Sunday, 03 March 2013 00:00

ሰው በመግጨት የተጠረጠሩት የአዋሽ ባንክ ፕሬዚዳንት ለሳምንት ተቀጠሩ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(2 votes)

“ዜብራ” ላይ ሰው ገጭተው ሸሽተዋል ተብለው በፖሊስ የተያዙት የአዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ፀሐይ ሽፈራው የዋስትና ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን፤ ፖሊስ ምርመራ አለመጨረሱንና የምስክሮችን ቃል ተቀብሎ አለማጠናቀቁን ስለገለፀ ለሳምንት ተቀጠሩ፡፡
ከትላንት በስቲያ ከሰዓት በኋላ በርካታ የአዋሽ ባንክ ሠራተኞች በተገኙበት የቂርቆስ ምድብ ችሎት፤ ፖሊስ ተጠርጣሪውን ለምን በጧት ወደ ችሎት እንዳላቀረቡ ዳኛው የጠየቁ ሲሆን ፖሊስም ከፊል የምስክሮችን ቃል ተቀብሎ ገሚሶቹን ስላላገኘ መሆኑን ገልጿል፡፡
ዳኛው በመቀጠልም “ምስክሮች ቃላቸውን የሰጡት የመኪናውን ታርጋ ቁጥር በማየት ብቻ ነው ወይስ ተጠርጣሪውን ፊት-ለፊት እያዩ ነው?” በማለት ጠየቁ፡፡ የፖሊስ መርማሪው ምስክሮች ቃላቸውን የሰጡት ተጠርጣሪውን እያዩ እንዳልሆነ ገለጸ፡፡ በዚህ ጊዜ የተጠርጣሪው ጠበቆች በአቶ ፀሐይ ላይ የቀረበው መረጃ የዋስትና መብት የማያስከለክል በመሆኑ በዋስ ተፈትተው በተጠየቁ ጊዜ እንዲቀርቡ ጠይቀው ነበር፡፡
ዳኛውም፤ አቶ ፀሐይ ክስ ሳይመሠረትባቸው ፖሊስና ጠበቆች ክርክር ውስጥ እየገቡ መሆኑን ጠቅሰው፣ ፖሊስ አሉኝ ያላቸውን ምስክሮች አቅርቦ ተጠርጣሪውን እያዩ ቃላቸውን እንዲሰጡ፣ ከዚያ በኋላ የግራ ቀኙን ሐሳብ አይተው፣ የዋስ መብት ያሰጣል ወይስ አያሰጥም ብሎ ለመወሰን ለማክሰኞ የካቲት 26 ቀን 2005 ቀጠሮ ሰጥተዋል፡፡
ይህ በእንዲህ ያለ ሪፖርተር ጋዜጣ በረቡዕ እትሙ “የአዋሽ ፕሬዚዳንት ገጭቶ በመግደል ተጠርጥረው ተያዙ” በሚል ርዕስ ባቀረበው ዘገባ አዋሽ ባንክ ክፉኛ ማዘኑን ገልጿል፡፡
የባንኩ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ከትናንት በስቲያ በሰጡት መግለጫ፤ አቶ ፀሐይ በፖሊስ ቁጥጥር ስር መሆናቸውን አልሸሸጉም፡፡ ነገር ግን ሪፖርተር ጋዜጣ “አቶ ፀሐይ ሰኞ ምሽት አቧሬ አካባቢ በተሽከርካሪ ገጭቶ በመግደልና ማምለጥ ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ዋሉ” በማለት ያወጣው ዘገባ፣ ለአንባቢ ትክክለኛ መረጃ የማይሰጥና በጣም አሰቃቂ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በዕለቱ አቶ ፀሐይ መደበኛ ሥራቸውን ካጠናቀቁ በኋላ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ወደሚሠሩበት በሻሌ ሆቴል መሄዳቸውን፣ እዚያም እስከ 2፡45 ገደማ ቆይተው ወደ ቤታቸው ሲሄዱ፣ ሲ ኤም ሲ አደባባይ ጋ ወደ ሰሚት የሚወስደውን መንገድ በመያዝ መኪናቸውን አቁመው ከአንድ የሥራ ባልደረባቸው ጋር ሥለሥራ ጉዳይ ሲያወሩ፣ ማንነታቸውን የማያውቋቸው ሰዎች ከጨለማ ውስጥ በመውጣት መኪናቸውን ከኋላ፣ ከጐንና ከፊት በድንጋይ በመምታታቸው ንግግራቸውን አቋርጠው መኪናቸውን አስነስተው መሄዳቸውንና ለፖሊስ ደውለው የማያውቋቸው ሰዎች አደጋ ሊያደርሱባቸው በመሆኑ እንዲደርሱላቸው መጠየቃቸውን የሥራ ሃላፊዎቹ ተናግረዋል፡፡
ፖሊስም ፈጥኖ በስፍራው በመድረስ ዕርዳታ እንዳደረገላቸው የጠቆሙት ሃላፊዎቹ፤ ቀደም ሲል አቶ ፀሐይ የሚያሽከረክሩት መኪና ታርጋ “ስኩል ኦፍ ቱሞሮ” አካባቢ ሰው ገጭቶ ማምለጡ ለፖሊስ ሪፖርት ተደርጐ ስለነበር፣ መኪናቸውና አቶ ፀሐይ ለጥያቄ ወደ ጣቢያ መወሰዳቸውን ገልጸዋል፡፡ እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ ሪፖርተር ጋዜጣ ትክክለኛውን መረጃ ሳይዝ፣ የተሳሳተ ዘገባ ማቅረቡ ከ800ሺህ በላይ ደንበኞች ያለውን ባንክ የሚጐዳና የግለሰቡንም ሞራል የሚነካ ነው ብለዋል፡፡

Read 1629 times