው፡፡ ከእነዚህ አካባቢዎች አንዱ ገቢዎችና ጉምሩክ ነው፡፡ በመቀጠል የኮንስትራክሽን ዘርፍ፣ ትልልቅ የመንግስት ግዢዎች፣… ቴሌኮም፣ የሀይል አቅርቦት፣ የመሬት አስተዳደር፣ ፍቃድ ሠጪ አካላትና የፍትህ አካላት… ለሙስና የተጋለጡ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ በአገራችን የተሰሩ አንዳንድ ጥናቶችም የሚያሳዩት እነዚህ አካባቢዎች ለሙስና የተጋለጡ መሆናቸውን ነው፡፡ ተጠርጣሪዎቹን በምትይዙበት ወቅት የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ዋና ዳሬክተር አቶ መላኩ ፈንቴ የአዲስ አበባ መስተዳድር ምክር ቤት አባል መሆናቸውን አታውቁም ነበር? በእኛ እምነት ተጠርጣሪው ይሔንን ቢገልፁልን ጥሩ ነበር፡፡ ሆኖም ቅሬታቸውን አቅርበው ፍ/ቤት ለግንቦት 19 ማስረጃቸውን እንዲያቀርቡ አዟል። እኛ ያው ህግን ተከትለን ነውና የምንሠራው ምን እንደሚሆን ወደፊት እናያለን፡፡

በእኛ በኩል መርመሪዎቻችን ይወቁ አይወቁ ገና አላወቅሁም። ግን አባል ከሆኑም ምን ይደረጋል የሚለውን እንወስናለን፡፡ ጥያቄው ከመብት ጋር የሚያያዝ ነው፡፡ እኛ ግን ምርመራችንን እንቀጥላለን፡፡ አባልነታቸው ከተረጋገጠ ክሱ ይቋረጣል? አይቋረጥም፡፡ ከዚህ በፊትም አጋጥሞናል። ለምሳሌ የቤንሻንጉል አፈ ጉባኤ ያለመከሠስ መብት አላቸው፡፡ ያንን መብታቸውን የማስነሳት አግባብ ስላለ፣ ያንን በማድረግ ጉዳዩን ወደ ፍ/ቤት ወስደናል፡፡ በአሁኑ ሁኔታ ግን ገና ምርመራ ላይ ነን። ክስም አልተመሠረተም፡፡ በአገሪቱ የሚፈፀሙትን የሙስና ወንጀሎች በሙሉ የመመርመር አቅም አላችሁ? የአቅም ጉዳይ በብዙ መንገዶች ይከፈላል። የሠው ሀይል ሊሆን ይችላል፡፡ የማቴሪያል ጉዳይ ሊሆንም ይችላል፡፡ ከሙስና ጋር የተያያዙ ነገሮችን ለመመርመር አቅም ያንሰናል የሚል ሀሳብ የለኝም። ነገር ግን የተሟላ ነገር አለን ለማለት አልችልም። የማስፈፀም ችግሮች በሁሉም በኩል የሚታዩ ናቸው፡፡ በእኛም በኩል ይሔ ችግር የለም ብሎ መደምደም አይቻልም፡፡ በአንድ ቦታ ያለን አቅም፣ በሌሎች ተለዋዋጭ ቦታዎች ላይሠራ ይችላል።

አቅም የመገንባቱ ስራ የማያቋርጥ ነው። በአንዱ ነገር አቅም ቢኖረን በሌላው ነገር ደግሞ ክፍተት ሊኖር ይችላል፡፡ አቅም አንዴ የሚገነባ ነው ማለት አይቻልም፤ ነገር ግን አሁን ባለንበት ሁኔታ ጥሩ የሆነ አቅም አለን፡፡ በተጨማሪ ደግሞ ከዚህ በፊት እንዳደረግነው ከሌሎች መንግስታዊ መ/ቤቶች ጋር በመቀናጀት እንሠራለን፡፡ የመረጃ ልውውጥ እናደርጋን፡፡ ለምሳሌ ከፖሊስ፣ ከመረጃና ደህንነት፣ ከዋና ኦዲተሮች ጋር የምንሠራበት ጊዜ አለ፡፡ ኦዲተሮች የእነሱን ሙያ የሚጠይቁ ነገሮች ኦዲት አድርገው እንዲልኩልን እናደርጋለን፡፡ አስፈላጊ ከሆነም የሌሎችን አቅም እንጠቀማለን። ይሔንን በማጠናቀር የበለጠ ሀይል በመያዝ የተለያዩ ስራዎችን እንሠራለን፡፡ ህብረተሠቡም አንዱ ሀይላችን ነው፡፡ ጥቆማ የሚሰጠውና ምስክር የሚሆነው ህብረተሠቡ ነው፡፡ ስለዚህ አቅም የሚባለው ነገር በዚህ በኩል እየተገነባና እየተሠራ የሚሔድ ነው፡፡ የአሁኑ ተጠርጣሪዎችን ጉዳይ ወደ እናንተ ያመጣው ግለሠብ ነው ወይስ ተቋም? ጥቆማውን ማን ሠጠው የሚለውን ነገር ለመናገር ይከብዳል፡፡ ነገር ግን ለእኛ ነው መጀመሪያ የተነገረን፡፡ ስለዚህ ይሔንን ሁኔታ ለማየትና ከሌሎች አካሎች ድጋፍ ለማግኘት ከቀድሞ ጠ/ሚ አስፈላጊው መመሪያ እንዲሠጥ አድርገን፣ በጋራ ስንሠራ ነው የቆየነው፡፡

በጥንቃቄ ለመሠራቱ ማሳያው አብዛኛዎቹ ተጠርጣሪዎቹ በስራ ገበታቸው ላይ እንዳሉ ነው የተያዙት፡፡ እኛ በቂ መረጃ እስኪኖረን ድረስ ምንም አይነት ነገር ማድረግ ስላልፈለግን ስራቸውን እንዲሠሩ ትተናቸው ነበር፡፡ ኮሚሽኑ ሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናትን ለመመርመር ድፍረት አግኝቷል ወይስ አሁንም ጠ/ሚኒስትሩን ማስፈቀድ አለባችሁ? ድሮም የሙስና ወንጀል በማንም በምንም ይፈፀም ድፍረት ያጣንበት ጊዜ የለም፡፡ ሠዎች እንደዚህ አይነት ሀሳብ ሊኖራቸው ይችላል። እኛን የሚያሳስበን ግን ሠዎችን ለመያዝና ወደ ህግ ለማቅረብ በቂ ማስረጃ አለን ወይ የሚለው ነው። ድፍረታችን የሚወሰነው ባለን ማስረጃ ነው። ሠዎችን ደፍረን ለመጠየቅና ፍ/ቤት ለመውሠድ የሚያስችለን ማስረጃ ካለን ምንም የሚያስፈራን ነገር የለም። በዚህ ሁኔታም ከዚህ በፊት ጠይቀናል። አሁንም ከፍተኛ ባለስልጣንን እየጠየቅን ነው። ነገም ማስረጃ ካለን እንጠይቃለን፡፡ ሌላው እኛ ማንንም ሠው ለመያዝ ጠ/ሚኒስትሩን አንጠይቅም። ምናልባት ጠ/ሚኒስትሩን ጠየቀን ያልነው፣ ሌሎች አካላት ድጋፍ እንዲሰጡን ከማድረግ አኳያ እንጂ እኛ ነፃነት አለን፡፡

በኮሚሽኑ አዋጅ ውስጥ በምርመራ ሁኔታ ላይ ያለማንም ጣልቃ ገብነት መስራት እንዳለብን ይደነግጋል፡፡ እስካሁን ጣልቃ ገብቶ ይሔንን አድርግ ያለን አካል የለም፡፡ ከተቋቋማችሁ ጊዜ ጀምሮ ከፍተኛ ምርመራ ጠይቆ የተሠራው የሙስና ወንጀል የአሁኑ ነው ማለት ይቻላል? በእኛ እምነት አሁን እያደረግን ያለነው እንቅስቃሴ ትልቅ ድል ነው፡፡ በፍ/ቤት ተከራክረን በመርታት አጥፊዎች ተገቢውን ቅጣት አግኝተው ያለ አግባብ የተወሠደው የመንግስትና የህዝብ ሀብት እንዲመለስ በማድረግ፣ ሂደቱን በውጤት ስንቋጨው ትልቅ ከሚባሉ የሙስና ወንጀሎች አንዱ እንደሚሆን እርግጠኛ ነኝ፡፡ አንዳንድ ባለሀብት ለስራው የጥሬ እቃ አቅርቦት ያጣና ከውጪ ለማስገባት ሲል ካቅሙ በላይ በሆነ ችግር ጉቦ ተጠይቆ ሊከፍል ይችላል፡፡ ይሄና ያልተገባ ሀብትን ለማፍራት የሚፈፀሙ የሙስና ድርጊቶችን በእኩል ዓይን ነው የምታዩት? ነጋዴው እንዲህ አይነት ችግር ሲደርስበት ሙስና ውስጥ ገብቶ እራሱን፣ ሀብቱንና ቤተሠቡን ችግር ላይ መጣል የለበትም፡፡ እንደ እኛ አይነት አካላት አሉ፡፡ እዛ ሔዶ ችግሩን ማስረዳት እና ችግሩን እንዲፈቱለት ማድረግ እንጂ ወንጀል ውስጥ እየገቡ ተቸግሬ ነው ማለት አያዋጣም፡፡ ይሄ ራስን ለማበልፀግ ካለ ፍላጐት የሚመነጭ እንጂ ምክንያት ሆኖ ሊቀርብ የሚችል አይደለም፡፡

Read 4845 times